ዛምቢያ፡ ድሮኖች ቀረጥ ያልከፈሉ ተሽከርካሪዎችን እያደኑ ነው

የፎቶው ባለመብት, Topsy Sikalinda/ZRA
የዛምቢያ የግብር ባለሥልጣናት ቀረጥ ሳይከፍሉ እቃዎችን የሚያዘዋውሩ ከባድ መኪናዎችን ለመቆጣጠር ድሮኖችን መጠቀም ጀመሩ።
ባሳለፍነው ቅዳሜና እሁድ የዛምቢያ ገቢዎች ባለሥልጣን በድሮኖች በመታገዝ ከዋናው መንገድ በመውጣት ተደብቀው የነበሩ ሰባት ተሽከርካሪዎች መያዛቸውን አስታውቀዋል።
" ድሮኖቹ የፍተሻ ሠራተኞች በማይደርሱባቸው እንዲሁም አደጋ ባለባቸውና ጥንቃቄን በሚጠይቁ ቦታዎች ድረስ በመግባት አሰሳ ያደርጋሉ" ሲሉ የዛምቢያ ገቢዎች ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ቶፕሲይ ሲካሊንዳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህ ሰባት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ፍተሻ ድሮኖቹ 'ካፒሪ ስርነጅ' በተባለ መንገድ በመግባት ማሰስ የጀመሩ ሲሆን ዋናው የተሽከርካሪ መንገድ ባዶ ሆኖ አግኝተውታል፤ ከዚያም ከዋናው መስመር 14 ኪሎሜትር በሚርቅ ጥሻ ውስጥ አመላክተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Topsy Sikalinda/ZRA
በዛምቢያ ወደ ደቡብ አቅጣጫ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች በአብዛኛው ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፣ ማላዊ፣ ወይም ታንዛኒያ የሚመጡ ናቸው።
ኃላፊው ሲካሊንዳ እንዳስታወቁት አብዛኞቹ ተሽከርካሪዎች በጣም በርካታ እቃዎችን ይጭኑና ወደ ፍተሻ ጣቢያው ሲቃረቡ በትንንሽ መኪና ቀንሰው ይጭናሉ ይህም ባለሙያዎቹ ጥርጣሬ ውስጥ እንዳይገቡ ምክንያት ሆኗል።
የዛምቢያ የገቢዎች መሥሪያ ቤት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ገቢውን ለማሳደግ ተስፋ እንዳለው የቀረጥ ባለሥልጣናት ጨምረው ተናግረዋል።













