የላይቤሪያ ሆስፒታል ሰዎች የሟች ዘመዶቻቸውን አስክሬን እንዲወስዱ አሳሰበ

የመቃብር ሥፍራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በላይቤሪያ የሚገኝ አንድ ትልቅ ሆስፒታል ማንነታቸው ያልታወቁ የ15 ሰዎችን አስክሬን ጠያቂ ከሌላቸው ሊቀብር መሆኑን የሆስፒታሉ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ግለሰቦቹ ሕይወታቸው ያለፈው ከባለፈው የአውሮጳዊያኑ ሚያዚያ ወር እስከ ሰኔ ባሉት ጊዜያት ቢሆንም አስከሬናቸው በጆን ኤፍ ኬኔዲ መታሰቢያ ሆስፒታል እስካሁን ሲቆይ 'የኔ ወገን ነው' ብሎ ሊወስድ የመጣ እንደሌለ የሆስፒታሉ አስተዳደሪ ዶ/ር ጀሪ ብራውን ለመንግሥት የራዲዮ ጣቢያ ተናግረዋል።

"አስክሬኖቹን ለመቅበር እቅድ ይዘናል" ሲሉ አስክሬናቸው ግን በአንድ የመቃብር ቦታ ላይቀበሩ እንደሚችሉ አክለዋል።

ይሁን እንጂ ዶ/ር ብራውን እንዳሉት ከሰኔ ወር መጨረሻ እስከ ነሐሴ መጀመሪያ ባሉት ጊዜያት የሞቱት ሰዎች አሁን በታሰበው እቅድ እንደማይቀበሩ አስረድተዋል። ምክንያቱ ደግሞ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው እነርሱን የመፈለጊያ በቂ ጊዜ ለመስጠት እንደሆነ አስረድተዋል።

በላይቤሪያ የኢኮኖሚ እድገት በፍጥነት እያሽቆለቆለ መሆኑ የሰው ልጆችን ዋጋ እያስከፈለ ነው። አብዛኞቹ ላይቤሪያዊያን ለቀብር ሥነ ስርዓት ማስፈፀሚያ የሚከፍሉት ገንዘብ እንኳን የላቸውም።

ሆስፒታሉ ደግሞ ባለው የአቅም ውስንነት እንዲሁም የአስክሬን ማቀዝቀዣ ችግር ምክንያት ሟቾቹን ለረጅም ጊዜ ለማቆየት እንደማይችል ዶ/ር ብራውን አክለዋል።

ዶ/ር ብራውን ጨምረው እንደተናገሩት ሆስፒታሉ በአሁኑ ሰዓት በጣም መሠረታዊ የሆኑ ግብዓቶች እጥረት ያለበት ሲሆን መድሃኒት ለማቅረብም የአገር ውስጥ መድሃኒት አቅራቢዎች እጅ ላይ ወድቋል።

እንደ ዶ/ር ብራውን ከሆነ ሆስፒታሉ በአሁኑ ሰዓት 50 ሺህ ዶላር ለአገር ውስጥ የመድሃኒት ሻጮች ለመክፈል ይገደዳል።

ጆን ኤፍ ኬኔዲ መታሰቢያ ሆስፒታል በአውሮጳዊያኑ 1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተቋቋመ ሲሆን ለምዕራብ አፍሪካ ወሳኝ ሆነ የሕክምና መስጫ ተቋምም ነበር።