ሃዩንዳይ የፀሐይ ብርሀንን የሚሰበስብ ጣሪያ የተገጠመለት መኪና ፈበረከ

የፎቶው ባለመብት, Hyundai
ሃዩንዳይ ባትሪውን ቻርጅ የሚያደርጉ በጣሪያቸው ላይ የፀሐይ ብርሃን ኃይል የሚሰበስብ ጣሪያ የተገጠመላቸው ሶናታ ተሽከርካሪዎችን አስተዋወቀ።
መኪና አምራቹ የኮሪያ ኩባንያ እንዳለው በመኪናው ጣሪያ ያለው የፀሐይ ብርሃን መሰብሰቢያ በቀን ውስጥ ለ6 ሰዓታት ያህል የሚያገለግል ከሆነ 60 በመቶ የሚሆን የመኪና ባትሪ ኃይል ይሰጣል።
የፀሐይ ብርሃን መሰብሰቢያ ጣሪያው ለአዲስ ሞዴል መኪና በቂ የሆነ ኃይል የሚሰጥ ሲሆን 1300 ኪሎሜትር (800 ማይልስ) በዓመት መጓዝ ያስችላል።
ሃዩንዳይ አክሎም የፀሐይ ብርሃን መሰብሰቢያውን ለብቻ በማምረትም ለሌሎች መኪናዎች እንደ አማራጭ የኃይል ምንጭ ለማቅረብም እቅድ እንዳለው ተናግሯል።
የፀሐይ ብርሃን ኃይልን የሚሰበስብ ጣሪያ በመኪናዎች ላይ መግጠም የነዳጅ ፍጆታን ከመቀነሱም ባሻገር ዝቅተኛ የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ልቀት ስላለው የአካባቢን ብክለትም ለመቀነስ ይረዳል ተብሏል።
መካካለኛ የሆነ መጠን ያለው ይህ የሰዎች ማጓጓዣ መኪና የተጠቀመውን ነዳጅ መቆጣጠር የሚያስችል የተሻሻለ ሞተርም ተገጥሞለታል።
በአንድ ዲጂታል ትሬንድ በተባለ የዜና ገፅ ላይ የፃፉት ስቴፈን ኤደልስቲን "ሃይብሪድ እንደ ሶናታ ከሌሎች የኤሌክትሪክ መኪናዎች በተለየ ተመሳሳይ የሆነና አነስተኛ ባትሪ ያላቸው ሲሆን የፀሐይ ብርሃን መሰብሰቢያ ጣሪያው ባትሪውን ቻርጅ ለማድረግ ስለሚረዳ ከፍተኛ ልዩነትን መፍጠር ይችላሉ" ብለዋል።
ሃዩንዳይ በመጠኑም ቢሆን የፀሐይ ብርሃንን የሚያስተላልፍ እና የፀሐይ ብርሃን መሰብሰቢያ የተገጠመለት መኪና እያመረተ ነው።
መኪናው በሰሜን አሜሪካና ኮሪያ በገበያ ላይ እንደሚውል ተገልጿል። ሃዩንዳይ እንዳለውም በሌሎች ክፍለ ዓለማት ለመሸጥ እቅድ የለውም።
በእንግሊዝ ዝቅተኛ የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ልቀት ያላቸው እንዲህ አይነት ተሽከርካሪዎች ከሁለት ዓመታት በላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ዝቅተኛ ሽያጭ ማስመዝገባቸውን የሞተር አምራችና ሻጭ ማህበረሰብ (SMMT) ባለፈው ወር በሪፖርቱ አስታውቋል።
ኤስ ኤም ኤም ቲ ለመኪኖቹ የሽያጭ መቀነስ ወጥነት የጎደላቸው ፖሊሲዎችና ለሃይብሪድ መኪናዎች ከመንግሥት ይደረግ የነበረው በሚገባ ያልታሰበበት ድጋፍ መነሳቱ እንደሆነ ያስቀምጣል።
ሃዩንዳይ የፀሐይ ብርሃን መሰብሰቢያ የተገጠመለት መኪና በማምረት የመጀመሪያው የመኪና አምራች አይደለም።
እንደ ቶዮታ ፕሪየስ እና ቅንጡ የሆነው ካራማ ሬቬሮ መኪኖች የፀሐይ ጉልበትን በአማራጭነት ይገለገሉበታል።
ከዚህም በተጨማሪ ኔዘርላንድስ ላይትይር የፀሐይ ብርሃንን ጉልበት በመጠቀም የመኪናውን ባትሪ መሙላት የሚችሉ በሞተር መሸፈኛው ላይ እና በጣራው ላይ የፀሐይ ብርሃን መሰብሰቢያ የተገጠመላቸው መኪኖችን ለማምረት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ይህ ላይትይር በአውሮፓዊያኑ 2021 ገበያ ላይ ሲውል የአንዱ መኪና ዋጋ 149 ሺህ ዩሮ (137 ሺህ ፓውንድ) እንደሚያወጣ ይጠበቃል።















