የቀድሞዋ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢኮኖሚውን አንኮታኩተዋል በመባላቸው ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ አሉ

የቀድሞዋ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትሩስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የቀድሞዋ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትሩስ የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት ለውድቅት ዳርገውታል በማለት የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር መናገራቸውን ተከትሎ ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ አሉ።

ሊዝ ትሩስ ለኬይር ስታርመር ይህንን ንግግራቸውን እንዲያቆሙ ህጋዊ ደብዳቤ ልከውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊዝ ምጣኔ ኃብቱን ለውድቀት መዳረጋቸውን አስመልክቶ በተደጋጋሚ የሰጧቸው አስተያየቶች "ሃሰተኛ እና ስም ማጥፋት" ነው ሲሉ ጠበቆቻቸው ተከራክረዋል።

እነዚህ ንግግሮች የቀድሞዋ መሪ የፖለቲካ ህይወት እንደጎዳው እና በደቡብ ምዕራብ ኖርፎክ ግዛትን ወክለው ባደረጉት የብሔራዊ ምርጫ መቀመጫቸውን አሳጥቷቸዋል ሲሉ ጠበቆቻቸው ይናገራሉ።

ትሩስ በዩናይትድ ኪንግደም የስልጣን ዘመን ታሪክ ለአጭር ጊዜ በስልጣን የቆዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው።

ከ49 የስልጣን ቀናት ቆይታ በኋላ መንግሥታቸው በነበረው አነስተኛ በጀት ምክንያት የብድር ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን ተከትሎ ከስልጣን ለመልቀቅ ተገደዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር ቃል አቀባይ በበኩላቸው በትሩስ የምጣኔ ኃብት ፖሊሲ ምክንያት የቤት ብድሮቻቸው በከፍተኛ ሁኔታ ለጨመረባቸው "በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች" ይህንን ህጋዊ ደብዳቤ እንዲጽፉ ሃሳብ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬይር ስለ ቀድሞው አስተዳደር ያላቸው አቋም "ንቅንቅ የማይል ነው" ሲል ቃል አቀባዩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

"ምጣኔ ኃብቱን ለውድቀት ዳርጋዋለች የሚለውን ውንጀላ ኪየር ስታርመር ውሸት መሆኑን ስለሚያውቅ አይደግመውም" ሲሉ ትሩስ በኤክስ ገጻቸው ምላሽ ሰጥተዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የታችኛው ምክር ቤት ኃላፊ ሉሲ ፓወል በበኩላቸው "ወግ አጥባቂዎች ኢኮኖሚውን እንዳንኮታኮቱት እውነተኛውን ነገር ከመናገር አናቆምም" ሲሉ ለምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።

በተጨማሪም የታችኛው ምክር ቤት የግምጃ ቤት ዋና ጸሐፊ ዳረን ጆንስ በበኩላቸው የወግ አጥባቂው መንግሥት በግዴለሽነት "በዚህች አገር ያሉ ነዋሪዎችን ህይወት ቀውስ ውስጥ ከቷል" ሲሉ በዚሁ ምክር ቤት ተችተዋል። የፓውንድ ማሽቆልቆል እንዲሁም የመንግሥት ብድር በ16 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛው ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ ነው ይህ አስተያየት እየተሰጠ ያለው።

የዕለት ተዕለት ወጪን ለመደገፍ መንግሥት ያወጣውን ህግ ለማሳካት እየሞከረ ባለበት በዚህ ወቅት እየጨመረ የሚሄዱ ወጪዎች ተጨማሪ የግብር ጭማሬ እንዲሁም ወጪ ቅነሳ ውስጥ መንግሥትን ሊያስገባው እንደሚችል የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።

በታችኛው ምክር ቤት በነበረው በዚህ ስብሰባ ላይ የአገሪቱን የምጣኔ ኃብት ለማረጋጋት "በፋይናንሺያል ገበያዎች ላይ አስቸኳይ የአደጋ ጊዜ ጣልቃ ገብነት አያስፈልግም" ሲሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ጆንስ ምላሽ ሰጥተዋል።