በዩኬ የበረራ ሰልጣኝ በወባ ትንኝ ከተነከሰች በኋላ ሕይወቷ ማለፉ በምርመራ ተረጋገጠ

ኦሪያና ፔፐር

የፎቶው ባለመብት, FAMILY PHOTO

የምስሉ መግለጫ, የኦሪያና ቤተሰቦች፣ ልጃቸው እንደመብረር የሚያስደስታት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም የንግድ አየር መንገድ አውሮፕላን ሰልጣኝ አብራሪ የነበረችው ግለሰብ በወባ ትንኝ ከተነከሰች በኋላ ወደ አንጎል በተሰራጨ ኢንፌክሽን ሳቢያ ሕይወቷ ማለፉ በምርመራ ተረጋገጠ።

ነዋሪነቷ ሰፎልክ፣ በሪይ ሴንት ኤድመንድስ የነበረው የ21 ዓመቷ ኦሪያና ፔፐር፣ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር በቤልጂየም፣ አንትወርፕ እያለች በወባ ትንኝ ከተነከሰች ከአምስት ቀናት በኋላ ሕይወቷ ማለፉ ተገልጿል።    

የሰፎልክ ከፍተኛ የወንጀል መርማሪ የሆኑት ናይጀል ፓርስሊይ፣ ወደፊት ጥሩ ሥራ የሚጠብቃት ወጣት ሞት እጅግ አሳዛኝ ነው ብለዋል።

በኢፕስዊች ከተማ የሚገኘው የሰፎልክ መርማሪ ፍርድ ቤት፣ ኦሪያና በኦክስፎርድ በኢዚጄት የአብራሪ ሥልጠና ፕሮግራምን የጽሁፍ ፈተናዋን አልፋ የበረራ ብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት ወደ ቤልጂየም ማቅናቷን አስረድቷል።

ሰልጣኝ አብራሪዋ በአውሮፓውያኑ ሐምሌ መጀመሪያ ቀኝ ዐይኗ ላይ በወባ ትንኝ ከተነከሰች በኋላ በሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ገብታ እንደነበርና የተነከሰችበት አካባቢ እብጠትና መመረዝ እንደታየበት ተነግሯል።

የፀረ ተህዋስ መድኃኒት ቢታዘዝላትም ከሁለት ቀናት በኋላ ራሷን በመሳቷ የፍቅር ጓደኛዋ መልሶ ወደ ሆስፒታል ወስዷታል።

ከዚያም ከሦስት ቀናት በኋላ ሕይወቷ ሊያልፍ ችሏል።

የሞቷ ምክንያት በነፍሳት ንክሻ ምክንያት በሚፈጠር ኢንፌክሽን ሳቢያ ወደ አንጎል የሚሄደው የደም ሥር መዘጋት [ሴፕቲክ ኢምቦሊ] መሆኑን የሕክምና ማስረጃዎች አመልክተዋል።

መርማሪው ፓርስሊይ፣ ኦሪያና የሞተችበትን ምክንያት ገለጻ ሲያደርጉ፣ ኦሪያና ሕይወቷ ሊያልፍ የቻለው ግንባሯ ላይ ባጋጠማት የነፍሳት ንክሻ በኋላ በተከሰተ አደገኛ የሆነ ኢንፌክሽን ነው ብለዋል።

መርማሪው እንደዚህ ዓይነት አደጋ ከዚህ በፊት አይተው እንደማያውቁም ተናግረዋል።

የምርመራ ውጤቱ በተነበበት ወቅትም የኦሪያና አባት ትሪስታን ልጃቸው “ከአባቷ እና ከወንድሟ ኦሊቨር ጋር እንደመብረር የሚያስደስታት ነገር አልነበረም” ብለዋል።

ኦሪያና የምትወደውን ሰው አግኝታ፣ ሕልሟን ለማሳካት “የአውሮፕላን አብራሪነት ሥልጠና እየወሰደች ነበር” ሲሉም አክለዋል።

የልጃቸው ሞት ምርመራ ከተሰማ በኋላ እናቷ ሉዊዛ በበኩላቸው፣ ለኦሪያና መታሰቢያ ከእንግሊዝ ሴት አብራሪዎች ማኅበር ጋር በመተባበር “ሌሎች ሴት አብራሪዎች ሙያውን እንዲቀላቀሉ ለማበረታታት ነጻ የትምህርት እድል ተዘጋጅቷል” ብለዋል።