ሩሲያ የጦር ምርኮኞችን ገድላለች መባሏን ዩክሬን አወገዘች

የዩክሬን ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሩሲያ የማረከቻቸውን ዘጠኝ የዩክሬን ወታደሮችን ገድላለች መባሏን የዩክሬን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅት አወገዘ።

ድርጅቱ የሩሲያ ኃይሎች በድንበር አካባቢ በሚገኝው ከርስክ ክልል የማረኳቸው የዩክሬን ወታደሮች ላይ ግድያ ፈጽሟል ብሏል።

የድርጅቱ ኃላፊ ዲሚትሮ ሉቢኔትስ ሩሲያ “ሁሉንም የጦርነት ህጎች እና አሰራሮች” ጥሳለች ሲሉ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ለቀይ መስቀል ቅሬታቸውን መጻፋቸውን ተናግረዋል።

ኃላፊውን ይህንን ያሉት የዩክሬን የጦርነት ውሎዎችን የሚተነትነው ድረገጽ፣ ዲፕስቴት የሰው አልባ አውሮፕላን ኦፕሬተሮች ናቸው ያላቸውን ወታደሮች አስክሬን በድሮን በተቀረጸ ቪዲዮ ማውጣቱን ተከትሎ ነው። የሩሲያ ባለስልጣናት ስለቀረበባቸው ክስ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።

ዩክሬን ባልተጠበቀ ሁኔታ የሩሲያን ድንበር ዘልቃ በመግባት ከፈጸመችው ወረራ ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሯቿን በድንበር አካባቢ እንዳሰማራች ይታመናል።

በዲፕስቴት ድረ ገጽ በታተሙ ምስሎች ላይ የውስጥ ሱሪ ብቻ ያደረጉት የዩክሬን ወታደሮች አስክሬኖች በሆዳቸው በኩል ተንጋለው ይታያሉ። አስክሬናቸው የታየበት ስፍራ የእርሻ ቦታ ነው የተባለ ሲሆን ቢቢሲ እነዚህን ምስሎች በተናጠል ማረጋገጥ አልቻለም።

ድረገጹ የገለፀው እነዚህ የዩክሬን ወታደሮች በሩሲያ ኃይሎች መገደላቸውን ነው።

“እነዚህ ተግባራት ሳይቀጡ መታለፍ የለባቸውም። ጠላት ሙሉ ኃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል። አለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲህ አይነት ወንጀሎችን ችላ ሊል አይገባም” ሲሉ ዲሚትሮ በቴሌግራም ገጻቸው አስፍረዋል።

ዩክሬን በጄኔቫ ስምምነት መሰረት የጦር ወንጀል የሆነውን ምርኮቾችን በመግደል ሩሲያን በተደጋጋሚ ስትወነጅላት ይሰማል። ከጥቂት ሳምንታተት በፊት የዩክሬን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሩሲያ ኃይል 93 የዩክሬን የጦር ምርኮኞችን ገድሏል የሚል ሪፖርት አቅርቦ ነበር።

በምስራቃዊ ዶኔትስክ ክልል በተፈጸመው የ16 የጦር ምርኮኞች ግድያ ላይ ምርመራ መክፈቱን አክሎ ገልጿል። ሩሲያ ወታደሮቿ በዩክሬን ጦርነት የጦር ወንጀል ፈጽመዋል መባሏን አትቀበልም።