በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት የ12 ዓመት ኤርትራዊ ስደተኛ መታገቱን ቤተሰቦቹ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, RAHMA
በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ዳባት ወረዳ አንድ ኤርትራዊ የ12 ዓመት ስደተኛ ህጻን ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች መታገቱን ቤተሰቦቹ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ታዳጊው ከዘጠኝ ቀናት በፊት መጋቢት 26፣ 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ላይ ታፍኖ መወሰዱን ገልጸዋል።
አማን መሐመድ የተባለው ታዳጊ ከሚማርበት ዳባት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ ቤቱ በመመለስ ላይ ድንገት ፊታቸውን የሸፈኑ ሦስት ሰዎች የአማንን ፊት በመሸፈን በባጃጅ መውሰዳቸውን ወላጅ እናቱ ወይዘሮ ራሕማ መሐመድ ተናግረዋል።
ከትምህርት ቤት በሚመለስበት ወቅት መንገድ ላይ አግኝቶት የነበረው የ14 ዓመት ወንድሙ ግለሰቦቹ አፍነው ሲወስዱት ተመልክቷል ተብሏል።
ልጁ ታግቶ ከተወሰደ በኋላም በመቶ ሺህ ብሮች እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን እናትየው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“800 ሺህ ብር ከከፈላችሁ ልጃችሁን በደቂቃዎች ውስጥ እናስረክባለን፤ ካልሆነ ግን በዶላር ይጨምራል” ሲሉ እያስፈራሩን ነው ብለዋል።
በዳባት በሚገኘው የኤርትራውያን የስደተኞች መጠለያ ካምፕ አለምዋጭ ውስጥ የሚኖሩት እናት አማርኛ ቋንቋ መናገር እንደማይችሉ እና “ልጄን አፍነው ወስደውታል ከሚሏቸው ግለሰቦች ጋር” በልጃቸው አማካይነት እየተነጋገሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
ራህማ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከአስር ዓመት በፊት ከኤርትራ የተሰደዱ ሲሆን ለስምንት ዓመታትም በትግራይ ክልል በሚገኘው አዲ ሃርሽ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ቆይተዋል።
ሆኖም ጥቅምት መጨረሻ 2013 ዓ.ም. የተቀሰቀውን የትግራይ ጦርነት ተከትሎ ከመጠለያ ማዕከሉ ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል፣ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ዳባት በሚገኘው አለምዋጭ ካምፕ ከሁለት ዓመት በላይ ማሳለፋቸው ገልጸዋል።
ታዳጊው አማን ከተሰወረ ዘጠኝ ቀናትን ያህል ያስቆጠረ ሲሆን እናቱ በአጋቾቹ የተጠየቁት ገንዘብ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ እና እርዳታ ለማግኘት እየጣሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
የታዳጊው አጋቾች “ለወላጅ አባቱ፣ ‘ገንዘብ እንፈልጋለን። ልጅህ ከገንዘብ በላይ ካልሆነብህ ገንዘቡን ሰጥተህ ልጅህን ውሰድ፤ አለበለዚያ ልጄ ተሸጠብኝ እንዳትል’ ብለውታል” ሲሉ ወይዘሮ ራሕማ ይናገራሉ።
በኃዘን ልባቸው የተሰበረው እና ቢቢሲ ሲያናግራቸውም ከእንባቸው ጋር እየታገሉ የነበሩት እናት ከዚህ ቀደም በመጠለያ ካምፑ ውስጥ ዘረፋ ሲፈጸም እንደነበረና ለደኅንነታቸው ሲሰጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
“የደኅንነት ዋስትና የለንም፤ ልጆቻችን ከእኛ ጋር እያሉም ፈጽሞ ደኅንነት ተሰምቶን አያውቅም። ልጄ ከዐይኔ ከተሰወረበት ቀን ጀምሮ እንቅልፍ የለኝም” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በዚህ የስደተኞች መጠለያ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ስምንት ስደተኞች መቁሰላቸው ይታወሳል።
ታጣቂዎች በወቅቱ አዲስ በነበረው መጠለያ በመግባት በፈጸሙት ጥቃት ስምንት ስደተኞች በመሳሪያ ተመትተው እንደቆሰሉም የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታውቆ ነበር።
አለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ ማዕከል ከትግራይ ክልል ለተፈናቀሉ የኤርትራ ስደተኞች ከሁለት ዓመት በፊት የተቋቋመ ማዕከል ነው። ማዕከሉ ከአቅም በላይ በመጨናነቁም በርካታ ቤተሰቦች ከማዕከሉ ወጣ ብሎ በዳባት ከተማ እንዲሰፍሩ መገደዳቸውን የአለም ዋጭ የስደተኞች መጠለያ ማዕከል ጸሐፊ አቶ ዮሴፍ ገብረንጉስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የታዳጊው አማን መሰወርን በተመለከተ የአካባቢው ፖሊስ እንዲያውቀው መደረጉን እና የጸጥታ አካላት ያለበትን ለማወቅ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጸሐፊው ገልጸዋል።
በተጨማሪም በወቅቱ አንዳንድ ተማሪዎች በሰጡት መረጃ መሰረት አንድ የባጃጅ ሹፌር በቁጥጥር ሥር መዋሉንም ተናግረዋል።
አቶ ዮሴፍ እንደሚሉት ከሆነ እንደዚህ ዓይነት ክስተቶች አዲስ እንዳልሆኑ እና ከዚህ ቀደም ወደ አምስት የሚጠጉ ህጻናት ታግተው መወሰዳቸውን እና ገንዘብ ተከፍሎ እንዲለቀቁ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ካለፈው ዓመት ማብቂያ ወዲህ ባለፉት ስድስት ወራት በአማራ ክልል ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች የሚካሄደው ግጭት የቀጠለ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።
በሁለቱ ኃይሎች መካከል በሚካሄደው ግጭት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሚደርሰው ጉዳት ባሻገር በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች አሳሳቢነት በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ድርጅቶች እየተገለጸ ይገኛል።
ስደተኞቹ ግጭቱ ለደኅንነታቸው አስጊ እንደሆነና በአካባቢው እየደረሰ ያለው አፈና እና የጸጥታ ችግር ለተለያዩ ችግሮች እያጋለጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የሰዎች በታጣቂዎች የመታገት ዜና እንግዳ መሆኑ ከቀረ ሰነባብቷል። ክስተቱም በተወሰኑ መጥፎ ዕጣ በገጠማቸው ሰዎች ላይ የሚከሰት ሳይሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እና በብዛት የሚያጋጥም ስጋት ሆኗል።
አልፎ አልፎ በተለያዩ አካባቢዎች ይፈጸም የነበረው እገታ አሁን መልኩን ቀይሮ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ማጋጠሙን የሚገልጹ ሪፖርቶች እየወጡ ይገኛሉ።
ከቤት ሠራተኞች እስከ ታጣቂዎች ድረስ ይህ ለገንዘብ ሲባል የሚፈጸመው እገታ በርካቶችን ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ዳርጓል።
ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከጥቂት ሺህ ብሮች ጀምሮ እስከ ሚሊዮኖች ድረስ ለመክፈል የተገደዱም በርካቶች ናቸው።












