ኢትዮጵያ ወደ ፑንትላንድ የጦር መሳሪያ እያስገባች ነው ስትል ሶማሊያ ከሰሰች

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ፊቅ

የፎቶው ባለመብት, MoF Somalia

የምስሉ መግለጫ, የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ፊቅ
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የጦር መሳሪያዎች በሕገወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ በኩል ወደ ፑንትላንድ እየገባ ነው ሲል የሶማሊያ መንግሥት ከሰሰ።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር አርብ መስከረም 10/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ የተፈጸመ ነው ያለውን ድርጊት በብርቱ አውግዟል።

ሶማሊያ ይህ ዓይነቱ እና መጠኑ ያልተገለጸ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ በኢትዮጵያ ድንበር በኩል የግዛቷ አካል ወደሆነችው ከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ ክልል እየገባ ስለሆነ ድርጊቱ እንዲቆም አሳስባለለች በመግለጫዋ።

ቢቢሲ ከሶማሊያ መንግሥት በኩል የተሰነዘረውን ክስ በተመለከተ የኢትዮጵያን መንግሥት ምላሽን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

የፑንትላንድ ማስታወቂያ ሚኒስትር ከኢትዮጵያ ገባ የተባለውን የጦር መሳሪያን በተመለከተ ጉዳዩ በማኅበራዊ ሚድያ ላይ ሲዘዋወር ከማየታቸው ውጪ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ከኢትዮጵያ ወደ ግዛታቸው አለመግባቱን ለቢቢሲ ሶማሊኛ ተናግረዋል።

የሶማሊያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ላይ ይህ የጦር መሳሪያ ዝውውሩ የሶማሊያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር ከመሆኑም ባሻገር፣ ቀጠናውን ወደ ትርምስ እንዲያመራ መንገድ የሚከፍት ሊሆን ይችላል ብሏል።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር በመግለጫው አሁን ከኢትዮጵያ ወደ ፑንትላንድ ግዛት የጦር መሳሪያ የጫኑ ሁለት ተሽከርካሪዎች “ያለ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወይንም ይሁንታ” መላካቸውን ጠቅሶ ይህ ግልጽ የሉዓላዊነት ጥሰት ነው ሲል ከሷል።

ይህም በሰነድ የተደገፈ ማስረጃ ያለው ጉዳይ መሆኑን መግለጫው የጠቀሰ ቢሆንም በይፋ የቀረበ ማስረጃ የለም።

በኢትዮጵያ በኩል ተፈጽሟል የተባለው ድርጊት በሶማሊያን የግዛት አንድነት ላይ የተሰነዘረ ጥሰት ማሳያ ነው በማለት፣ ክስተቱ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ሕግ እና ለቀጣናው መረጋጋት ያላት ፈቃደኝነት አሳሳቢ መሆኑን በመጥቀስ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ተግባሩን በፍጥነት እንዲያቆም አሳስቧል።

በተጨማሪም የጦር መሳሪያ ወደ ሶማሊያ ግዛት የማስገባት ድርጊት በኢትዮጵያ ሲፈጸም የመጀመሪያው አይደለም ያለ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ወደ ጋልሙደግ እና ባይዶዋ ክልል በአየር ጭምር የጦር መሳሪያ ተሸጋግሯል ብሏል።

በወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቀረበው ክስ በሰጠው ምላሽ ወደ ጋልሙዱግ ግዛት ገብቷል ከተባለው የጦር መሳሪያ ጋር አገሪቱ የሚያገናኛት ነገር እንደሌለ በመግለጽ ክሱን አስተባብሎ ነበር።

በሶማሊያ ውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር የወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ከዚህ ድርጊቷ እንድትታቀብ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውግዘቱን እንዲያሰማ ጠይቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሶማሊያ መንግሥት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ በማዕከላዊ ሶማሊያ ጋልሙዱግ ግዛት የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ግዛቱ የጦር መሳሪያ አስገብቷል በማለት ቢከስም የአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት ክሱን ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በወቅቱ የሶማሊያ መንግሥት ከኢትዮጵያ በድብቅ የገባ ጦር መሳሪያን የሶማሊያ የደኅንነት ኃይሎች ይዘው ሲያጓጉዙ ነበር ያለ ሲሆን፣ የጋልሙዱግ ግዛት የደኅንነት ምክትል ኃላፊ አሊ ባሺ አብዱላሂ ጦር መሳሪያውን ሲያጓጉዙ የነበሩት የሶማሊያ መረጃ እና የደኅንነት ኤጀንሲ አባላት ናቸው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ይህ አወዛጋቢ የጦር መሳሪያ በጋልሙዱግ ግዛት ውስጥ በሚገኙ ሚሊሻዎች ጥቃት ተፈጽሞበት በነዋሪዎች ጭምር መዘረፉ ይታወሳል።

ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ላይ ከደረሰች በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረት ነግሷል።

ኢትዮጵያ በኤደን ባሕረ-ሰላጤ የባሕር ኃይል ሰፈር እንድትገነባ እና የባሕር በር እንዲኖራት የሚያስችል ነው የተባለው የመግባቢያ ሰነድ፣ በምትኩ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድን የአገርነት እውቅናን በይፋ እንደምትሰጥ ተነግሯል።

ሶማሊላንድን የራሷ ግዛት አድርጋ የምትቆጥረው ሶማሊያ ይህ ስምምነት ሉዓላዊነቷን እና የግዛት አንድነቷን የሚጥስ ነው በማለት ቁጣዋን የገለጸች ሲሆን፣ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ጋር ለዓመታት የዘለቀ ውዝግብ ውስጥ ካለችው ግብፅ ጋር የፈረመችው ወታደራዊ ስምምነት የተፈጠረውን ውጥረት አባብሶታል።

ስምምነቱን ተከትሎ ሁለት የግብፅ ወታደራዊ አውሮፕላኖች የጦር ሠራዊት እና ወታደራዊ ቁሳቀሶችን ጭነው የሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ማረፋቸው ደግሞ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት አማካይነት ሌሎች አገራት እንዲሳተፉበት በር የከፈተ ሆኗል።

ኢትዮጵያ የግብፅ አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ ገብተው ማረፋቸውን ተከትሎ ጎረቤት አገር ሶማሊያ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥሉ ኃይሎችን እያስጠለለች ነው በማለት ማስጠንቀቋ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መንግሥት መካከል የተፈጠረው ውጥረት በንግግር እንዲረግብ የቱርክ መንግሥት ባለፉት ወራት ተከታታይ ጥረት ሲያደረግ ቆይቷል።