ረዥም ዕድሜ የመኖርን ሚስጥር ይዘዋል የተባሉት የአይጥ ዝርያዎች

የፎቶው ባለመብት, Washington Post via Getty Images
ወጣ ወጣ ያለ ጥርስ ያላቸው ቋሊማ የሚመስሉ እንግዳ ፍጥረቶች፣ ፀጉር የሌላቸው፣ ከመሬት በታች የሚኖሩ አይጦች ናቸው።
እናም ረዥም ዕድሜ የመኖር ምስጢርን የያዘ ዘረመል መያዛቸው በቅርቡ ተደርሶበታል።
እንግዳ በሆነው 'ኔክድ ሞል አይጥ' ላይ የተደረገ አዲስ ጥናት እንስሳቱ ረዥም ዕድሜ መኖራቸውን የሚያብራራ የዲኤንኤ መጠገኛ ዘዴ እንደፈጠሩ ያሳያል።
እነዚህ ጉድጓድ ቆፍረው የሚኖሩ አይጦች ረዥሙ የሕይወት ዘመናቸው ወደ 40 የሚጠጋ ሲሆን ይህም የዓለማችን ረዥሙ የአይጥ ዕድሜ ባለቤት ያደርጋቸዋል።
በሳይንስ ጆርናል ላይ የታተመው አዲሱ ግኝት ለምን ኔክድ ሞል አይጦች ከእድሜ ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎችን የመቋቋም ችሎታ ኖራቸው የሚለው ላይ ብርሃን ሊፈነጥቅ ይችላል።
እንስሳቱ ካንሰርን፣ የአንጎል እና የአከርካሪ አጥንት መድከምን እና የመገጣጠሚያ ሕመምን የመቋቋም ችሎታ አላቸው።
ስለዚህ ብዙ ሳይንቲስቶች አካላቸው እንዴት እንደሚሰራ የበለጠ ለመረዳት ይፈልጋሉ።
ይህ ጥናት፣ በቻይና፣በሻንጋይ ቶንጂ ዩኒቨርሲቲ በሚገኝ ቡድን የተመራ ሲሆን ትኩረቱ የዲኤንኤ ጥገና በሰውነታችን ሴሎች ውስጥ ያለ ተፈጥሯዊ ሂደት ነበር።
የዲኤንኤ ክፍሎች፣ የዘረ መል ግንባታ ሂደት ሲበላሽ ሌላ ያልተበላሸ የዲኤንኤ ክፍል ብልሽቱን ለመጠገን እንደ አብነት ያገለግላል።
የዚህ ምርምር ትኩረት በዚያ የጉዳት ዳሰሳ እና ጥገና ስርዓት ውስጥ ሚና ያለው ፕሮቲን ላይ ነበር።
አንድ ሕዋስ ጉዳት መፈጠሩን ሲያውቅ ከሚያመነጨው ንጥረ ነገር ውስጥ አንዱ ሲ-ጋስ (c-GAS) የሚባል ፕሮቲን ነው።
ያ ፕሮቲን በርካታ ሚናዎችን ይጫወታል፤ ነገር ግን የእነዚህን ሳይንቲስቶች ትኩረት የሳበው ነገር በሰዎች ውስጥ ዲኤንኤ አንድ ላይ የመገጣጠም ሂደት ውስጥ ጣልቃ የሚገባ እና የሚያደናቅፍ መሆኑ ነው።
የሳይንስ ሊቃውንት ይህ ጣልቃ ገብነት ካንሰርን ሊያስፋፋ እና እድሜያችንን ሊያሳጥረው ይችላል ብለው ያስባሉ።
በኔክድ ሞል አይጦች ውስጥ ግን ተመራማሪዎቹ ተመሳሳይ ፕሮቲን ተቃራኒውን ሲያከናውን ተመልክተዋል።
ሰውነታችን የዲኤንኤ ሰንሰለቶችን እንዲጠግን እና በእያንዳንዱ ሕዋስ ውስጥ ያለው የዘረመል ኮድ እንዳለ እንዲቆይ ያደርጋል።

የፎቶው ባለመብት, Chicago Tribune via Getty Images
ፕሮፌሰር ጋብሬል ባልሙስ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የዲኤንኤ ጥገና እና እርጅናን ያጠናሉ።
እነዚህ እንስሳት ለምን በጣም ረዥም ዕድሜ እንደሚኖሩ ለመረዳት ግኝቱ አስደሳች እና "የትልቅ ነገር መጀመርያ" ነው ብለውታል።
"ሲ ጋስን (cGAS) እንደ ባዮሎጂካል ሌጎ ማሰብ ትችላለህ፤ በሰዎች እና በኔክድ ሞል አይጦች ውስጥ ተመሳሳይ መሠረታዊ ቅርጽ አለ። ነገር ግን ሞል አይጥ ስሪት ውስጥ ጥቂት ማያያዣዎች ተለውጠው ሙሉ በሙሉ የተለየ መዋቅር እና ተግባር እንዲገጣጠም ፈቅዷል።"
ፕሮፌሰር ባልሙስ እንዳብራሩት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዓመታት በነበረ የዝግመተ ለውጥ ሂደት፣ኔክድ ሞል አይጦች ያንኑ መንገድ እንደገና በማስተካከል "ለራሳቸው ጥቅም የተጠቀሙበት" ይመስላል።
"ይህ ግኝት መሠረታዊ ጥያቄዎችን ያስነሳል፤ ዝግመተ ለውጥ ተመሳሳይ ፕሮቲንን በተለየ መንገድ እንዲሠራ እንዴት እንደረገ? ምን ተለወጠ? እና ይህ አንድ የተለየ ጉዳይ ነው ወይስ የሰፊ የዝግመተ ለውጥ ንድፍ አካል?"
ከሁሉም በላይ የሳይንስ ሊቃውንት የሰውን ጤና ለማሻሻል እና የሕይወት ጥራትን ከእድሜ ጋር ለማራዘም ከእነዚህ አይጦች ምን እንደሚማሩ ማወቅ ይፈልጋሉ።
"የኔክድ ሞል አይጥ ሥነ ሕይወት እንዴት እንደሚሰራ መረዳት ከቻልን" ይላሉ ፕሮፌሰር ባልሙስ፣ "በእድሜ ለገፋው ማኅበረሰብ በጣም አስፈላጊ የሆኑ የሕክምና ብልሃቶችን ማግኘት እንችላለን።"















