ኬንያ በጥራት ስጋት ምክንያት ታዋቂ የምግብ ዘይት ምርቶችን አገደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኬንያ ከጤናና ጥራት ጋር በተያያዘ ስጋት ምክንያት 10 ታዋቂ የምግብ ዘይት ምርቶች ገበያ ላይ እንዳይውሉ እገዳ ጣለች።
የኬንያ ደረጃዎች ተቆጣጣሪ ኬብስ በችርቻሮ ለሚሸጡ ሱቆች እና መገበያያ መደብሮች በጸፈው ደብዳቤ ላይ እነዚህ ምርቶች መደበኛ የጥራት ፈተናዎችን ማለፍ አልቻሉም ብሏል።
እነዚህ ምርቶች ከሽያጭ መደርደሪያዎች በአስቸኳይ እንዲወርዱ ትዕዛዝ ተላልፏል።
ተቋሙ የተላለፈው ትዕዛዝ ሙሉ እገዳ ሳይሆን አምራቾቹ የተወሰኑ የጥራት መስፈርቶችን እስካሟሉ ድረስ ጊዜያዊ እገዳ መሆኑን አብራርቷል።
ትልልቅ የመገበያያ መደብሮችንና ትላልቅ ቸርቻሪዎችን ላቀፈው የኬንያ የችርቻሮ ነጋዴዎች ማህበር ተቋሙ በጻፈው ደብዳቤ የተጠቀሱት የምግብ ዘይት ምርቶች ወደ ገበያ ከመመለሳቸው በፊት የጥራት ማረጋገጫ ማግኘታቸው ሊረጋገጥ እንደሚገባም አሳስቧል።
እነዚህ 10 የምግብ ዘይት ምርቶች የሚመረቱ በኬንያ የሚጠቀሱ አራት ትልልቅ የምግብ ዘይት ኩባንያዎች ሲሆኑ እነሱም ቢድኮ አፍሪካ፣ ፕዋኒ የዘይት አምራች፣ ካቻ የዘይት ማጣሪያ እና ሜኔንጋይ የዘይት ማጣሪያ ናቸው።
ቢቢሲ ሁለቱን ኩባንያዎች ምላሽ የጠየቃቸው ሲሆን እስካሁን ድረስ ምላሽ አልሰጡም።
ጉዳዩን ለመፍታት ተቋሙ እና ዘይት አምራቾቹ በዛሬው ዕለት አርብ እንደሚገናኙም የኢንዱስትሪ ምንጮች ገልጸዋል።












