ትራምፕ ተጨማሪ 50 በመቶ ታሪፍ ቻይና ላይ ለመጣል ዛቱ

የቻይና ፋብሪካ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዶናልድ ትራምፕ ተጨማሪ 50 በመቶ ታሪፍ ቻይና ላይ ለመጣል ዝተዋል። ቻይና ወደ አሜሪካ የምትልካቸው ሸቀጦች ላይ ቻይና የጣለችው 34 በመቶ ታሪፍ የማይነሳ ከሆነ ተጨማሪ 50 በመቶ ታሪፍ ቻይና ላይ እንደሚጥሉ አስታውቀዋል።

ባለፈው ሳምንት ቻይና ላይ ለጣሉት ታሪፍ በምላሹ ቻይና 34 በመቶ ታሪፍ እንደምትጥል አስታውቃለች። ትራምፕም ቻይና የጣለችውን የአጸፋ ታሪፍ እስከ ማክሰኞ ድረስ ካላነሳች 50 በመቶ ተጨማሪ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀዋል።

ትራምፕ የጣሉትን ታሪፍ በተመለከተ በአሜሪካ የቻይና ኤምባሲ "የምጣኔ ሀብት ጭቆና ነው። መብታችንን ከማስጠበቅ ወደኋላ አንልም" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ትራምፕ ተጨማሪ 50 በመቶ ታሪፍ ቻይና ላይ ከጣሉ የአሜሪካ ተቋማት ከቻይና የሚያስገቡት ምርት በአጠቃላይ 104 በመቶ ታሪፍ የተጣለበት ይሆናል።

ይህም የዓለም ሁለት ትልቅ ምጣኔ ሀብት አገራትን የንግድ ጦርነት እንዳያባብስ ተሰግቷል።

ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው "ከቻይና ጋር ስለ ታሪፍ እንድንነጋገር የተያዘው ዕቅድ ተሰርዟል" ብለዋል።

ከሌሎች አገራት ጋርም ስለ ታሪፍ የሚደረግ ድርድርን ለጊዜው መግታታቸውን አክለዋል።

"ብዙ፣ ብዙ አገራት ከኛ ጋር ለመደራደር እየመጡ ነው። ፍትሐዊ ድርድሮች ይሆናሉ" ብለዋል።

ቻይና የአጸፋ ታሪፍ እንዳትጥል ቢያስጠነቅቁም ቻይና ግን ታሪፍ ለመጣል ወስናለች።

የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ሉ ፔንግዩ "ቻይናን ማስፈራራት ትክክለኛ አካሄድ አይደለም። አሜሪካ ራስ ወደድ ፍላጎቷን ሌሎች አገራትን እየጎዳች ማስፈጸም ትፈልጋለች" ብለዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው "36 ትሪሊዮን ዶላር እዳ ያለብን ያለ ምክንያት አይደለም። ቻይና እና ሌሎችም አገራት ጥሩና ፍትሐዊ ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው። አሁን ጊዜው አሜሪካ ትቅደም ነው" ብለዋል።

በዋናነት ምርታቸውን ወደ አሜሪካ የሚልኩ የቻይና ፋብሪካዎች ዋነኛ ተጎጂ ይሆናሉ።

ቻይና ኤሌክትሮኒክስ፣ የእንጨት ምርት፣ መኪና እንዲሁም ሌሎችም ሸቀጦች ወደ አሜሪካ ትልካለች።

የትራምፕን ታሪፍ ተከትሎ በዓለም አቀፍ የስቶክ ገበያ ላይ መዋዠቅ ታይቷል። የገበያ መቀዛቀዝም ተስተውሏል።

የአሜሪካ ስቶክ ገበያን ጨምሮ ዋና ዋና የአውሮፓ የስቶክ ገበያዎች አሽቆልቁለዋል።

ትራምፕ ታሪፍን በተመለከተ ከአገራት ጋር የሚደረገው ድርድር ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

17% ታሪፍ የተጣለባት እስራኤል ፕሬዝደንት ቤንያሚን ኔታንያሁ ከትራምፕ ጋር ተገናኝተው "በአሜሪካና እስራኤል መካከል የንግድ ሚዛኑን እናስተካክላለን" ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት አረሰላ ቮን ደር ሌን ከዚህ ቀደም አሜሪካ ላይ የአጸፋ ታሪፍ ሊጣል እንደሚችል ቢጠቁሙም አሁን ግን በሁለቱም መካከል የሚደረገው ንግድ ከታሪፍ ነጻ እንዲሆን ለመደራደር አስበዋል።

ትራምፕ ግን ከዚህ ቀደም የአውሮፓ ኅብረት የተፈጠረው "አሜሪካንና ንግዷን ለመጉዳት ነው" ብለዋል።