የእስራኤል ሠፋሪዎች በዌስት ባንክ ፍልስጤማውያንን መግደላቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሁለት ፍልስጤማውያን በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኙ የእስራኤል ሠፋሪዎች በፈጸሙት ጥቃት መገደላቸውን የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የ20 ዓመቱ ጥምር ዜግነት ያለው ሳይፎላህ ሙሳሌት አርብ ማምሻውን በሲንጂል በደረሰበት ድብደባ መሞቱን ሚኒስቴሩ ተናግሯል።
ሳይፎላህ ሙሳሌት የአሜሪካ ዜግነት ያለው ሲሆን ነዋሪነቱ በፍሎሪዳ ነበር ተብሏል።
ሁለተኛው ግለሰብ ደግሞ መሀመድ አል ሻላቢ የተባለው የ23 ዓመት ወጣት ሲሆን ደረቱ ላይ በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ ማለፉን ሚኒስትሩ አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር በሲንጂል አቅራቢያ በእስራኤላውያን ላይ ድንጋይ ከተወረወረ በኋላ "በአካባቢው ከባድ ግጭት ተፈጠሯል" ብሏል።
የጸጥታ ኃይሎች የአንድ ፍልስጤማዊ ሕይወት መጥፋቱን የሚያሳዩ ሪፖርቶችን እየመረመሩ እና በሁለተኛው ላይ የተከሰተውን ደግሞ እየገመገሙ መሆኑንም አክሏል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "በዌስት ባንክ የአንድ አሜሪካዊ መሞቱን እንደሚያውቅ" እና "የቤተሰቡን ነጻነት ለማክበር" በሚል ምንም ተጨማሪ አስተያየት እንደማይሰጥ ተናግሯል።
ሳይፎላህ ሙሳሌት፣ በቅፅል ስሙ ሳይፍ እየተባለ የሚጠራ ነጋዴ ሲሆን ተወልዶ ያደገው ፍሎሪዳ ነው። እአአ ሰኔ 4 ከሚኖርበት ታምፓ ወደ ዌስት ባንክ የሄደው "ከሚወዳቸው ጋር ጊዜ ለማሳለፍ" መሆኑን ቤተሰቦቹ ተናግረዋል።
ቤተሰቦቹ በሰጡት መግለጫ ላይ "የቤተሰቡን መሬት ለመስረቅ ከሚሞክሩ ሠፋሪዎች ለመከላከል በሚሞክርበት ወቅት በእስራኤላውያን ሠፋሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድቦ ሕይወቱ አልፏል" ብለዋል።
"የድንገተኛ ጊዜ የሕክምና ባለሙያዎች ሊደርሱለት በሚሞክሩበት ወቅት የእስራኤላውያን ሠፋሪዎች ሳይፍን ከሦስት ሰዓታት በላይ ከብበውት ነበር፤ ሠፋሪዎቹ አምቡላንስ እና የሕክምና ባለሙያዎች የሕይወት አድን እርዳታ እንዳይሰጡ ከልክለዋል።"
"የከበቡትን የእስራኤላውያን ሠፋሪዎችን ገለል ካሉ በኋላ፣ የሳይፍ ታናሽ ወንድም ወንድሙን ወደ አምቡላንስ አንስቶ ወስዶታል፤ ሳይፍ ሆስፒታል ከመድረሱ በፊት ሕይወቱ አለፏል።"
መግለጫው አክሎም "የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አፋጣኝ ምርመራ እንዲመራ እና ሳይፍን የገደሉትን እስራኤላውያን ሰፋሪዎች ለፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆኑ እንጠይቃለን" ይላል።
የፍልስጤም ይፋዊ የዜና ወኪል ዋፋ እንደዘገበው መሀመድ አል ሻላቢ ከሲንጂል በስተደቡብ የምትገኘው አልማዝራ አል ሻርቂያ ከተማ ነዋሪ ነበር።
የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴርን ጠቅሶ እንደዘገበው ሳይፎላህ ሙሳሌት በተገደለበት በዚሁ ጥቃት በሠፋሪዎች በተተኮሰ ጥይት ደረቱ ላይ ተመትቷል።
የድንገተኛ አደጋ የሕክምና ባለሙያዎች ከመድረሳቸው በፊት ለሰዓታት ደም እየፈሰሰው ነበር ሲልም አክሏል።
ዋፋ በሲንጂል እና አጎራባች አካባቢዎች አውቶማቲክ ጠመንጃ ከታጠቁ ሰፋሪዎች ጋር በተፈጠረ ግጭት ከ10 በላይ ፍልስጤማውያን ቆስለዋል ሲል ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር አርብ ምሽት በሰጠው መግለጫ "አሸባሪዎች ከሲንጂል አቅራቢያ በሚገኙ የእስራኤል ሰላማዊ ዜጎች ላይ ድንጋይ በመወርወር ሁለት ሰው ላይ ቀላል ጉዳት አድርሰዋል" ብሏል።
"በአካባቢው ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን ሰላማዊ ዜጎችን ያሳተፈ ከባድ ግጭት ተፈጠሯል፣ ይህም የፍልስጤማውያኑን ንብረት ማውደም፣ማቃጠል፣አካላዊ ግጭት እና የድንጋይ ውርወራን ያካትታል።"
የአገሪቱ መከላከያ እንዳለው ወታደሮች፣ፖሊሶች እና የድንበር ጠባቂዎች ወደ አካባቢው የተላኩ ሲሆን "አመጽ ለተቀላቀለበት ግጭት ምላሽ ሰጥተዋል" ብሏል።
"በግጭቱ ሳቢያ አንድ ፍልስጤማዊ እንደተገደለ እና በርካቶችመቁሰላቸውን የሚገልጽ ሪፖርት ደርሶናል" ካለ በኋላ የሺን ቤት የጸጥታ ክፍል እና የእስራኤል ፖሊስ እየተመለከተው መሆኑንም አክሏል።
ቢቢሲ ስለተገደለው ሁለተኛው ፍልስጤማዊ መከላከያን የጠየቀ ሲሆን "ሁኔታው በግምገማ ላይ ነው" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
በሌላ በኩል በእየሩሳሌም የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በቅርቡ በዌስት ባንክ ታይቤህ በምትባል የክርስቲያን ከተማ ላይ የእስራኤል ሠፋሪዎች ያደረሱትን ጥቃት እንደሚያወግዝ ገልጿል።
አብዛኛው መሬት በፍልስጤም አሜሪካውያን ባለቤትነት የተያዘ ነው።
እንዲሁም እንደ አካባቢው ነዋሪዎች ገለጻ ወደ 300 የሚጠጉ ነዋሪዎች የአሜሪካ ፓስፖርት የያዙ ናቸው።
ጭንብል የለበሱ ሰዎች ቤቶች ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት እና መኪና ማቃጠል እየተባባሰ መጥቷል።
ሰኞ ዕለት ሠፋሪዎች በአምስተኛው ክፍለ ዘመን እንደተገነባ የተነገረውን ቤተክርስትያንን ማቃጠላቸውን ተከትሎ የከተማው ካህናት ዓለም አቀፍ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በምላሹ በባህር ማዶ ከሚገኙ የአሜሪካ ዜጎች ደህንነት የበለጠ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሌለው እና ክርስቲያኖችን መጠበቅ ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ነው ብሏል።
እስራኤል ዌስት ባንክን እና ምሥራቅ እየሩሳሌምን ከወረረች ጀምሮ 160 የሚጠጉ ሠፈራዎችን ገንብታ 700,000 አይሁዶች አስፍራለች።
3.3 ሚሊዮን የሚገመቱ ፍልስጤማውያን በዚሁ አካባቢ ከእስራኤላውያን ጋር አብረው ይኖራሉ።
ሠፈራዎቹ በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ሕገ ወጥ ተደርገው ይቆጠራሉ።
በጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በዌስት ባንክ ሰፋሪዎች በሰላማዊ ፍልስጤማውያን ላይ የሚፈጸሟቸው ጥቃቶች ተባብሰዋል።
የጋዛ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የእስራኤል ጦር በዌስት ባንክ በፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 910 ፍልስጤማውያን፣ የእስራኤል ሠፋሪዎች ባደረሱት ጥቃት ደግሞ 13 ፣ እና ሌሎች ሰባት በእስራኤል ወታደሮች ወይም ሰፋሪዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።
በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ በዌስት ባንክ ፍልስጤማውያን ባደረሱት ጥቃት በትንሹ 44 እስራኤላውያንም ተገድለዋል።















