የኮቪድ መነሻ የቻይናዋ ዉሃን መሆኗን መረጃዎች ይጠቁማሉ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በቻይናዋ ዉሃን የሚገኘው ሁዋናን የባሕር ምግቦች እና የዱር እንስሳት ሥጋ ገበያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማዕከል እንደነበረ የሚያሳይ “አሳማኝ ማስረጃ” አለ ሲሉ ተመራማሪዎች ገለጹ።

ማክሰኞ የታተሙ ሁለት ጥናቶች በቻይናዋ ከተማ ከመጀመሪያው ወረርሽኝ የተገኘውን መረጃ እንደገና መርምረዋል።

ከጥናቶቹ አንዱ እንደሚያሳየው ቀደም ብለው የታወቁ የቫይረሱ መነሻዎች በገበያው ስፍራ በብዛት ተገኝተዋል።

ሌላው ጥናት የወረርሽኙን የመነሻ ጊዜ ለመለየት የዘረመል መረጃን ተጠቅሟል።

እአአ በኅዳር ወይም በታኅሣሥ 2019 መጀመሪያ ላይ ወደ ሰዎች የተላለፉ ሁለት የበሽታው ዝርያዎች እንዳሉም ተጠቁሟል።

ተመራማሪዎቹ በጋራ እንደገለጹት ይህ ማስረጃ ሳርስ-ኮቭ-2 በ2019 መጨረሻ በሁዋናን ገበያ በተሸጡና በሕይወት ባሉ አጥቢ እንስሳት ላይ ይገኝ እንደነበር ያሳያል ብለዋል።

በሁለት የተለያዩ “ክስተቶች” ቫይረሱ ካለበት እንስሳ በገበያው ወደ ሚሠሩ ወይም ወደ ሚገዙ ሰዎች ተላልፏል ብለዋል።

ከተመራማሪዎቹ አንዱ የሆኑትና በግላስጎው ዩኒቨርሲቲ የቫይረስ ተመራማሪ በመሆን የሚያገለግሉት ፕሮፌሰር ዴቪድ ሮበርትሰን ጥናቶቹ “ቫይረሱ ከላብራቶሪ መጣ የሚለውን የሐሰት ዘገባ ያስተካክላል” የሚል እምነት እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የወረርሽኝ ማዕከል

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኮቪድ-19ን የሚያመጣው ቫይረስን ለመረዳት የተደረገው የሁለት ዓመታት ሳይንሳዊ ጥረት ለእነዚህ ተመራማሪዎች የበለጠ በመረጃ ላይ እንዲመሠረቱ አግዟቸዋል።

ይህም በመጀመሪያዎቹ የታካሚዎች መረጃ ውስጥ ያለውን ቁልፍ ችግር ለመፍታት አስችሏቸዋል። በዉሃን በከቪድ-19 ተይዘው በሆስፒታል ከታከሙ በመቶዎች ከሚቆጠሩት ሰዎች መካከል 50 ያህሉ ብቻ ከገበያው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ነበራቸው ።

ፕሮፌሰር ሮበርትሰን “ብዙዎቹ ከገበያው ጋር ሊገናኙ አለመቻላቸው ግራ የሚያጋባ ነበር” ብለዋል።

“ነገር ግን ስለቫይረሱ አሁን የምናውቀውን ማወቃችን በትክክልም የምንጠብቀው ነገር ነው። ምክንያቱም ብዙ ሰዎች በጣም በመጠኑ ስለሚታመሙ ሕብረተሰቡ ውስጥ ሆነው ቫይረሱን ወደ ሌሎች ያስተላልፋሉ። በዚህም ከፍተኛ ህመም ካጋጠማቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማወቅ አስቸጋሪ ይሆናል።”

ይህ የኮቪድ-19 ጥናት እንደሚያሳየው ቀድመው በዚህ በሽታ የተያዙት አብዛኞቹ ሰዎች ከገበያው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳይኖራቸው ከገበያው አቅራቢያ የሚኖሩ ናቸው።

የአሪዞና ዩኒቨርሲቲ ባዮሎጂስቱ ፕሮፌሰር ሚካኤል ዎሮቤይ እንዳሉት ይህ ገበያው የወረርሽኙ ማዕከል ነው የሚለውን ሀሳብ ይደግፋል። ነጋዴዎች መጀመሪያ በበሽታው ከተያዙ በኋላ “በአካባቢው ባሉ የማኅበረሰብ አባላት መካከል የኢንፌክሽን ሰንሰለት ይፈጥራሉ” ብለዋል።

ጥናት ይበልጥ ትኩረቱን በገበያው ላይ አድርጓል። ሳይንቲስቶቹ የካርታ ልየታ በማድረግ ከውሃ ፍሳሽ ማስወገጃዎች እና ከገበያው ድንኳኖች ላይ ናሙና ወስደው ሲመረምሩ ቫይረሱን አግኝተዋል።

“አብዛኞቹ ቫይረሱ የተገኘባቸው ናሙናዎች ከገበያው ደቡብ ምዕራብ በኩል የተሰበሰቡ ናቸው” ሲሉ ፕሮፌሰር ሮበርትሰን አብራርተዋል።

“ስለዚህ [ለኮቪድ-19 መንስኤ የሆነው የሳርስ-ኮቭ-2] አጋላጭ እንደሆኑ የምናውቃቸው እአአ እንስሳት በ2019 መገባደጃ ላይ ተሽጠው እንደነበር ማረጋገጫ አለን።”

የፎቶው ባለመብት, WOROBEY ET AL

ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ነው ያመለጠ ነው የሚለው ጽንሰ ሃሳብ

ባለፉት ሁለት ዓመታት የወረርሽኙን መነሻ ለማግኘት የሚደረገው ፍለጋ ከሳይንሳዊ ምርመራ ወደ መርዛማ የፖለቲካ ፍጥጫ ተለውጧል።

በዋነኛነት [በተለይም በዩናይትድ ስቴትስ እና በቻይናውያን ፖለቲከኞች መካከል] ከነበሩት ዓለም አቀፍ ወቀሳዎች አንዱ ቫይረሱ ዉሃን የቫይረሶች ምርምር ተቋም ከሚገኘው ቤተ ሙከራ ሊወጣ ይችላል የሚል ጽንሰ ሃሳብ ነበር።

የኪንግስ ኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆኑት ስቱዋርት ኒል እንደሚሉት መላምቱን “በመረጃው ማብራራት አልተቻለም” ብለዋል።

“አሁን በቻልነው መጠን እርግጠኛ ነን። ባለን መረጃ መሠረት ይህ በገበያው ላይ የተከሰተ ትልቅ ክስተት መሆኑን ነው።”

የተጨናነቁና በሕይወት ያሉ የእንስሳት ገበያዎች ከእንስሳት ለሚነሱ አዳዲስ በሽታዎች አመቺ የመተላለፊያ ቦታ ይፈጥራሉ ሲሉ ብዙ ሳይንቲስቶች ይስማማሉ።

ሌላ ጥናት ደግሞ ወረርሽኙ እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ ባሉት 18 ወራት ውስጥ 38 የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ወደ 50,000 የሚጠጉ እንስሳት በዉሃን ገበያዎች ተሽጠው ነበር።

ፕሮፌሰር ኒይል በበኩላቸው ወረርሽኙ “የቻይና ባለሥልጣናት ማስጠንቀቂያ የሰጡባቸው ጤናማ ያልሆኑ፣ ጨካኝ እና ንጽህና የጎደለው ተግባር” ውጤት ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ የሆነን ነገር በቤተ ሙከራ ውስጥ በመፈለግ ትኩረታችንን የመከፋፈል ዋነኛው አደጋ በመሆኑ “በተሳሳተ ችግር ላይ ትኩረት ስላደረግን ይህ እንደገና እንዲከሰት ልንፈቅድ እንችላለን” ብለዋል።