ፈረንሳይ ለቻይና ኩባንያ ይገባል በሚል ለጥገና የመጡ ሶስት የናይጄሪያ ጄቶችን ያዘች

የፎቶው ባለመብት, @NGRPresident
የቻይና ኩባንያ እና የናይጄሪያ መንግሥት የገቡትን እሰጣገባ ተከትሎ የፈረንሳይ ፍርድ ቤት የናይጄሪያ መንግሥት ንብረት የሆኑ ለጥገና የመጡ ሶስት ጄቶችን በቁጥጥር ስር አዋለ።
የቻይናው ዞንግሻን ፉቸንግ ኢንደስትሪያል ኢንቨስትመንት ኩባንያ እና የናይጄሪያ ደቡብ ምዕራብ ኦጉን ግዛት መካከል ነጻ የንግድ ቀጣና ለመመስረት በአውሮፓውያኑ 2007 ከተደረሰ ስምምነት ጋር በተያያዘ ነው ውዝግቡ የተነሳው።
ይህ የንግድ ቀጣና ባለሃብቶችን ለመሳብ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የመገንባት እቅድ የያዘ ነበር።
ሆኖም ግዛቲቷ ከቻይናው ኩባንያ ጋር የገባችው ውል በአውሮፓውያኑ 2015-2016 መካከል እንዲቋረጥ ተደርጓል።
የቻይናው ኩባንያ “በህገወጥ ዘመቻ” ከስምምነቱ እንዲወጣ መደረጉን መናገሩን ፋይናንሺያል ታይምስ ዘግቧል።
የናይጄሪያ ባለስልጣናት አውሮፕላኖቻቸው መያዛቸውን አጥብቀው አውግዘው ዞንግሻን የአፍሪካን መንግሥት “የማጭበርበር እና የማራከስ” አላማ እንዳለው ጠቁመዋል።
ኩባንያው በፓሪስ የፍትህ ፍርድ ቤት ከተወሰነለት በኋላ ሶስት የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት አውሮፕላኖች በፈረንሳይ እንዲቆዩ ተደርገዋል።
አውሮፕላኖቹ በወቅቱ “ጥገና” እየተደረገላቸው እንደነበር የናይጄሪያ መንግሥት አስታውቆ ነበር።
የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ቃለ አቀባይ ባዮ አናኑጋ ዞንግሻን አገሪቱ በውጭ አገራት ያላትን ንብረቶች ለመቆጣጠር ዘመቻ እያካሄደ ነው ሲሉ ከሰዋል።
ከሶስት ዓመት በፊት በዩኬ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የሚመራ የግልግል ፍርድ ቤት የቻይና ኩባንያ 74.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፈለው ወስኖ ነበር። የኦጉን ግዛት ይህንን ገንዘብ ለመክፈል ፈቃደኛ አልሆነም ተብሏል።
በእንግሊዝ ሊቨርፑል ከተማ የናይጄሪያ ንብረት የሆኑ ህንጻዎች በተመሳሳይ በፍርድ ቤት መያዛቸውን የናይጄሪያ ጋዜጣ ፕሪሚየም ታይምስ ዘግቧል።
የአሜሪካ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ኩባንያው የናይጄሪያን በውጪ የሚገኙ ንብረቶችን እንዲወርስ ወስኗል። ፍርድ ቤቱ የናይጄሪያን “የሉዓላዊ ያለመከሰስ መብት” መከላከያንም ውድቅ አድርጎታል።
ናይጄሪያ ኩባንያው በእንግሊዝ፣ በአሜሪካ እና በፈረንሳይ ላሉ ፍርድ ቤቶች የተሳሳተ መረጃ እያቀረበ ነው ስትል ከሳለች።
ቃለ አቀባዩ የኦጉን ግዛት ውል በተቋረጠበት ወቅት ኩባንያው ለነጻ ንግድ ቀጠና ተብሎ በተዘጋጀው መሬት ዙሪያ አጥር ከመዘርጋት የዘለለ ነገር አላደረገም ብለዋል።
የነጻ ንግድ ቀጠና ማለት ዕቃዎች በቅናሽ ወይም ያለምንም ቀረጥ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበት እና የሚወጡበት ስፍራ ነው።
በናይጄሪያ ውስጥ የአፍሪካው ስመ ጥር ባለጸጋ አሊኮ ዳንጎቴ በሌጎስ የተመሰረተው የዳንጎቴ የፔትሮሊየም ማጣሪያን ጨምሮ ሌሎች ነጻ የንግድ ቀጠናዎች አሉ።
ዞንግሻን ለናይጄሪያ ሚዲያ በሰጠው መግለጫ “የኦጉን ነጻ የንግድ ቀጠና እንደሚባለው አጥር ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኑት ትልቅ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት እንደሆነ ሰፍሯል” ሲል አክሏል።
የናይጄሪያ ባለስልጣናት የፈረንሳይ ፍርድ ቤት የወሰነውን “የማይረባ ብያኔ” እንዲቀለብስ እና አውሮፕላኖቻቸው እንዲመለሱ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
“የናይጄሪያ መንግሥት ብሄራዊ ሃብቶቻችንን ባለሃብት ከሚመስሉ አጭበርባሪዎች እና ቀማኞች ለመጠበቅ ምንጊዜም ይሰራል” ብሏል በመግለጫው












