የአዋቂዎች የእርምጃ ፍጥነት በሕይወት የሚቆዩበትን እድሜ እንደሚተነብይ ያውቃሉ? እንዴት?

በመንገድ ላይ የሚረማመዱ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

አረማመድዎ እንዴት ነው? ፈጠን ያለ ወይስ ዝግ ያለ? የእርምጃዎ ፍጥነት በድንገት ቀንሶብዎታል ወይስ የተለመደው ነው?

የእርምጃ ፍጥነት ከእድሜ ጋር የሚያያዝ ቢሆንም ገና በለጋ እድሜያቸው ቀስ እያሉ የሚራመዱ እንዲሁም በአመሻሽ እድሜያቸው ደግሞ አብራችኋቸው ለመራመድ የማትደርሱባቸው ሰዎች አልገጠሟችሁም?

ይህ ከአዕምሯችን ብቃት ጋር ይያያዛል ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ?

ጥናቶች የእርምጃችን የፍጥነት መጠን የአንጎላችንን የእርጅና ደረጃ እንደሚያመለክት አሳይተዋል። ቀስ ብለው የሚራመዱ ሰዎች ትንሽ አንጎል ያላቸው ሲሆን በወሳኝ አወቃቀሩም የተለየ ነው።

እርምጃ እና አንጎልን ምን አገናኛቸው? ትሉ ይሆናል። ጉዳዩ ተራ ነገር ሊመስልም ይችላል። ሆኖም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመድረስ የምንራመድበት ፍጥነት በሰውነታችን እና በአንጎላችን ውስጥ ምን እየተካሄደ እንዳለ እንደሚያመለክቱ ጥናቶች አረጋግጠዋል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወደ ሱቅ፣ ወደ መናፈሻ አሊያም ወደ አውቶብስ ፌርማታ ለመሄድ የምንራመድበት ፍጥነት ለሕመም የመዳረጋችንን፣ ለልብ ሕመም የመጋለጥ ዕድላችንን እና በሕይወት የምንቆይበትን እድሜ ለመተንበይ ያስችላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የአንጎልን እድሜ ለማወቅ ይጠቅማሉ።

የእርምጃ ፍጥነት የአንድ ሰው የተግባር አቅም መለኪያ ሲሆን ምን ያህል ደካማ እንደሆንን ይጠቁማል። በተጨማሪም ስትሮክ ካጋጠመን በኋላ ለማገገም የምንሰጠውን ምላሽም ለመተንበይ ያስችላል።

በእርግጥ ሰዎች እንደየ እድሜያቸው ደረጃ በዝግታ መራመዳቸው የሚጠበቅ ነው። ሆኖም የእርምጃቸው ፍጥነት በከፍተኛ ሁኔታ ከቀነሰ በሰውነታቸው ውስጥ አሳሳቢ የሆነ ነገር እየተከሰተ እንደሆነ ሊያመለክት ይችላል።

በሃርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት ክርስቲያና ዲሊ ኮንውራይት እንደሚሉት " የአንድ ሰው የተለመደ የእርምጃ ፍጥነት ከቀነሰ ብዙ ጊዜ አሳሳቢ ከሆነ የጤና መናጋት ጋር ይያያዛል"

እንቅስቃሴ በካንሰር ሕክምና ላይ በሚኖረው ውጤት ላይ ጥናት ያካሄዱት ዲሊ ኮንውራይት ከተለመደው በተለየ የእርምጃ ፍጥነት መቀነስ ሥር የሰደደ በሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል ብለዋል።

"ይህ ማለት የጡንቻዎቻቸው ጥንካሬ እንዲሁም ሌላ የጤና እክልን የሚያስከትሉ የመገጣጠሚያ አጥንቶቻቸው የመንቀሳቀስ አቅም ቀንሷል ማለት ነው" ሲሉ ዲሊ ኮንውራይት አስረድተዋል።

የእርምጃ ፍጥነታችንን እንዴት ማወቅ እንችላለን?

የእርምጃ ፍጥነታችንን ለማወቅ ሰዓት እና የምንራመደውን ርቀት የምንለካበት ዘዴ ብቻ ነው የሚያስፈልገን። እርምጃችን በምንራመድበት አካባቢ የሚወሰን በመሆኑ በሁለት መልኩ ልንለካው እንችላለን- ከቤት ውጭ እና በቤት ውስጥ።

ከቤት ውጭ ከሆንና የምንራመድበት በቂ ቦታ ካለ መጀመሪያ ላይ 10 ሜትር ርቀት በመራመድ ፍጥነታችንን መለካት እንችላለን - መጀመሪያ ላይ 5 ሜትር መራመድ ከዚያም 10 ሜትር መራመድ።

ወደ የተለመደው ፍጥነታችን ለመመለስም 5 ሜትር በመራመድ መጀመር ይመከራል። ከዚያም በተለመደው ፍጥነታችን 10 ሜትር መራመድ። የእርምጃ ፍጥነታችንን ለመለካትም የተራመድነውን 10 ሜትር ለወሰደብን ጊዜ በማካፈል ማወቅ እንችላለን።

በእግረኛ ማቋረጫ ላይ የምትራመድ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቤት ውስጥ ከሆን እና ለመራመድ ያለን ቦታ ውስን ከሆነ ደግሞ አራት ሜትር በፍጥነት በመራመድ መሞከር እንችላለን። ይህንን ለማድረግ በአንድ ሜትር ጀምረን ከዚያም አራት ሜትር ርቀት መራመድ። የመጀመሪያው ሜትር እርምጃ የሚጠቅመው በተለመደው የእርምጃ ፍጥነታችን ላይ ለመሆን ነው።ይህንን ካደረግን በኋላ አራት ሜትሩን ለመራመድ ምን ያህል ጊዜ እንደወሰደብን ማስላት እንችላለን።ይህም ቀደም ሲል እንደተገለጸው አራት ሜትሩን ለወሰደብን ሰከንዶች ማካፈል ነው።

በአማራጭነትም ፍጥነታችንን ለመለካት የሚውሉ እንደ ማፕማይዎክ፣ ስትራቫ እና ጉግል ፊት ያሉ በርካታ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ምን ያህል እንደምንራመድ ማወቅ እንችላለን።

አማካይ የእርምጃ ፍጥነት በእድሜ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የእርምጃችን ፍጥነት እንደየ የእድሜ ደረጃችን እና ፆታችን ይለያያል።ለመሆኑ አማካይ የእርምጃ ፍጥነት እንደ የእድሜ ደረጃችን ምን ያህል ነው?

  • ከ40 እስከ 49 ዓመት እድሜ ያላት ሴት የእርምጃ ፍጥነት በአማካይ በሰከንድ 1.39 ሜትር ሲሆን በተመሳሳይ የእድሜ ክልል ያሉ ወንዶች ደግሞ በሰከንድ 1.43 ሜትር ነው።
  • ከ50 እስከ 59 እድሜ ያላት ሴት በሰከንድ 1.31 ሜትር ሲሆን ወንድ ደግሞ በሰከንድ 1.43 ሜትር ነው።
  • ከ60 እስከ 69 የእድሜ ክልል የምትገኝ ሴት 1.24 ሜትር በሰከንድ የምትራመድ ሲሆን ወንድ ደግሞ 1.43 ሜትር በሰከንድ ይራመዳል።
  • ከ70 እስከ 70 ዓመት ያለች ሴት 1.13 ሜትር በሰከንድ ስትራመድ ወንድ ደግሞ 1.26 ሜትር በሰከንድ ይራመዳል።
  • ከ80 እስከ 89 የእድሜ ክልል ያለች ሴት 0.94 ሜትር በሰከንድ ወንድ ደግሞ 0.97 ሜትር በሰከንድ የሚለካ አማካይ የእርምጃ ፍጥነት ይኖራቸዋል።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የአዋቂዎች የእርምጃ ፍጥነት በሕይወት የሚቆዩበትን የእድሜ ጣሪያቸውን ለማወቅ ወሳኝ አመላካቾች ናቸው።

የፒትስበርግ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ከ34 ሺህ በላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉባቸውን ዘጠኝ ጥናቶች አንድ ላይ በማሰባሰብ ጥናት አካሂደዋል።ተመራማሪዎቹ በዚህ ጥናታቸው የእርምጃ ፍጥነት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ በሕይወት ከመቆያ እድሜ ጋር እጅጉን እንደሚገናኝ አመልክተዋል።

ለምሳሌ 75 ዓመታቸው ላይ አነስተኛ የእርምጃ ፍጥነት ያላቸው ወንዶች ለተጨማሪ አስር ዓመት በሕይወት የመቆየታቸው እድል 19 በመቶ ሲሆን ከፍተኛ የእርምጃ ፍጥነት ያላቸው ደግሞ አስር ዓመት የመቆየት እድላቸው 87 በመቶ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2009 በፈረንሳይ የተካሄደ ጥናትም፣ በጥናቱ ከተሳተፉትና እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ በሆኑ ጤናማ ሰዎች መካከል በዝግታ የሚራመዱት በፍጥነት ከሚራመዱት ጋር ሲነጻጸር ከልብ እና ከደም ቧንቧዎች ጋር በተያያዙ በሽታዎች የመሞት እድላቸው ሦስት እጥፍ መሆኑን አሳይቷል።

" መራመድ ቀላል ነገር ይመስላል። ብዙዎቻችን ስለመራመድ አናስብም፤እንደዘበት ነው የምናደርገው" የሚሉት በሰሜን ካሮላይና ደክ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና እና ኒውሮሳይንስ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ሊን ራስሙስን፣እርምጃችን ከጤናችን እና ከእድሜ ጣሪያችን ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ያስረዳሉ ።

"በእግር መራመድ በርካታ የተለያዩ የአካል ሥርዓታችን በጥምረት ከመስራታቸው ጋር የሚገናኝ ነው። አጥንታችን እና ጡንቻዎቻችን ተሸክመውን እንድንቀሳቀስ ያደርጋሉ። ዓይኖቻችን ወደ የት እንደምንሄድ ያሳዩናል።ልባችን እና ሳንባችን ደግሞ ደምና ኦክስጅን ያዘዋውራሉ። አንጎላችን እና ነርቮቻችን ደግሞ ይህንን ያስተባብራሉ።"

አመሻሽ ላይ በድልድይ ላይ የሚራመድ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዝግታ የሚራመዱ ሰዎች አካል በፍጥነት ያረጃል

እንደ ራስሙስን ከሆነ እድሜያችን እየጨመረ ሲሄድ የእነዚህ አካል ክፍሎቻችን ሥርዓት ተግባር እየቀነሰ ይሄዳል።በዝግታ መራመድም የእነዚህን ተግባራት መዳከም የሚያሳዩ ሲሆን እያረጀን ለመሆኑም ምልክቶች ናቸው።

ይህ እድሜያቸው በገፋ ሰዎች ላይ ብቻ የሚታይ አይደለም። በአውሮፓውያኑ በ2019 ራስሙስን እና ባልደረቦቻቸው በሰሩት ጥናት 45 ዓመት ከሆናቸው አዋቂዎች መካከልም የእርምጃ ፍጥነታቸው አንጎላቸው እና አካላቸው መቼ እንደሚያረጅ ለመተንበይ እንዳስቻለ አረጋግጠዋል።

" በጣም ያስገረመኝ ነገር፣ ሰዎች በ45 ዓመታቸው የሚራመዱበት ፍጥነት ከልጅነታቸው ጀምሮ ካላቸው የእውቀት [ኮግኒቲቭ] ችሎታ ጋር ያለውን ግንኙነት ማግኘቴ ነው" ብለዋል ሊን ራስሙስን።

ራስሙስን እና በደክ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተመራማሪዎች 'ለዱንዲን መልቲዲሲፕሊነሪ ኸልዝ ኤንድ ዲቨሎፕመንት ስተዲ' ለተሰኘው ጥናታቸው እድሜያቸው 45 ዓመት የሆነ 904 ሰዎችን እንዲሳተፉ አድርገው ነበር። እነዚህ ግለሰቦች በአዕምሯቸውና በአጠቃላይ የጤና ሁኔታቸው ላይ እስከ ሕይወት ፍፃሜያቸው ድረስ መደበኛ ክትትል ተደርጎላቸዋል።

በግኝታቸውም በተመሳሳይ እድሜ ላይ ያሉ ሰዎች የተለያየ የእርምጃ ፍጥነት እንዳላቸው መመልከታቸውን ራስሙስን ተናግረዋል።

" ሁሉም 45 ዓመት የሆናቸው ሰዎች አማካይ የሆነ የእርምጃ ፍጥነት እንዳላቸው ልትጠብቁ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን አንዳንዶቹ እንደ 20 ዓመት ወጣት በፍጥነት የሚራመዱ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ከእነርሱ በእድሜ እንደሚበልጡ ሰዎች በዝግታ ይራመዳሉ" ብለዋል።

በዚህ ጥናት ከተሳተፉት የ45 ዓመት ጎልማሶች መካከል አነስተኛ የእርምጃ ፍጥነት ያላቸው በፍጥነት ከሚራመዱት ጋር ሲነጻጸሩ የተፋጠነ የእርጅና ምልክት እንዳሳዩ ጥናቱ አመልክቷል። ሳንባቸው፣ ጥርሶቻቸውና የበሽታ የመከላከል ሥርዓታቸውም ድክመት አሳይተዋል።

ከዚህም ባሻገር እንደ የደም ግፊት መጨመር ፣ ከፍተኛ ኮሌስትሮል እና ዝቅተኛ የልብና የመተንፈሻ አካል ብቃት ካሉ ከእርጅና መፋጠን ጋር የተያያዙ ምልክቶች ነበሯቸው። በዝግታ የሚራመዱ ሰዎች እንደ ደካማ የእጅ ጥንካሬ፤ ከወንበር የመነሳት ችግር ያሉ ሌሎች የአካላዊ ጤንነት እክል ምልክቶች እንዳሏቸውም ጥናቱ ደርሶበታል።

ራስሙስን እና ባልደረቦቻው ዘገምተኛ ተራማጆች ከፍተኛ የሆነ የአዕምሮ ብቃት [ኮግኒቲቭ] እርጅና ምልክቶች እንዳሳዩም በጥናታቸው አግኝተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአዕምሮ ብቃት (አይኪው) ልኬት በማስታወስ ችሎታቸው፣ ሃሳቦችን ከማሰብ ፍጥነት ፣ ምክንያታዊነት እና ሌሎች አዕምሯዊ ብቃቶች ላይ የላሸቀ ውጤት አስመዝግበዋል።

በኤምአርአይ በተደረገላቸው ምርመራ በጥናቱ ተሳታፊዎች አንጎል ውስጥ የታዩት ለውጦች የአዕምሮ ብቃታቸው እየቀነሰ መምጣቱን አመልክተዋል።

በዝግታ የሚራመዱ ሰዎች አነስተኛ የአንጎል መጠን፣ እሳቤን እና ከፍተኛ የመረጃ ማቀነባበርን የሚቆጣጠር ቀጭን የአንጎል ሽፋን ( ኒዎኮርቴክስ) ነበራቸው።

በዝግታ የሚራመዱት የጥናቱ ተሳታፊዎች የፊት ገጽታም ከሌሎቹ ተሳታፊዎች በላቀ ሁኔታ በፍጥነት እያረጀ እንደሆነ አሳይተዋል።

ከዚህም ባሻገር ተሳታፊዎቹ የሦስት ዓመት ሕፃን ሳሉ በተወሰዱ የእውቀት [ኮግኒቲቭ]፣ የቋንቋ እና አካላዊ ችሎታ ላይ በመመስረት 45 ዓመታቸው ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን የእርምጃ ፍጥነት መተንበይ በመቻላቸው እነዚህ ልዩነቶች ከልጅነት ጀምሮ እንደነበሩ የሚያሳዩ ምልክቶች ታይተዋል።

" በጣም ያስገረመኝ ነገር ሰዎች በ45 ዓመታቸው የሚራመዱበት ፍጥነት በልጅነታቸው ካላቸው የአዕምሮ [ኮግኒቲቭ] ብቃት ጋር ግንኙነት መኖሩ ነው" ያሉት ራስሙስን፣ ይህም የእርምጃ ፍጥነት የእርጅና ምልክት ብቻ ሳይሆን የእድሜ ልክ የአዕምሮ ጤናን የመመልከቻ መስኮት እንደሆነ ገልጸዋል።

ሆኖም በዝግታ የሚራመዱ ሰዎች ይህንን ጽሑፍ ሲያነቡ መጨነቅ የለባቸውም ይላሉ። የእርምጃ ፍጥነትን ለማሻሻል የሚረዱ በርካታ ዘዴዎች አሉ።

ዲሊ ኮንውራይት የካንሰር ህሙማንን ለመርዳት ባደረጉት ጥናት የካንሰር ታማሚዎች ከኬሞቴራፒ ሕክምና አገግመው ጥንካሬያቸውን እንዲያገኙ የሚያስችል የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ያዘጋጃሉ።

በዚህ የሚሳተፉት አቅማቸውን ለማጠናከር በየሦስት ወይም በየአራት ሳምንቱ የእርምጃ እንቅስቃሴያቸውን ፍጥነት እና ቆይታ እንዲጨምሩ ይመከራሉ።ሌሎች ሰዎች ሊያደርጓቸው የሚችሏቸው አማራጮችም አሉ።

" በአካል ንቁ ሆኖ መቆየት ወሳኝ በመሆኑ በመደበኛነት የእግር ጉዞ ማድረግ አስፈላጊ ነው" የሚሉት ዲሊ ኮንውራይት በእግር ለመራመድ የሚያስችሉንን ማንኛውም እድሎች መጠቀም እንደሚገባ ይመክራሉ።

መኪናችሁን ከመዳረሻችሁ ራቅ ያለ ቦታ ማቆም፣ ከጓደኛ ጋር በመገናኘት በቡድን የእግር ጉዞ ማድረግ ወይም የቤት እንስሳትን ለማናፈስ ማውጣት የእግር ጉዞ ለማድረግ እንደሚያበረታቱ ይናገራሉ።

" በተለይ ብዙ ጊዜ ተቀምጠው የሚሰሩ ሰዎች ተነስተው በመራመድ እረፍት ማድረግ ያስፈልጋል። የምንወስደው እረፍት ወደ መታጠቢያ ቤት ለመሄድ ወይም በሕንፃው ዙሪያ ለአምስት ደቂቃ መራመድ ሊሆን ይችላል። ይህንን በማድረግም የምንቀመጥበትን ሰዓት መቀነስ ወሳኝ ነው" ብለዋል።