በታይላንድ ከመነኮሳት ጋር ወሲብ ፈጽማ በቪዲዮዎች በማስፈራራት 11.9 ሚሊዮን ዶላር ተቀብላለች የተባለችው ግለሰብ ተያዘች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በታይላንድ ከቡድሂስት መነኮሳት ጋር ወሲብ ከፈጸመች በኋላ ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን ገንዘብ ለማግኘት በማስፈራሪያነት ተጠቅማ ከፍተኛ ሃብት አከማችታለች የተባለችው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለች።
ፖሊስ "ሚስ ጎልፍ" በሚል ቅጽል ስም የጠራት ይህች ግለሰብ ቢያንሰ ከዘጠኝ መነኮሳት ጋር ወሲብ መፈጸሟን ማክሰኞ ዕለት ፖሊስ በጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።
ግለሰቧ በባለፉት ሶስት ዓመታት መነኮሳቱን አስፈራርታ 11.9 ሚሊዮን ዶላር እንዳገኘች ፖሊስ ያምናል።
ቤቷን የፈተሹ መርማሪዎች መነኮሳቱን ለማስፈራራት የተጠቀመችባቸውን ከ80 ሺህ በላይ ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን ማግኘታቸውን የፖሊስ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
በታይላንድ በቅድስና እና ክብር ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው የቡድሂስት ተቋም በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ቅሌቶች መነከሩ እየተነገረ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ አደገኛ ዕጽ ዝውውር እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃቶች ናቸው። በቅርቡ የዚህች ግለሰብ ተግባር የእምነቱን ተቋም ያናጋ ሆኗል።
ይህ ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ የፖሊስን ትኩረት ያገኘው ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በሴትዮዋ ገንዘብ የተወሰደባቸው አበምኔት በድንገተኛ ሁኔታ ምንኩስናቸውን መተዋቸውን ተከትሎ ነው።
'ሚስ ጎልፍ' ከአበምኔቱ ጋር ባለፈው ዓመት "ግንኙነት" እንደነበራት ፖሊስ አስታውቋል።
በኋላም ልጅ ወልጄልዎታለሁ በማለት የልጅ ድጋፍ እንዲያደርጉ 7 ሚሊዮን ባህት (የታይላንድ ገንዘብ መገበያያ) መጠየቋ ተገልጿል። ፖሊስ ከሳቸው ብቻ ሳይሆን ሌሎች መነኮሳትም ገንዘብ እንዳዛወሩላት መረዳት ቻለ።
ግለሰቧ ገንዘቡን ከሞላ ጎደል አውጥታ የተወሰነው ለኦንላይን ቁማር መዋሉን ማረጋገጡን ፖሊስ አክሏል።
መርማሪዎች በቅርቡ በቤቷ ውስጥ ባደረጉት ፍተሻ መነኮሳቱን ገንዘብ ለመቀበል ያስፈራራችበትን ስልኳ ላይ ከ80 ሺህ በላይ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች መገኘቱን ፖሊስ ገልጿል።
ግለሰቧ ገንዘብ በማስፈራራት በመቀበል፣ ህገወወጥ የገንዘብ ዝውውር እና የተሰረቁ እቃዎችን በመቀበል ክሶች ይመሰረትባታል ተብሏል።
ፖሊስ በተጨማሪም "አግባብ ያልሆነ ባህርይ በሚያሳዩ መነኮሳት" ላይ ሪፖርት እንዲደረግ የስልክ መስመር ከፍቷል።
ይህ ቅሌት የታይላንድን ቡድሂዝምን በበላይነት የሚያየው የሳንጋ ጠቅላይ ምክር ቤት የገዳማቱን መመሪያዎች ለመገምገም ልዩ ኮሚቴ አዋቅራለሁ ብሏል።
መንግሥት በበኩሉ የገዳሙን ህግጋት በሚጥሱ መነኮሳት ላይ የገንዘብ እና የእስር ቅጣትን ጨምሮ ከባድ ቅጣት እንዲጣልባቸው እየገፋ ነው።
በዚህ ሳምንት የታይላንድ ንጉስ ቫጂራሎንግኮርን በሰኔ ወር ለ81 መነኮሳት ከፍተኛ ማዕረግ እንዲሰጥ ያስተላለፉትን ንጉሳዊ ትዕዛዝ ሽረዋል።
ለዚህም ምክንያታቸው በቅርቡ የተከሰተው የስነ ምግባር ጉድለት መሆኑን ጠቅሰው ይህም ሁኔታ "የቡድሂስት እምነት ተከታዮችን አዕምሯቸውን የረበሸ" ነው ብለዋል።
በታይላንድ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ የቡድሂዝም እምነት ተከታይ ወይም ራሳቸውን ቡድሂስት ብለው ይጠራሉ።
የቡድሂስት መነኮሳትም እንደ ቅዱሳትና ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጣቸው ናቸው።
በርካታ የታይላንድ ወንዶች የሚቀጥለው ህይወታቸውን የተሻለ ለማድረግ መነኮሳትን መሆንን ይመርጣሉ።















