በዝንጀሮ ፈንጣጣ ምክንያት የውጭ ዜጎችን እንዳትነኩ ሲሉ የቻይና ባለሥልጣን አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዘ የመጀመሪያውን ሰው ማግኘቷን ተከትሎ አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ የጤና ባለሥልጣን ቻይናውያን ከውጭ ዜጎች ጋር እንዳይነካኩ አስጠንቅቀዋል።
በቻይና የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ዋና ኤፒዲሚዮሎጂስት የሆኑት ዉ ዙንዩ፣ ዌቦ በተሰኘው የቻይና የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ላይ ዜጎች “ከውጭ አገር ሰዎች ጋር ቆዳ-ለቆዳ ንክኪ” እንዳይኖራቸው መክረዋል።
ይህ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተላለፈው ምልዕክት ውዝግብ ቀስቅሷል። አንዳንዶች ዘረኛ ሃሳብ ብለው እስከመሰየም ደርሰዋል።
በልጥፉ ላይ ያሉ አስተያየት መስጫ ስፍራዎች በኋላ ላይ ተዘግተዋል።
“እንደ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤያችን፤ የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለመከላከል ሲባል ከውጭ አገር ሰዎች ጋር በቀጥታ ቆዳ ለቆዳ ንክኪ እንዳይኖረን ይመከራል” ሲሉ ዉ ቅዳሜ ዕለት በዌቦ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተጨማሪም ባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ከውጭ አገራት ከተመለሱ ተጓዦች እና ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር እንዳይነካኩ ጥሪ አቅርበዋል።
አስተያየቱ የተለጠፈው ደቡብ ምዕራብ በምትገኘው ቾንግኪንግ ከተማ ከውጭ በመጣ ግለሰብ ላይ የመጀመሪያው የዝንጀሮ ፈንጣጣ መገኘቱ ከተዘገበ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ግለሰቡ የየት አገር ዜጋ እንደሆነ ግልጽ አልተደረገም።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሰፊው የተሰራጨው መልዕክት በዌቦ ላይ ትችት አዘል አስተያየቶችን አስከትሏል።
አንድ አስተያየት ሰጪ “ይህ ተገቢ አይደለም። በወረርሽኙ [ኮሮና] ጀማሮ አንዳንዶች የውጭ ዜጎች ቻይናውያን ቫይረስ አይደሉም ሲሉ ተከላክለውናል” ብሏል።
“ይህ እንዴት ዘረኛ ነው? እንደ እኔ በቻይና ለአስር ዓመታት ያህል የኖሩትስ? ለ3 እና ለ4 ዓመታት ድንበር በመዘጋቱ ቤተሰቦቻችንን አላየንም” ሲል በዌቦ ላይ የውጭ ዜጋ የሚመስል ግለሰብ ጽፏል።
ቻይና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ፈጣን የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣል፣ ድንበር በመዘጋት፣ አስገዳጅ ምርመራ እና የጉዞ ገደቦችን ያካተተ በጣም ጠንካራ የኮቪድ እርምጃዎችን ወስዳለች።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ፤ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች፣ ከእንስሳት ወይም የተበከሉ ቁሶችን በመንካት የሚተላለፍ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ እንደ ትኩሳት፣ ራስ ምታት እና ሽፍታ ያሉ ምልክቶችን ያስከትላል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወደ 90 በሚጠጉ አገራት ውስጥ መከሰቱ ሪፖርት ተደርጓል። የዓለም ጤና ድርጅት ደግሞ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት ነው ብሎ አውጇል።
በበሽታው ከ60,000 በላይ ሰዎች መያዛቸው ሲገለጽ፣ አንዳንድ አገራትም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰዎች መሞታቸውን አስታውቀዋል።












