ቲክቶክን ማን ሊገዛው ይችላል? ኢላን መስክ፣ ኦራክል ወይስ ሚስተር ቢስት?

ጂሚ ዶናልድሰን አሊያም ሚስተር ቢስት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የቲክቶክ ተከታዮቹ ማኅበራዊ ሚድያውን ሊገዛ እንዳሰበ ሲናገር በደስታ ነው።
"አዲሱ ሥራ አስኪያጃችሁ ልሆን እችላለሁ! በጣም ደስ ብሎኛል" በማለት ሚስተር ቢስት በግል ጄቱ እየበረረ የለቀቀው ቪድዮ ያሳያል። ቀጥሎ ደግሞ ለአምስት ተከታዮቹ በነሲብ 10 ሺህ ዶላር ለመስጠት ቃል ይገባል።
የሚስተር ቢስት ቪድዮ ከተለጠፈበት ሰኞ ጀምሮ ከ70 ሚሊዮን በላይ ጊዜ ታይቷል። በዩቲዩብ ቪድዮች ለበርካቶች ገንዘብ፣ ቤትና ንብረት በመስጠት የሚታወቀው ሚስተር ቢስት ቲክቶክን ለመግዛት ስለማሰቡ ብዙ ባይልም "ይህ እወቁ። አስገራሚ ነው የሚሆነው" ብሏል።
ሚስተር ቢስት ቲክቶክን ለመግዛት ፍላጎት ካሳዩ በርካታ ሰዎች መካከል አንዱ ነው።
በወጣቶች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነው ቲክቶክ አጋር ባለቤት ለመሆን አቅም ያላቸው ሰዎች እየተሰለፉ ነው። ቲክቶክ በአሜሪካና ቻይና መካከል ያለው የፖለቲካ ውጥንቅጥ አካል ሆኗል።
ባለፈው ዓመት የቀድሞው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የቲክቶክ ባለቤት የሆነው የቻይናው ባይትዳንስ እስከ አውሮፓውያኑ ጥር 19 ድረስ በአሜሪካ የሚገኘውን ክንፍ እንዲሸጥ ካልሆነም እንደሚዘጋ ወስነው ነበር።
ሕጉ እንደሚለው ቲክቶክ ከቻይና መንግሥት ጋር ግንኙነት ስላለው መተግበሪያው ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ነው።
አዲሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለቲክቶክ የጥቂት ወራት እፎይታ ከሰጡት በኋላ ከአሜሪካ ኩባንያ ጋር አብሮ እንዲሠራ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
"ዩናይትድ ስቴትስ 50 በመቶ ድርሻ እንዲኖራት እፈልጋለሁ" ሲሉ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበዊ ሚድያቸው ፅፈዋል። "ይህን በማድረጋችን ቲክቶክን ከመታገድ እንጠብቀዋለን፤ ሥራውንም አያቋርጥም" ብለዋል።
ትራምፕ ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ በፈረሙት ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዝ ቲክቶክ ለ75 ቀናት ሥራውን እንዲቀጥል ወስነዋል።
በያዝነው የአውሮፓውያኑ ወር ጥር መባቻ ብሉምበርግ በዘገባው ቻይና ቲክቶክ ለኢላን መስክ ልትሸጥ አስባለች ብሏል። የዓለማችን ሀብታሙ ሰው ኢላን መስክ የኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ባለቤት እና የትራምፕ የቅርብ ሰው ነው።
መስክ በኤክስ ገፁ በፃፈው መልዕክት ቲክቶክ እንዲታገድ መወሰኑን ሲቃወም እንደቆየ ተናግሮ ነገር ግን "ቲክቶክ በአሜሪካ እየሠራ ኤክስ ግን ቻይና ውስጥ እንዳይሠራ መታገዱ ሚዛናዊ አይደለም። አንድ ነገር መቀየር አለበት" ብሏል።
ትራምፕ ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ በነበረ አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ መስክ ቲክቶክን እንዲገዛው ይፈልጉ እንደሁ ተጠይቀው ነበር።
"እሱ ሊገዛው ከፈለገ ችግር የለውም" ሲሉ ፕሬዝደንቱ ምላሽ ሰጥተዋል።
አክለው "ላሪ እንዲገዛው እፈልጋለሁ" ብለዋል። ላሪ ኤሊሰን ኦራክል የተባለው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሊቀ-መንበር እንዲሁም የረዥም ጊዜ የትራምፕ ደጋፊ ናቸው።
ኦራክል ለቲክቶክ 'ሰርቨር' ከሚያቀርቡ ድርጅቶች መካከል አንዱ ሲሆን የቲክቶክ ቪድዮዎች የሚከማቹባቸውን የዴታ ማዕከሎች ይቆጣጠራል።
ባለፈው ዓመት ኦራክል ቲክቶክ መታገዱ በከፍተኛ ሊጎዳው እንደሚችል አሳውቆ ነበር። በ2020 ትራምፕ ቲክቶክን ለማገድ በተነሱበት ወቅት ኦራክል ሊገዛው እንቸሚችል በሰፊው ሲነገር ነበር።
ቢሊየነሩ ኢንቨስተር ፍራንክ ማክኮርት ቲክቶክን ለመግዛት ፍላጎታቸውን ከገለፁ ባለሀብቶች መካከል አንዱ ነው።
ማኅበራዊ ሚድያዎች የተጠቃሚዎችን መረጃ መሰብሰባቸውን የሚቃወመው ፍራክን ከሰሞኑ ለሲኤንቢሲ በሰጠው ቃለ-ምልልስ ነው ቲክቶክን መግዛት እንደሚሻ የተናገረው።
ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ የቲክቶክን ድርሻ ማን ሊገዛው ይችላል በሚለው ጉዳይ ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።
የጆርጅታውን ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት አኑፓም ቻንድለር "የጨረታው አሸናፊ የሚሆነው ለፕሬዝደንት ትራምፕ አዘኔታ ያለው ነው" ይላሉ።
ትራምፕ 50/50 ይሁን ሲሉ ያመጡት ሐሳብ ኮንግረሱ ካፀደቀው ሐሳብ ጋር የማይጣጣም ስለሆነ ኮንግረሱ ሕጉን እንዲከልሰው ሊጠይቁ ይችላሉ።












