የፒዛ ቤት ባለቤት ለአንድ ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ በነጻ ፒዛ ሊጋግር ነው

አንድ የፒዛ ቤት ባለቤት መልካምነትን ለመግለጽ በስኮትላንድ መዲና ለኤደንብራህ ነዋሪዎች በሙሉ ነጻ ቪዛ ሊሰጥ ነው።
ፒዩር ፒዛ የተባለው ፒዛ ቤት ባለቤት ማርክ ዊልኪንሰን በዋጋ ንረት እየተቸገሩ ያሉ ሰዎችን ለመርዳት መልካም ነገር ለመፈጸም ብዙ ሲያልም መቆየቱን ተናግሯል።
የ55 ዓመቱ ማርክ ለከተማው ነዋሪ በሙሉ ነጻ ፒዛ ለመስጠት ማቀዱ ሁሉንም ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ደስተኛ ነኝ ብሏል።
“ደንበኞቼ ይጠቀማሉ፣ አቅራቢዎች ይጠቀማሉ፣ ፒዛ ጋጋሪ ሼፎች ረዥም ሰዓት ሠርተው የተሻለ ክፍያ ስለሚያገኙም ይጠቀማሉ” ብሏል።
“የኑሮ ውድነት በርካታ ሰዎችን እየፈተነ መሆኑን በተደጋጋሚ እየሰማሁ ነው። ፒዛ መጋገሪያ ምድጃዎቼ ቀኑን ሙሉ ተለኩሰው መዋላቸው ካልቀረ ቢጋገርባቸውና ለተቸገሩ ቢደርሱ ጉዳት አይሆንም” ብሏል።
“ለሌሎች መኖር የሚለው ሐሳብ የሚማርከኝ ነገር ነው፤ አሁን ደግሞ ልኖረው እሻለሁ” ብሏል ዊልኪንሰን።
ይህ አንድን ከተማ በፒዛ ማንበሽበሽ ዊልኪንሰንን እስከ 12ሺህ ፓውንድ ሊያስወጣው ይችላል።
የዊልኪንሰን ፒዛ ቤት የተከፈተው እአአ በመጋቢት 2020 የኮቪድ እንቅስቃሴ ገደብ ሊጣል በነበረበት ጊዜ ነበር።
የፒዛ ቤቱ ምድጃዎች በየ6 ደቂቃው 18 ፒዛዎችን የመጋገር አቅም አላቸው።
ፒዛው የሚታደላቸው በጥር ወር ወደ ፒዛ ቤቱ ብቅ የሚሉት ሁሉ ናቸው። ነገር ግን ከምሽቱ 11፡30 እስከ 2፡30 አገልግሎት አይሰጥም።
ይህ ለጋስ የፒዛ ቤት ባለቤት በኔ ደጅ ያለፈና አንድ ፒዛ ያነሳ ሁሉ ስለ ለጋስነትና ለሌሎች ስለመኖር ማሰቡ አይቀርም ብሏል።












