የብረት ሰንሰለት አጥልቆ ወደ ኤምአርአይ ክፍል የገባው አሜሪካዊ በመሳሪያው ወደ ውስጥ ተስቦ ህይወቱ አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ክብደት ያለው የብረት ሰንሰለት አጥልቆ ወደ ኤምአርአይ ክፍል የገባው አሜሪካዊ ግለሰብ በአገልግሎት ላይ በነበረው መሳሪያ ወደ ውስጥ ተስቦ ህይወቱ ማለፉ ተገለጸ።
በኒውዮርክ ሎንግ አይላንድ በሚገኘው የናሳው ኦፕን ኤምአርአይ ማዕከል ውስጥ ያለፍቃድ ግለሰቡ ሲገባ የኤምአርአይ መሳሪያው እንቅስቃሴ ላይ ላይ እንደነበር ተገልጿል።
የ61 ዓመቱ ግለሰብ ማንነት ባይገለጽም፤ በተቋሙ የነበረች አንዲት ታካሚ ህይወቱ ያለፈው ግለሰብ ባለቤቷ መሆኑን ገልጻለች።
ግለሰቧ ረቡዕ ዕለት የኤምአርአይ ምርመራ ን ካደረገች በኋላ ባለቤቷን ወደ ክፍሉ እንደጠራችው ገልጻለች።
ባለስልጣናቱ እንዳሉት ይህ የህክምና አደጋ ካጋጠመ በኋላ ወደ ሆስፒታል ለህክምና ቢወሰድም በማግስቱ ሐሙስ ህይወቱ ማለፉን ገልጸዋል።
ኤምአርአይ መሳሪያዎች የሰውነት የውስጥ አካላትን ዘርዘር ያለ ምስል ለማግኘት ጠንካራ ማግኔቶችን ይጠቀማሉ።
ታካሚዎች ወደ መሳሪያው ከመጠጋታቸው በፊት ወይም ለምርመራ ከመግባታቸው በፊት ማንኛውንም ብረታማ ቁሶች ከሰውነታቸው እንዲያወልቁ እና ልብሳቸውን እንዲቀይሩ ይጠየቃሉ።
"ሟቹ በአንገቱ ላይ ትልቅ የብረት ሰንሰለት አጥልቆ የነበረ ሲሆን ይህም መሳሪያው ወደ ውስጥ እንዲስበው አድርጎታል፤ በዚህም የህክምና ችግር ተከትሏል" ሲል ሁኔታውን እየመረመረ ያለው የናሳው ግዛት ፖሊስ መምሪያ ገልጿል።
ምንም እንኳን ፖሊስ የሟቹን ስም ባይጠቅስም፣ አድሪየን ጆንስ ማክ አሊስተር የተሰኘችው ግለሰብ ለአካባቢው የቴሌቪዥን ጣቢያ ኒውስ 12 ሎንግ አይላንድ የሞተው ባሏ ኪት መሆኑን ተናግራለች።
"እጁን አውለበለበ እና መላ ሰውነቱ ተዝለፈለፈ" በማለት እያለቀሰች ገልጻለች።
ጆንስ ማክ አሊስተር ለጉልበቷ ኤምአርአይ ልትነሳ እንደሄደች እና ስትጨርስ ባለቤቷ እንዲረዳት እንደጠየቀችው ለሚዲያው ገልጻለች።
ባለቤቷ በወቅቱ ለአካላዊ እንቅስቃሴ የሚጠቀምበትን ቁልፍ ያለው 9 ኪሎግራም የሚመዝን የብረት ሰንሰለት አንገቱ ላይ አጥልቆ እንደነበር አስረድታለች።
"በዚያች ቅጽበት መሳሪያው አዞረው እና ስቦ አስገባው ከዚያም መሳሪያው መታው" ብላለች።
ባለቤቱ አክላም ከቴክኒሻኑ ጋር ሆነው ባለቤቷን ከኤምአርአይ መሳሪያው ለማውጣት ሞክረው ነበር።
"መሳሪያውን ማጥፋት ትችላለህ? ፖሊስ ጋር ደውል! እባክህ የሆነ ነገር አድርግ! ይህንን የተረገመ ነገር አጥፋው" አልኩት ብላለች።
እንደ አሜሪካ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር አስተዳደር የኤምአርአይ መሳሪያዎች በየትኛውም መጠን ያሉ ማግኔት የተገጠመላቸው እንደ ቁልፍ፣ የተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ የኦክስጅን መሳሪያዎች ይሳባሉ።
ይህም ስበት ደግሞ "በመሳሪያው ፣ በህመምተኞች ወይም በጤና ባለሙያዎች ላይ" ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ ይላል።
በአውሮፓውያኑ 2001 በኒውዮርክ ከተማ በሚገኝ አንድ የጤና ማዕከል የኤምአርአይ ምርመራ እየተደረገለት ያለ አንድ የስድስት ዓመት ህጻን ልጅ ጭንቅላቱ ተጎድቶ ህይወቱ አልፏል።
ኤምአርአይ መሳሪያው በክፍሉ ውስጥ ያለ የኦክስጅን ታንክ ስቦ በተፈጠረ አደጋ ነው ህጻኑ የሞተው።















