ሶሪያ ምጣኔ ኃብቷን ለማነቃቃት የሠራተኞቿን ደመወዝ በእጥፍ ጨመረች

የሶሪያ ፓውንድ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, በሶሪያ ጦርነቱ ሲጀምር የአንድ ዶላር ዋጋ 47 የሶሪያ ፓውንድ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ምንዛሬው 15 ሺህ ደርሷል።

የሶሪያ መንግሥት በጦርነት የተደቆሰውን የአገሪቷን ምጣኔ ኃብት ለማነቃቃት የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝ በእጥፍ ሲጨምር፣ የነዳጅ ድጎማውን አነሳ ።

ይህ የተገለጸው የሶሪያ ፓውንድ ዋጋ ከአሜሪካ ዶላር ጋር በትይዩ ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን ተከትሎ ነው።

የአገሪቷ የመገበያያ ገንዘብ መውደቅም በነዳጅ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትን ያስከተለ ሲሆን 90 በመቶ የሚሆነውን ሕዝብም ከድህነት ወለል በታች እንዲሆን አድርጎታል።

ይህ የኑሮ ውድነትም በመንግሥት ሥር በሚገኙ አካባቢዎች ተቃውሞን ቀስቅሷል።

በአውሮፓውያኑ 2011 በዲሞክራሲ አቀንቃኞች በተካሄዱ ተቃውሞዎች ፕሬዚደንት ባሽ አል አሳድ የኃይል እርምጃ ከወሰዱ በኋላ በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከዚያን ጊዜ በኋላ አገሪቷ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።

በዚህም 70 በመቶ የሚሆነውና ከ15 ሚሊየን በላይ ሕዝቧ ሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ ሲሆን 12.1 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝቧም የምግብ ዋስትና ችግር እንዳለበት ይታሰባል።

ረቡዕ ዕለት ይፋ በተደረገው ፕሬዚደንታዊ ውሳኔዎች ለመንግሥት ሠራተኞች፣ ለመንግሥት ጡረተኞች እና የታደራዊ የሰው ኃይል እና የመንግሥት ተቋራጮች በእጥፍ ደመወዝ እንዲጨመርላቸው ታዟል።

ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ሲጨመር ከታኅሳስ 2021 ወዲህ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ለሁሉም ሠራተኞች ዝቅተኛው ወርሃዊ ክፍያ 185 ሺህ 940 የሶሪያ ፓውንድ እንዲሆን ወስኗል።

ይህ ገንዘብ በባንክ ባለው የአንድ ዶላር የምዛሬ ዋጋ 8 ሺህ 542 ሲሰላ 21.76 ዶላር ሲሆን በትዩዩ የዶላር ገበያ በ15 ሺህ የሶሪያ ፓውንድ ምንዛሬ ሲሰላ ደግሞ 12.40 ዶላር ይሆናል።

በሶሪያ ጦርነቱ ሲጀምር የአንድ ዶላር የምንዛሬ ዋጋ 47 የሶሪያ ፓውንድ ነበር።

አሁን ላይ የተቀመጠው ዝቅተኛ ክፍያ፣ የዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም ግንቦት ወር ባስቀመጠው መረጃ ስሌት መሠረት አምስት የቤተሰብ አባላት ያሉት አንድ ቤተሰብ በወር ከሚያስፈልገው መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ ውስጥ አንድ ሦስተኛውን ለመግዛት ብቻ የሚበቃ ነው።

ከዚህም ባሻገር አንድ ቤተሰብ ከሚያወጣው ዝቅተኛ የቤት ውስጥ ወጪ ውስጥ ከ10 በመቶ በላይ የሚሆነውን ነው የሚሸፍነው።

እንደ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከሆነ በአገሪቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የኑሮ ውድነት በርካታ ቤተሰቦች ወጪዎቻቸውን ለመክፈል ሲታገሉ ቆይተዋል።

ዝቅተኛ ወጪያቸው በግንቦት 2022 ከነበረው በ62 በመቶ የጨመረ ሲሆን በመስከረም ወር 2021 ከነበረው ደግሞ በ159 በመቶ አሻቅቧል።

የንግድ ሚኒስቴር ምሽቱን በሰጠው ሌላ መግለጫም፣ በፔትሮሊየም [ ድፍድፍ ነዳጅ] ላይ ያለውን ድጎማ ሙሉ በሙሉ፣ በነዳጅ ዘይት ላይ የነበረውን ድጎማ ደግሞ በከፊል ማንሳቱን አስታውቋል።

በዚህም በሊትር 3 ሺህ የሶሪያ ፓውንድ ይሸጥ የነበረው የፔትሮሊየም ዋጋ ወደ 8 ሺህ ፓውንድ የሚጨመር ሲሆን፣ የአንድ ሊትር የነዳጅ ዘይት ዋጋም ከ700 ፓውንድ ወደ 2 ሺህ ከፍ እንደሚል ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሁሴን አርኖስ ባለፈው ዓመት የነዳጅ ድጎማዎችን ማንሳት ድሃ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ እና የበጀት ጉድለትን እንደሚቀንስ እንዲሁም የሶሪያን ፓውንድ እንደሚያረጋጋ ተናግረው ነበር።

ይሁን እንጂ የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች መንግሥት ድጎማዎችን አንስቶ መቆየት አይችልም ብለዋል።

ባለሙያዎቹ ጨምረውም የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪው የዋጋ ንረትን እንደሚጨመር እና የሶሪያ ፓውንድ ዋጋን የበለጠ እንዲያሽቆለቁል እንደሚያደርግ አስጠንቅቀዋል።

ባለሥልጣናት በአገሪቷ ለተከሰተው የምጣኔ ኃብት ቀውስ እና ለተራው የሶሪያ ዜጎች የኑሮ ፈተና ምክንያቱ አሜሪካ በ2019 ለአሳድ ድጋፍ ይሰጣሉ ያለቻቸውንና ማንኛውም የውጭ ዜጎች እና አካላትን ኢላማ ያደረገ ማዕቀብ መጣሏ ነው ይላሉ።

አሜሪካ ግን እርምጃው የሰብዓዊ እርዳታ ላይ ተፅዕኖ እንደማያሳድር ገልጻለች።