ሰዎች ለ‘ኤንኤፍቲ’ ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል የማይሳሱት ለምንድን ነው?

ኤንኤፍቲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምዕራባውያን ሚዲያ፣ የአርት እና የክሪፕቶክረንሲ ወዳጆች ከቅርብ ጊዜ አጀንዳዎቻቸው መካከል አንዱ ኤንኤፍቲ (NFT) ነው።

በክሪፕቶከረንሲ ብሎክቼይን ሥርዓት ላይ የተመረኮዘው ኤንኤፍቲ የበርካታ ሰዎችን ቀልብ ይዟል።

ከአንድ ዓመት በፊት ትውልደ ሕንዳዊ ወጣት 67 ሚሊዮን ዶላር አውጥቶ የማይዳሰሰውን ‘ዲጂታል አርት’ የግሉ ማድረጉ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

ከትዊተር መስራቾች አንዱ የሆነው ጃክ ዶርሲ የመጀመሪያ ትዊቱ በኤንኤፍቲ 2.9 ሚሊዮን ዶላር መሸጡም ብዙዎችን አስደንቋል።  

ኤንኤፍቲ ምንድን ነው?

NFT- Non-fungible token የሚለው ምሕጻረ ቃልን ይወክላል።

የኤንኤፍቲ ጽንሰ ሃሳብ ለመረዳት እና እንዴት እንደሚሰራ ለማወቅ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮችን ቀድመን መገንዘብ ይኖርብናል።

የመጀመሪያው የኤንኤፍቲ ኢኮሚያዊ ትርጉሜ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ የብሎክቼይን ጽንሰ ሃሳብን መረዳት ይጠይቃል።

ፈንጀብል (Fungible) የሚለውን ቃል የኦክስፎርድ ኢኮኖሚክስ መዝገበ ቃላት “የአንድ ዕቃ በሌላ ተመሳሳይ ዕቃ የመተመካት አቅም’ (the ability of a good or asset to replaceable by another identical item) ሲል ይተረጉመዋል።

ይህ በአጭሩ ‘ፈንጀብል’ መተኪያ ያለው፤ ወይም በሌላ ተመሳሳይ ነገር ሊቀየር የሚችል ነገር እንደማለት ነው።

ለምሳሌ አንድ የ10 ብር ኖት በሁለት የባለ አምስት ብር ኖቶች ሊቀየር ይችላል። 1 ባለ 10 ብር ኖት በሁለት የአምስት ብር ኖቶች ስለሚተካ ባለ 10 ብር ኖት መተኪያ አለው ማለት ነው።

non-fungible (ነን-ፈንጀብል) ማለት ደግሞ በተቃራኒው መተኪያ የሌለው፤ በሌላ የማይቀየር ነገር ማለት ነው።

ለዚህ ምሳሌ ሊሆን የሚችለው የሞናሊዛ ስዕል ነው። ሊዮናርዶ ዳቪንቺ በእጁ ስሎ ሞናሊዛ ሲል የሰየመው የጥበብ ሥራ አንድ ብቻ ነው።

'ዘ ሉቭ' የምትገኘው ሞናሊዛ አንድ ብቻ ናት። በሌላ ልትተካ አትችልም። ስለዚህ የሞናሊዛ ስዕል 'ነን-ፈንጀብል' ነው።

ስለዚህ 'ነን-ፈንጀብል' ቶክን ማለት በሌላ ሊተካ ወይም ሊቀየር የማይችል ነገር ማለት ነው።

ብሎክቼይን

የብሎክቼይን ሥርዓት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኮምፒዩተሮችን እርስ በእርሳቸው በማስተሳሰር በሥርዓቱ ውስጥ የሚደረጉ ልውውጦችን በሙሉ መዝግቦ የሚይዝ ነው።

መንግሥታትም ሆኑ ባንኮች ጣልቃ ሳይገቡበት ግብይቶችን ሰንዶ ይይዛል።

ብሎክቼይን የሚመዘግባቸው ግብይቶች በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ኮምፒውተሮች ላይ ስለሚቀመጥ በመረጃ መንታፊዎች ጥቃት ሊሰነዘርበት አይችልም።

አንድን የዲጅታል አርት ሥራ በብሎክቼይን ሥርዓት ላይ በተመሰረተው ኤንኤፍቲ መልክ ስንገዛ፤ ይህ የዲጂታል አርት ሥራ ከዚህ ቀደም ማን፣ መቼ፣ በምን ያህል ገዛው፤ እንዲሁም አሁን ባለቤትነቱ ማን ነው የሚለውን ማወቅ ያስችለናል።

ዲጂታል አርት

የፎቶው ባለመብት, BEEPLE / CHRISTIE'S

የምስሉ መግለጫ, ይህ ከ5ሺህ በላይ ምስሎች ስብስብ ነው የተባለ ዲጂታል አርት ለጨረታ ቀርቦ በኤንኤፍቲ መልክ በ69 ሚሊዮን ዶላር ተሽጧል።

ሰዎች ለኤንኤፍቲ በሚሊዮን ዶላር ለመክፈል የማይሳሱት ለምንድን ነው?

ከላይ ያለውን ምስል በ69 ሚሊዮን ዶላር ተገዝቷል።

ምንም እንኳ ለዚህ ምስል ይህን ያህል ገንዘብ ወጪ ይሁንበት እንጂ፣ ይህን ስዕል የትኛውም ሰው ሊያየው ይችላል። በመኖሪያ ቤቱ በፍሬም አድርጎ የሰቀለም ሊኖር ይችላል።

ሰዎች ለምን ከኢንተርኔት ላይ ማውረድ የሚችሉትን ስዕል መግዛት አስፈለጋቸው?

ለዚህ ምላሹ፤ የዲጂታል ጥበብ ብቸኛ ባለቤት የመሆን ፍላጎት እንዲሁም ኤንኤፍቲ የኢንቨስትመንት አማራጭ ነው የሚሉ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ።

የብሎክቼይን ሥርዓት ሰዎች ‘ዋና ቅጂ’ የሆነ የዲጂታል ጥበብ ባለቤት እንደሆኑ ያረጋግጥላቸዋል። በኤንኤፍቲ አማካይነት አንድ ሰው ማንም ሰው ጋር የሌሉ ዋና ቅጂ የሆኑ እና ባለቤትነታቸው የተረጋገጠላቸው የአርት ሥራዎች በዲጂታል መልክ ሰብስቦ እንዲይዝ ያስችለዋል።

የቢዝነስ ኢንሳይደር ዘጋቢዋ ግሬስ ኬይ ባለፉት ዓመታት ክሪፕቶከረንሲዎች በአማካይ ዋጋቸው እየጨመረ በመምጣቱ ሰዎች ኤንኤፍቲ ላይ ኢንቨስት ቢያደርጉ የተሻለ ትርፍ ሊያስገኝላቸው እንደሚችል ያስባሉ ትላለች።

ግሬስ ኬይ አንድ ማስተዋል ያለብን ነገር አለ ትላለች። ይህም የአንድ ኤንኤፍቲ ዋጋ የሚተመነው እንደ ገዢው ፍላጎት መሆኑን ነው። ሰዎች ለመክፈል ፍቃደኛ በሆኑበት መጠን በኤንኤፍቲ መልክ የቀረበው የዲጂታል ጥበብ ሥራ ዋጋ ከፍ ወይም ዝቅ ሊል ይችላል።

“ኤንኤፍቲ አዲስ ዕድል ይዞ መጥቷል”

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ X ይዘት መጨረሻ

ብዙዎቻችን ኮሜዲያን ቶማስ በሚለው የመድረክ ስሙ በስፋት ይታወቃል። ኮሚዲያን እዮስያስ አያሌው። ኮሜዲያን ቶማስ በቅርቡ ሁለት የዲጂታል ጥበብ ሥራዎቹን በኤንኤፍቲ አማካኝነት ሸጧል።

ከላይ የሚታየውን ምስል በ0.1 ኢቲሪየም ሽጧል። ይህም 9ሺህ ብር ገደማ ማለት ነው።

ኮሜዲያን ቶማስ “ኤንኤፍቲ ነገሮችን ቀላል እያደረገ ነው . . . ወደፊት በአርት ላይ ለተሰማሩ ሰዎች በጣም ጥሩ ነገር ይዞ ይመጣል” ሲል በኤንኤፍቲ ላይ ያለውን ተስፋ ይገልጻል።

ኮሜዲያን ቶማስ ‘ቶርፓ ጋንግስ’ ተብለው የተሰየሙ እና በእርሱ ፊት አምሳያ የተሰሩ ዲጂታል የጥበብ ሥራዎችን በኤንኤፍቲ አማካኝነት ለገበያ ሲያቀርብ “ሊሸጥም ላይሸጥም ይችላል ብዬ ነበር። ተሽጦ ወደ ዋሌቴ ሲገባ 'እንዴ ይሄ ነገር እውነት ነው?' አስባለኝ” በማለት ቀድሞ የተሰማውን ስሜት ያጋራል።

ቀደም ሲል የተሰነዘረውን ጥያቄ ለቶማስ እናቅርብ፤ ሰዎች ይህን መስል በስልካቸው ወይም ኮምፒዩተራቸው ላይ አውርደው ማየት፤ ወይም ግድግዳቸው ላይ መስቀል እየቻሉ ለምን 9ሺህ ብር ወጪ ያደርጉበታል?

ኮሜዲያን ቶማስ ለዚህ ጥያቄ መልሱ አጭር ነው። “ቤት ላይ መስቀል ትችላለህ። ግን ያ ዲጂታል አርት ያንተ አይደለም። የዚያ ስዕል ባለቤት አንድ እና አንድ ሰው ብቻ ነው። ምን ያህል እንዳወጣበትም ይታያል” ይላል።

ኮሜዲያን ቶማስ ሰዎች አንድን የዲጂታል አርት በኤንኤፍቲ የሚገዙት ለጌጥ ሳይሆን የተለየ ዋጋ ስለሚሰጧቸው ወይም ዋጋቸው ወደፊት ሊጨምር ይችላል ብለው ሲያምኑ ነው ይላል።

“ወደፊት (በእጅ የሚሳሉ) ስዕሎች ዋጋቸው እየቀነሰ የዲጂታል ስዕሎች ደግሞ ዋጋ ከፍ እያለ ይሄዳል” ሲል የወደፊት ምልከታቸውን ያስቀምጣል።