በፓሪስ በደረሰ የስለት እና የመዶሻ ጥቃት የሰው ሕይወት አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በማዕከላዊ ፓሪስ ላይ በደረሰ የስለት እና የመዶሻ ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል ሁለት ሰዎች ቆሰሉ።
ጥቃቱ የተፈጸመው ቅዳሜ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ላይ በታሪካዊው ኤይፍል ታወር አካባቢ በምትገኘው ኩዋይ ደ ግሬኔሌ ሰፈር ነው።
የፈረንሳይ ዜግነት ያለው የ26 ዓመቱ ጥቃት አድራሽ በቁጥጥር ስር ውሎ የጸረ ሽብርተኝነት አቃብያነ ሕግ ምርመራ ከፍተውበታል።
በጥቃቱ የተገደለው ግለሰብ ጀርመናዊ መሆኑን ባለስልጣናት አረጋግጠዋል።
የ24 ዓመት እድሜ ያለው ሰለባም በጥቃቱ ወቅት ከባለቤቱ ጋር እንደነበርም የፈረንሳዩ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጄራልድ ዳርሚኒ ገልጸዋል።
ባለቤቱም ሕይወቷ የተረፈው አንድ የታክሲ አሽከርካሪ ጣልቃ በመግባቱ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ግለሰቡ በአቅራቢያው የሚገኘውን የሴይን ወንዝ አቋርጦ መሸሹን ተናግረዋል።
ጥቃቱን ያላቆመው ተጠርጣሪ፣ ሁለት ግለሰቦች ላይ ጥቃት የከፈተ ሲሆን አንደኛውን ግለሰብ ዐይኑን በመዶሻ መምታቱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ግለሰቡ በግድያ ወንጀል እንዲሁም ከአሸባሪ ድርጅት ጋር ግንኙነት አለው በሚልም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል። በመዶሻ ጥቃት የተከፈተባቸው የ60 ዓመቱ ፈረንሳዊ እና ሌላኛው የውጭ አገር ቱሪስት ለሕክምና የተወሰዱ ሲሆን አንዳቸውም ለሕይወታቸው በሚያሰጋ ሁኔታ ላይ አለመሆናቸው ተገልጿል።
ጥቃቱ አድራሹ በአረብኛ ‘አላሁ አክባር’ (አምላክ ታላቅ ነው) እያለ ሲጮህ መሰማቱን ሚኒስትሩ ተናግረው በአፍጋኒስታን እና በፍልስጤም በርካታ ሙስሊሞች እየረገፉ መሆናቸው እንዳበሳጨው ለፖሊስ ተናግሯል ተብሏል።
ተጠርጣሪው በአውሮፓውያኑ 2016 ሌላ ጥቃት በማቀነባበር ተፈርዶበት አራት ዓመታትን በእስር ያሳለፈ ሲሆን የፈረንሳይ የደኅንነት አገልግሎትም በጥብቅ ሲከታተለው ነበር ተብሏል።
ግለሰቡ የአዕምሮ ህመሞች እንዳሉበት እንደሚታወቅም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
ቅዳሜ ዕለት ተጠርጣሪው የፈረንሳይ መንግሥትን የተቸበት እንዲሁም በንጹሃን ሙስሊሞች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግድያ የሚያወግዝበትን ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ማጋራቱንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።












