በአፍሪካ በሕይወት መቆያ ዕድሜ በ10 ዓመት ጨመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአፍሪካ በሕይወት የመቆያ ዕድሜ በ10 ዓመት መጨመሩን የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ።
አፍሪካ ውስጥ ሰዎች በሕይወት ይቆዩበት የነበረው አማካይ ዕድሜ ከዚህ ቀደም 46 የነበረ ሲሆን፣ አሁን ወደ 56 ከፍ ብሏል።
ሰዎች ዘለግ ያሉ ዓመታት መኖር የጀመሩት የተሻለ የሕክምና አቅርቦት በመዘርጋቱ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
ነገር ግን የዕድሜ ልኬቱ ከተቀረው ዓለም ጋር ሲነጻጸር አሁንም ከአማካዩ ያነሰ እንደሆነ አክሏል።
ሰዎች በሕይወት የሚቆዩበት ዕድሜ የሚሰላው ዕድሜያቸውን፣ ጾታቸውን እና የሚኖሩበትን አገር ከግምት በማስገባት ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት አሁን ያወጣው መረጃ ላይ ለመድረስ እአአ ከ2000 እስከ 2019 ከ47 የአፍሪካ አገራት የሰበሰበውን መረጃ ገምግሟል።
“በሌሎች አካባቢዎች ካለው መሻሻል የአፍሪካ ይበልጣል። ግን ኮሮናቫይረስ ያሳደረው ተጽዕኖ ለውጡን ሊቀለብስ ይችላል” ብሏል የዓለም ጤና ድርጅት።
የተባበሩት መንግሥታት፣ የዓለም ጤና ድርጅትም መረጃ ጠቅሶ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፣ በአፍሪካ ለታየው በሕይወት መቆያ ዕድሜ መሻሻል የጤና ሚኒስትሮች ምስጋና ይገባቸዋል።
እአአ በ2000 የሕክምና ሽፋን 24 በመቶ የነበረ ሲሆን በ2019 ወደ 46 በመቶ አድጓል።
በአፍሪካ በሕይወት መቆያ ዕድሜ ከጨመረባቸው ምክንያቶች አንዱ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት መሻሻሉ ነው።
እንደ ኤችአይቪ፣ ቲቢ እና ወባ ያሉ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ከ2005 ወዲህ ከፍተኛ ጥረት እየተደረ መሆኑ ይጠቀሳል።
ተመድ እንደሚለው፣ ተላላፊ በሽታዎችን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት አበረታች ቢሆንም በተቃራኒው እንደ ስኳርና ደም ግፊት ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በቁጥር እየጨመሩ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶ/ር ማትሺዲሶ ሞይቲ “ሰዎች ጤናማ ሆነው ለረዥም ዓመታት እየኖሩ ነው። በሽታን ለመከላከልም አበረታች ጥረት ተጀምሯል። ነገር ግን የታየው ለውጥ መገታት የለበትም። አገራት እንደ ካንሰር ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቅረፍ ጥረት ካላደረጉ የታየው ለውጥ ይከስማል” ብለዋል።
ኮሮናቫይስ በሕክምና መስጫ ተቋማት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ በሕይወት መቆያ ዕድሜ ላይ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል አያይዘው አንስተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የዳሰሳ ጥናት ሲሠራ ምላሽ ከሰጡ 36 የአፍሪካ አገራት መካል ወደ 90 በመቶው የሕክምና አገልግሎት መስተጓጎል እንደገጠማቸው ተናግረዋል።
መንግሥታት ለዜጎች ጤና ጥበቃ የሚመድቡት በጀት ከፍ ማለት እንዳለበት የዓለም ጤና ድርጅት መክሯል።
በአብዛኛው የአፍሪካ አገራት ከብሔራዊ የጤና በጀት 50 በመተo ብቻ ነው የሚያቀርቡት። ይህም ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ፈጥሯል።
ከግማሽ በላይ በጀት የሚመድቡ አገራት አልጄሪያ፣ ቦትስዋና፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ኢስዋቲኒ፣ ጋቦን፣ ሲሸልስ እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው።
ዜጎች ከኪሳቸው ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው ለሕክምና መክፈል እንደሌለባቸው የጠቀሰው የዓለም ጤና ድርጅት፣ የመንግሥት በጀት የግድ መሻሻል እንዳለበት ምክረ ሐሳቡን አስቀምጧል።
ከደመወዛቸው ከ10 በመቶ በላዩን ለሕክምና የሚያውሉ ሰዎች አስጊ ደረጃ የደረሱ ይባላሉ።
ባለፉት 20 ዓመታት በ15 የአፍሪካ አገራት ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ የራሳቸውን የሕክምና ወጪ ሲሸፍኑ ተስተውሏል።












