የቴሌግራም መስራች እና ኃላፊ ለወለዳቸው ከመቶ በላይ ልጆቹ ሃብቱን ሊያወርስ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለማችን ታዋቂ ከሆኑ የመረጃ መለዋወጫ መተግበሪያዎች አንዱ የሆነው ቴሌግራም መስራች እና ኃላፊ ፓቬል ዱሮቭ ለወለዳቸው ከ100 በላይ ልጆቹ 13.9 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብቱን ሊያወርስ እንደሆነ አስታወቀ።
እነዚህ ከመቶ በላይ ልጆች የተወለዱት ከ15 ዓመት በፊት ለአንድ ክሊኒክ በለገሰው ስፐርም አማካኝነት መሆኑን ተናግሯል።
"ሁሉም ልጆቼ ናቸው እናም እኩል መብት ይኖራቸዋል። እኔ ከሞትኩ በኋላ እርስ በርሳቸው እንዲበጣበጡ አልፈለግም" ሲል ዱሮቭ ለፈረንሳዩ የፖለቲካ መጽሔት ለ ፖይንት ተናግሯል።
ፓቬል በአባትነት እያሳደጋቸው ያሉ ስድስት ልጆችን ከሶስት አጋሮቹ አፍርቷል።
ሆኖም እሱ እንደሚለው "ጓደኛዬን ለመርዳት ከአስራ አምስት ዓመት በፊት ስፐርም የለገስኩበት ክሊኒክ በ12 አገራት ከ100 በላይ ህጻናት በኔ ስፐርም እንደተጸነሱ ነግሮኛል" ብሏል።
ሩሲያዊው የቴክኖሎጂ ባለጸጋ ጨምሮ እንደተናገረው ልጆቹ ውርሳቸውን 30 ዓመት እስከሚሞላቸው ድረስ እንደማያገኙት ለመጽሄቱ ተናግሯል።
"አንደ ተራ ሰው እንዲኖሩ እፈልጋለሁ፤ በራሳቸው ህይወታቸውን እንዲገነቡ፣ በራሳቸው መተማመን እንዲማሩ እንዲሁም መፍጠር እንዲችሉ እንጂ በባንክ አካውንታቸው ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ አልፈልግም" ሲል ተናግሯል።
የ40 ዓመቱ ወጣት አሁን ኑዛዜውን ማሰፈር ያስፈለገበት ምክንያት ከስራው ጋር በተያያዘ ያለውን አደጋ በመገንዘብ እንደሆነ ያስረዳል። "ነጻነትን መደገፍ ኃያላን መንግሥታትን ጨምሮ በርካታ ጠላቶችን ያተርፍልሃል" ይላል።
ሚስጥራዊ እና ግላዊነትን በጠበቀ መልኩ መረጃዎችን መለዋወጥ የሚያችለው ቴሌግራም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወርሃዊ ተጠቃሚዎች አሉት።
በፈረንሳይ ከቀረበበት ከባድ የወንጀል ክስ ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ጥፋት እንዳልፈጸመም በድጋሚ ተናግሯል።
ኃላፊው መተግበሪያውን ወንጀል ለመከላከል ተገቢውን የመከላከል ስራ አልሰራም በሚል ባለፈው ዓመት በፈረንሳይ ክስ ተመስርቶበታል።
ከአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር፣ የህጻናት ወሲባዊ ጥቃት ይዘት እና ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ከህግ አስከባሪ አባላት ጋር እየተባባረ አይደለም የሚለውን ኃላፊው አጣጥሏል።
ቴሌግራም ከዚህ ቀደም በቂ የቁጥጥር እና የክትትል ስርዓት አልዘረጋም የሚለውን አልተቀበለውም።
ክሱን "ፍጹም እርባና የሌለው" ሲል የቴሌግራም ኃላፊው ለመጽሄቱ ተናግሯል።
"ወንጀለኞች የእኛን ጨምሮ ሌሎች መረጃ መለዋወጫ መተግበሪያዎችን ስለሚጠቀሙ እነዚህን መተግበሪያዎች የሚያስተዳድሩትን ወንጀለኛ አያደርጋቸውም" ሲል አክሏል።
በሩሲያ የተወለደው ፓቬል ቴሌግራም መቀመጫውን ባደረገበት ዱባይ ውስጥ ነው ነዋሪነቱ።
ፓቬል የፈረንሳይ እና የተባበሩት አረም ኤምሬትስ ጥምር ዜግነት አለው።
የሩሲያው ማህበራዊ ሚዲያ ቭኮንታኬ መስራች የሆነው ፓቬል ከዚህ ቀደም ክሬምሊን ጽሁፎችን ሳንሱር እንዲያደርግ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ በማድረጉ ከዚህ ማህበራዊ ሚዲያ መባረሩን ተናግሯል።
ፓቬል ቴሌግራምን የመሰረተው በአውሮፓውያኑ 2013 ሲሆን መተግበሪያውም በሩሲያ ውስጥ ተወዳጅ ሆኖ ቆይቷል።
ቴሌግራም እስከ 200 ሺህ አባላት ያሉትን ቡድኖችን መመስረት ይፈቅዳል።
ይህም ተቺዎች የተሳሳተ መረጃ በቀላሉ እንዲሰራጭ እንዲሁም ለሴረኞች፣ የናዚ ደጋፊዎች፣ ህጻናት ደፋሪዎች እንዲሁም ከሽብር ጋር የተያያዙ ይዘቶች እንዲሰራጩ በር ከፍቷል ይላሉ።















