ተወዳጇ የሀሪ ፖተር ተዋናይት ማጊ ስሚዝ በ89 ዓመቷ አረፈች

የፎቶው ባለመብት, Alamy
በትወናው ዓለም ስምንት አስርታትን በተወዳጀነት ያሳለፈችው ማጊ ስሚዝ በትናንትናው ዕለት ሕይወቷ ማለፉ ተሰምቷል።
በሀሪ ፖተር፣ በዳውንታውን አቢ እንዲሁም ሌሎች ተወዳጅ የፊልም እና የመድረክ ስራዎቿ የምትታወቀው ዴም ማጊ ስሚዝ በ89 ዓመቷ ነው ሕይወቷ ያለፈው።
በ1950ዎቹ በመድረክ ላይ ቴአትር በማቅረብ ወደ ጥበቡ ዓለም የገባችው ዴም ማጊ ስሚዝ ከአንድ ዓመት በፊት ‘ዘ ሚራክል ክለብ' የተሰኘ ፊልሟ ለእይታ በቅቷል።
ሁለት ኦስካሮችን ያሸነፈችው ማጊ ስሚዝ አራት ኤሚ እንዲሁም ቶኒ ከአሜሪካ ስታገኝ በአገሯ ደግሞ ሰባት ባፍታ እንዲሁም የክብር ሽልማቶችን ተቀብላለች።
ንጉሥ ቻርለስ “ብሔራዊ ሀብት” ሲሉ ያንቆለጳጰሷት ሀሪ ፖተር ላይ አብሯት የተወነው ዳንኤል ራድክሊፍ ደግሞ “ድንቅ ብቃት” ሲል ችሎታዋን እንዲሁም “አንደበቷ የሰላ” ሲል መስክሮላታል።
የሞቷ ዜና ከተሰማ በኋላ የእንግሊዙ ንጉሥ እና ንግሥት በጋራ በሰጡት መግለጫ “በብሔራዊ ሀብታችን ላይ መጋረጃው ሲጋረድ፣ በድንቅ ብቃቷ የተወነቻቸውን ስራዎቿን፣ በመድረክም ሆነ ከመድረክ ውጪ ጎልቶ የሚታየውን ቀልዷን፣ ጨዋታዋን በበዛ ፍቅር እና አድናቆት ከመላው ዓለም አድናቂዎቿ ጋር ስናስታውስ እንኖራለን” ብለዋል።
ብሪታንያዊቷ ተወዳጅ እና ድንቅ ተዋናይ ዴም ማጊ ስሚዝ ከሼክስፔሩ ኦቴሎ እስከ ሀሪ ፖተር እና ዳውንታውን አቢ ድረስ ተውናለች።
ሞቷ የተሰማው በትናንትናው ዕለት ሲሆን ሁለት ልጆች እና አምስት የልጅ ልጆች ማፍራቷም ሞቷን አስመልከቶ የወጣው መግለጫ ያስረዳል።
እኤአ በ1934 በለንደን የተወለደችው ማጊ ስሚዝ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ቤተሰቦቿ ወደ ኦክስፎርድ አምርተው በዚያ ኑሯቸውን አድርገዋል።
ለመጀመርያ ጊዜ ወደ መድረክ ብቅ ያለችው በሼክስፔር ስራዎች እንደሆነ በሕይወቷ ላይ የተጻፉ ድርሳኖች ያሳያሉ።
የዊሊያም ሼክስፒር ተውኔት የሆነው 'ትዌልፍዝ ናይት' የተሰኘው ስራ ላይ ከተወነች በኋላም በተለያዩ ተውኔቶች ላይ ተሳትፋለች።
በ1964 ኦቴሎ ላይ የዴዝዴሞናን ገጸ ባህሪ ተላብሳ የተወነችው ማጊ ስሚዝ፣ በተከታዩ ዓመት ወደ ፊልሙ ዓለም ገብታለች።
ማጊ ስሚዝ የመጀመርያውን አካዳሚ አዋርድ በ1969 በ 'ዘ ፕራይም ኦፍ ሚስ ጄን ብሮዲ' ላይ ላሳየችው ድንቅ የትወና ብቃት ተሸልማለች።
በ1978 እንዲሁ በረዳት ተዋናይነት በ 'ካሊፎርኒያ ስዊት' ላይ ላሳየችው ትወና ሁለተኛውን የአካዳሚ አዋርድ ሽልማት አግኝታለች።
ዴሚ ስሚዝ በበርካታ ታዳጊ የፊልም አፍቃርያን ዘንድ የምትታወቀው በ 'ሀሪ ፖተር ኤንድ ዘ ሶርሰረርስ ስቶን' ላይ በነበራት የጠንቋይ መምህርት ገጸባህሪ ነው።
ከዚያም በመቀጠል በርካታ የሃሪፖተር ተከታታይ ፊልሞች ላይ ተውናለች።
ማጊ ስሚዝ በመላው የፊልም እና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ አፍቃርያን ዘንድ በ 'ዳውንታውን አቢ' ላይ በነበራት ትወና ተወዳጅነትን አትርፋለች።
በዚህም ትወናዋም ሦስት የኤሚ አዋርዶችን ተቀብላለች።












