የተባበሩት መንግሥታት በዌስት ባንክ በተፈጸመው ግድያ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠየቀ

አይሰኑር እዝጊ ኢይጊ

የፎቶው ባለመብት, International Solidarity Movement

የምስሉ መግለጫ, አይሰኑር እዝጊ ኢይጊ በቤታ ከተማ የአይሁዳውያን ሰፈራ መስፋፋትን በመቃወም በተካሄደ ሰልፍ ላይ ተሳትፋ ነበር።
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የተባበሩት መንግሥታት በዌስት ባንክ አርብ ዕለት በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የአሜሪካ እና የቱርክ ጥምር ዜግነት ያላት ወጣት ግድያን በተመለከተ ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ ጠየቀ።

አይሰኑር እዝጊ ኢይጊ የተገደለችው የእስራኤል ኃይሎች ተኩስ ከከፈቱ በኋላ ነበር።

የ26 ዓመቷ ወጣት በናብላስ አቅራቢያ በምትገኘው ቤታ ከተማ የአይሁዶችን ሰፈራ መስፋፋትን በመቃወም በተካሄደው ሳምንታዊ ተቃውሞ ላይ ተሳትፋ ነበር።

የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ ኢይጊ በእስራኤል ወታደሮች ተተኩሶባት ነው የተገደለችው።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ በአካባቢው በተከፈተ ተኩስ የውጭ ዜጋ መገደሏን የሚያሳዩ ሪፖርቶችን እየመረመርኩ ነው ብሏል።

አንድ የዓይን እማኝ በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ሁለት ጊዜ የተኩስ ድምጽ መስማታቸውን ለቢቢሲ ኒውስ አዎር ፕሮግራም ተናግረዋል።

ግድያውን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ “ ስለሁኔታው የሚያስረዳ የተሟላ ምርመራ ማየት እንፈልጋለን።ይህንን የፈፀሙ አካላትም ተጠያቂ መሆን አለባቸው” ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም ሰላማዊ ሰዎች ሁል ጊዜም ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

አሜሪካም ግድያውን በተመለከተ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቃለች። የዋይት ሃውስ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ሲን ሳቬት እንዳሉት ዋሽንግተን በዜጋዋ ላይ በተፈፀመው አሳዛኝ ግድያ ክፉኛ መበሳጨቷን ገልጻለች።

“ በግድያው ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘትና ስለክስተቱ ምርምራ እንዲደረግም እስራኤልን ጠይቀናል” ብለዋል ሳቬት።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከተኩሱ በኋላ የተቀረጸ ተንቀሳቃሽ ምስል የጤና ባለሙያዎች ኢይጊን ወደ አምቡላንስ በጥድፊያ ሲወስዷት አሳይቷል።

በተቃውሞ ሰልፉ ላይ የነበረው አይሁዳዊ-እስራኤላዊ የማኅበረሰብ አንቂ ጆናታን ፖላክ፣ወታደሮች ጣራ ላይ ሆነው ሲያነጣጥሩ መመልከቱንና ሁለት ጊዜ ተኩስ መስማቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ የሆነ ሰው ስሜን እየጠራ 'እርዳን፣ እርዳታህን እንፈልጋለን' ሲለኝ ወደ እነሱ ሮጥኩ” ብሏል ጆናታን የዓይን ምስክርነቱን ለቢቢሲ ሲሰጥ።

ከዚያም ኢይጊ ጭንቅላቷ እየደማ በወይራ ዛፍ ሥር ወድቃ መመልከቱን ተናግሯል።

ጥምር ዜግነት ያላት ኢይጊ ወደ ሆስፒታል የተወሰደች ሲሆን የራፊዳ ሆስፒታል ኃላፊ ዶክተር ፉአድ ናፋ በ20ያዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ የምትገኝ የአሜሪካ ዜጋ በጥይት ጭንቅላቷ ላይ ተመትታ መሞቷን አረጋግጠዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሞቷን አሳዛኝ ያሉት ሲሆን የቱርኩ ፕሬዚደንት ሬሲፕ ታይብ ኤርዶዋን ደግሞ የእስራኤልን ድርጊት 'አረመኒያዊ' ሲሉ ገልጸውታል።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ኢይጊ፣ ናብለስ ከተማ ውስጥ በእስራኤል ወታደሮች ተገድላለች ብሏል።

ኢይጊ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ከማምራቷ በፊት በቅርቡ ሲያትል ከሚገኘው ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ተመርቃለች።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት አና ማሪ ካውስ በኢይጊ ሞት ማዘናቸውን ገልጸው፣ ኢይጊ የሌሎች ተማሪዎች አርዓያ ነበረች ብለዋል።

እስራኤል ባለፉት 50 ዓመታት በኃይል በያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ እየሩሳሌም ለ700 ሺህ የሚጠጉ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች።

እስራኤል ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ እየሩሳሌም እያደረገች ያለውን ሰፈራ እና በእነዚህ አካባቢዎች እና በጋዛ ውስጥ የምትካሂደውን ሕገ ወጥ ወረራ በአስቸኳይ እንድታቆም ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም ብያኔ አስተላልፏል።

ይህ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እና የእንግሊዝ እንዲሁም የሌሎችም አቋም ነው።እስራኤል ግን ውሳኔውን አትቀበለውም።