የናፖሊዮን ሁለት ሽጉጦች በ1.69 ሚሊዮን ዩሮ ተሸጡ

በጨረታ የተሸጡት የናፖሊዮን ሽጉጦች

የፎቶው ባለመብት, Osenat auction house

የፈረንሳዩ ንጉሠ ነገሥት ናፖሊዮን ቦናፓርት ንብረት የሆኑ ሁለት ሽጉጦች በ1.69 ሚሊዮን ዩሮ በጨረታ ተሸጡ።

ከሁለቱ ሽጉጦች በአንደኛው ናፖሊዮን በአንድ ወቅት ራሱን ሊያጠፋ እንደነበር ይነገራል።

እነዚህ በፓሪስ ሽጉጥ አምራቹ ሉዊስ ማሪን ጎሴ የተሠሩት ሽጉጦች ከ1.2 ሚሊዮን ዩሮ እስከ 1.5 ሚሊዮን ዩሮ ያወጣሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።

ሽጉጦቹ እሑድ ዕለት በኦሴናት የጨረታ ቤት ነው የተሸጡት። ጨረታው የተካሄደበት ስፍራ ናፖሊዮን በ1814 ከሥልጣን መወገዱን ተከትሎ ሕይወቱን ለማጥፋት ከሞከረበት ፎንቴንብሉ ቤተ መንግሥት አጠገብ የሚገኝ ነው።

ሽጉጦቹ ለጨረታ ሽያጭ የቀረቡት የፈረንሳይ የባህል ሚኒስቴር በቅርቡ በብሔራዊ ቅርስነት ከሰየማቸው እና ከአገር እንዳይወጡ ካገዳቸው በኋላ ነው።

ይህ ማለት የፈረንሣይ መንግሥት ለጊዜው ስሙ ካልተገለጸው አዲሱ ባለቤት ሽጉጦቹን ለመግዛት 30 ወራት አሉት ማለት ነው። ነገር ግን ሽጉጦቹ በጊዜያዊነት ብቻ ከፈረንሳይን መውጣት ይችላሉ።

ሽጉጦቹ በወርቅ እና በብር ያሸበረቁ ሲሆን የናፖሊዮን ምስልም ተቀርጾባቸዋል።

ናፖሊዮን ጦሩ በውጭ ኃይሎች መሸነፉን ተትሎ እአአ ሚያዝያ 12 ቀን 1814 ሌሊት እራሱን ለመግደል ሊጠቀምባቸው ፈልጎ ነበር ተብሏል።

የቅርብ ረዳቱ ከጥይቶቹ ውስጥ ባሩዱን አውጥቶት ስለነበር ናፖሊዮን በመርዝ እራሱን ለማጥፋት ቢሞክርም ሕይወቱ ሳያልፍ ለመትረፍ ችሏል።

በኋላም ሽጉጦቹን ለዚሁ የቅርብ ረዳቱ የሰጠ ሲሆን እሱም ለዘመዶቹ አውርሷል።

በጨረታው ላይ ከሽጉጦቹ ጋር የተለያዩ መለዋወጫዎችም አብረው ተሽጠዋል።

የናፖሊዮን ዕቃዎች በጣም ተፈላጊ ናቸው። መለያዎቹ ከሆኑት ኮፍያዎቹ አንዱ ባለፈው ኅዳር ወር በ1.9 ሚሊዮን ዩሮ ተሸጧል።

ታሪካዊው መሪ ወደ ሜዲትራኒያን ደሴቷ ኤልባ ከተሰደደ በኋላ በ1815 ወደ ሥልጣን የተመለሰ ቢሆንም በዋተርሉ ጦርነት ተሸንፎ ከሥልጣን ተወግዷል።

ናፖሊዮን ለሁለተኛ ጊዜ በደቡብ አትላንቲክ ውቅያኖስ ወደምትገኘው ሴንት ሄለና ደሴት ከተሰደደ በኋላ በ 1821 ነበር ሕይወቱ ያለፈው።