ስድስት ፈረንሳዊያን ታዳጊዎች ከመምህራቸው ግድያ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት ቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ስድስት ፈረንሳዊያን ታዳጊዎች በመምህራቸው ግድያ ላይ ተሳትፈዋል በሚል በፓሪስ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ታዳጊዎቹ የመምህሩን ስም በማጥፋት እና የቼቺን ስደተኛ ለሆነው የመምህሩ ገዳይ ጥቆማ በመስጠት ክስ ቀርቦባቸዋል።
ከሦስት ዓመታት በፊት ግድያው ሲፈፀም ታዳጊዎቹ ከ13 እስከ 15 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የነበሩ ሲሆን የፍርድ ሒደቱ የተካሄደው በዝግ ችሎት ነው።
የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የሁለት ዓመት ከመንፈቅ እስር የሚጠብቃቸው ተጠርጣሪዎቹ፣ ሰኞ እለት የአዳጊ ወንጀል ፈጻሚዎች ጉዳይ የሚመለከት ፍርድ ቤት ሲደርሱ ማንነታቸውን ደብቀው ነበር።
መምህር ሳሙኤል ፓቲ በነጻነት ሐሳብን ስለመግለጽ እያስተማረ ባለበት ወቅት ለተማሪዎቹ የነብዩ መሐመድን ካርቱኖች አሳይቷል ከተባለ በኋላ በስልት ተወግቶ እና አንገቱ ተቀልቶ የተገደለው እንደ አውሮፓውያኑ 2020 ነበር።
በእድሜ ትንሿ ተጠርጣሪ ግድያው ሲፈፀም እድሜዋ 13 የነበረ ሲሆን፣ መምህር ፓቲ ከመገደሉ ዘጠኝ ቀናት በፊት ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት በሌላቸው ምክንያቶች ከትምህርት ቤቱ ታግዳ ነበር።
ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው ታዳጊዋ ፍርድ ቤት ስትደርስ ማንነቷ እንዳይታወቅ ረጅም ጥቁር ጃኬት ተከናንባ ነበር።
ታዳጊዋ ሙስሊም ተማሪዎች ክፍሉን ለቀው እንዲወጡ ከጠየቀች በኋላ ከመምህር ፓቲ ጋር ግብግብ በመፈጠሩ መቀጣቷን በሐሰት ለአባቷ ተናግራለች ተብሏል።
ይህንንም ተከትሎ የታዳጊዋ አባት መምህሩ ከሥራው እንዲባረር በማኅበራዊ ሚዲያ ባጋራቸው ቪዲዮዎች ጠይቋል።
አቃቤ ሕጎች እነዚህ ቪዲዮዎች ገዳዩን ቼቺን ጎሳ አባል አብዶላህ አንዞሮቭን ይኖርበት ከነበረው ኖርማንዲ ወደ 80 ኪሎ ሜትር በመጓዝ በፓሪስ አቅራቢያ ወደ ሚገኘው ኮንፍላንስ ሴንት ሆኖሪን እንዲጓዝ አነሳስተውታል ብለው ያምናሉ።
በወቅቱ የ18 ዓመት ወጣት የነበረው አንዞሮቭ ግድያውን ከፈፀመ በኋላ እዚያው በፖሊስ ተገድሏል።
ሌሎች አምስት ተጠርጣሪዎችም 260 ዶላር በመቀበል መምህር ፓቲን በመጠቆም አንዞሮቭን ረድተዋል ተብሏል።
አንደኛው ተጠርጣሪ እንዳለው አንዞሮቭ፣መምህር ፓቲ የነብዩ መሐመድን ካርቱኖች በማሳየቱ ይቅርታ ሲጠይቅ መቅረጽ እንደፈለገ እንደነገረው ተናግሯል።
በግድያው ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ ሌሎች ስምንት አዋቂዎችም በመጭው የፈረንጆቹ ዓመት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።
ከእነዚህ ግለሰቦች መካከል የ13 ዓመቷ ታዳጊ አባት ብራሂም ቺኒና ይገኝበታል።
አቃቤ ሕጎች በሽብር ግድያ ላይ በመሳተፍ በአንዞሮቭ ሁለት ጓደኞች ላይም ክስ መስርተዋል።
ክስ የቀረበባቸው፣አንደኛው አንዞሮቭ መሣሪያ ሲገዛ አብሮት በመሄዱ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ግድያው በተፈፀመበት ወቅት መምህር ፓቲ ወደሚያስተምርበት ትምህርት ቤት በመኪና በማድረሱ ነው ።












