እስራኤል ሟቹን የሄዝቦላህ መሪ ይተካሉ የተባሉትን ግለሰብ መግደሏን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤል ጦር ሠራዊት ከሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህ መገደል በኋላ የቡድኑ መሪ ይሆናሉ የተባሉት ምክትላቸውን ከሦስት ሳምንት በፊት በፈጸመው የአየር ጥቃት መግደሉን አስታወቀ።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል እንደገለጸው ሐሼም ሳፌዲን የቡድኑ ከፍተኛ አመራር የተገደሉት በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ደቡባዊ ክፍል ዳርቻ ላይ በተፈጸመ የአየር ድብደባ ነው።
ከእስራኤል ጋር እየተፋለመ ያለው በሊባኖስ ኃያል የሆነው የሺአ ሙስሊም ድርጅት ሄዝቦላህ ግን የሴፌዲንን ሞት እስካሁን አላረጋገጠም።
የቡድኑ መሪ የነበሩት ሐሳን ናስራላህ እስራኤል ባለፈው መስከረም 17/2017 ዓ.ም. ቤይሩት ውስጥ በፈጸመው ጥቃት ነበር የተገደሉት።
በዋና ከተማዋ አየር ማረፊያ አቅራቢያ መስከረም 24 ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ የሄዝቦላህ ባለሥልጣናት ከሳፌዲን ጋር ያላቸው ግንኙነት መቋረጡን የተናገሩ ሲሆን፣ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ የእስራኤል ባለሥልጣናትን በመጥቀስ የአየር ጥቃቱ ዒላማ ሳፌዲን ነበሩ ብለው ዘግበዋል።
ማክሰኞ ዕለት የእስራኤል የመከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ ቤይሩት በሚገኘው የሄዝቦላህ የደኅንነት ዋና መሥሪያ ቤት ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ሳፌዲንን ጨምሮ የቡድኑ የደኅንነት ኃላፊ አሊ ሁሴን ሃዚማ ተገድለዋል።
መግለጫው ሳፌዲን ለዓመታት “በእስራኤል ላይ የሽብር ጥቃቶች እንዲፈጸሙ” ሲያዙ መቆየታቸውን እና በሄዝቦላህ “ማዕከላዊ የውሳኔ ሰጪ አካል ውስጥ” ተሳታፊ ናቸው በማለት ከሷል።
ሄዝቦላህ በሊባኖስ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ድርጅት ነው። ቡድኑ በእስራኤል፣ በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በሌሎች አገራትም ሽብርተኛ ተብሎ ተሰይሟል።
ሳፌዲን ራሳቸው በአሜሪካ እና በሳዑዲ አረቢያ በአውሮፓውያኑ 2017 “ዓለም አቀፍ ሽብርተኛ” ተብለዋል።
ከተገደሉት የቡድኑ መሪ ጋር ዝምድና ያላቸው ሳፌዲን ኢራን ውስጥ ሃይማኖታዊ ትምህርት የተከታተሉ ሲሆን፣ ወንድ ልጃቸው ደግሞ ከአራት ዓመት በፊት ኢራቅ ውስጥ በአሜሪካ የድሮን ጥቃት የተገደሉት ኃያሉ የኢራን ጄኔራል ቃሴም ሱሌይማኒ ሴት ልጅን አግብቷል።
በተገደሉበት ጊዜ ዕድሜያቸው 60 እንደሚደርስ የሚታመነው ሳፌዲን፤ ከወራት በፊት ቤይሩት ውስጥ ባደረጉት ንግግር ሄዝቦላህ እንዴት አመራሩ እንደሚተካካ ገልጸው ነበር።
“በትግላች ውስጥ የትኛውም መሪ መስዋዕት ሲሆን፣ ሌላ ሰው አርማውን አንስቶ በአዲስ፣ በእርግጠኝነት፣ በቆራጥነት ወደፊት ይቀጥላል” ማለታቸውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቧል።
እስራኤል እና ሄዝቦላህ በጋዛ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ድንበር ተሻጋሪ የከባድ መሳሪያ ግጭቶች እና የአየር ድብደባ ሲያካሂዱ ለአንድ ዓመት ያህል ከቆዩ በኋላ ነው ወደለየለት ጦርነት የገቡት።
እስራኤል በሄዝቦላህ የሚሳዔል፣ የሮኬት እና የድሮን ጥቃቶች ምክንያት ከሰሜናዊ ግዛቶቿ የተፈናቀሉ ዜጎቿን ለመመለስ እና ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ በሚል አንድ ወር ያለፈው የአየር እና የእግረኛ ሠራዊት ጥቃት በሊባኖስ ውስጥ እያካሄደች ነው።
ግጭቱ ከተከሰቀሰ በኋላ ባለው በአንድ ዓመት ውስጥ ቢያንስ 2 ሺህ 464 ሊባኖሳውያን ሲገደሉ ወደ 12,000 የሚጠጉት ደግሞ የመቁሰል ጉዳት እንደደረሳባቸው የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በተመሳሳይ ጊዜ ሄዝቦላህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶች እና ድሮኖችን በመጠቀም በእስራኤል ላይ ጥቃት የፈጸመ ሲሆን፣ ቢያንስ 59 እስራኤላውያን በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል እና በወረራ በያዘችው የጎላን ተራሮች አካባቢ መገደላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።















