ተመራማሪዎች የወፍ ጉንፋን ቀጣዩ የዓለማችን ወረርሽኝ ይሆናል ብለው ለምን ሰጉ?

ዶሮ የያዘ የሕክምና ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ተመራማሪዎች ለወራት በእርሻዎች ላይ እየተስፋፋ ያለው የወፍ ጉንፋን ቀጣዩ የዓለም ወረርሽኝ ይሆናል በሚል የማስጠንቀቂያ ደወል እያሰሙ ነው።

በሽታዎች እንዴት እንደሚጎለብቱ የሚያጠኑ ተመራማሪዎች የወፍ ጉንፋን ልብ ሳንለው ወደ ሰዎች በመዛመት ወረርሽኝ ይሆናል በማለት አስጠንቅቀዋል።

ኤች5ኤን1 በሚል የሚጠራው 'አቪያን ፍሉ' ከአውስትሬሌዚያ (አውስትራሊያ፣ ኒውዝላንድ እና አጎራባች ደሴቶች) ውጭ ያሉ አህጉራት ደርሷል።

በሽታው በአንታርቲካ ፔንጉዊኖች እና በመካከለኛው ምሥራቅ ግመሎች ላይ ተገኝቷል።

በሽታው አሁን ላይ በ50ዎቹም የአሜሪካ ግዛቶች በዱር ወፎች እና አጥቢ እንስሳዎች ላይ ተገኝቷል። እንደ አሜሪካ የግብርና መሥሪያ ቤት መረጃ በሽታው ከዶሮ እርባታዎች በመውጣት አንድ ሺህ ላሞች ላይ ተገኝቷል።

70 ሰዎችም በበሽታው ሲያዙ የአንድ ሰው ሕይወት አልፏል።

በሽታው ከመሰራጨቱ በፊት ለማስቆም የነበሩ ወሳኝ ዕድሎች የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የጆ ባይደን አስተዳደሮች እንዳመለጧቸው በጆን ሆፕኪንስ የኅብረተሰብ ጤና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ካትሊን ሪቨርስ ተናግረዋል።

በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች በእንስሳት ዝውውር ላይ የተለያየ ሕግ አላቸው።

"[አቪያን ፍሉ] ጊዜያዊ ችግር አይደለም። ወዲያው ይጠፋል የሚል የተሳሳተ እምነት ነበር። አሁን ግን ችግሩ በደንብ መታየት እንዳለበት ግንዛቤ ላይ ተደርሷል" ብለዋል።

"አሁን ትልቁ ቅድሚያ የሚሰጠው ግኝቱ ነው። እንዴት እየተለወጠ መሆኑን ለማየት በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ማግኘት ነው። ይህ ነው ትልቁ ስጋት" በማለት አክለዋል።

የወፍ ጉንፋን ቀጣዩ ወረርሽኝ ይሆን?

በሽታን የሚያጠኑ ተመራማሪዎች አሜሪካ ብቻ ሳትሆን መላው ዓለም በበቂ ሁኔታ አልተዘጋጀም በሚል አሳስቧቸዋል።

"አሳሳቢው ነገር በአሜሪካ በእንስሳት ላይ የተቀሰቀሰው በሽታ ለሌላ ወረርሽኝ የሚወስድ ነው የሚለው ነው" ሲሉ በቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ካምራን ካህን ተናግረዋል።

"በታሪክ ኤች5ኤን1 ለሰዎች በጣም አደገኛ ቫይረስ እንደሆነ እናውቃለን" ብለዋል።

ከኅዳር 2016 ዓ.ም. ወዲህ በዋናነት ከ15 አገራት 700 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ለዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት ተደርጎለታል።

ከእነዚህ አገራት መካከል ኢንዶኔዢያ፣ ቬትናም እና ግብፅ ከፍተኛ ቁጥር በበሽታው የተያዘባቸው ናቸው።

አቪያን ፍሉ አዲስ ነገር አይደለም። ነገር ግን አሁን ተመራማሪዎች በሦስት ምክንያቶች ተጨንቀዋል።

የመጀመሪያው በበሽታው የተያዙ አጥቢ እንስሳት ዝርያ ሲሆን ከእርሻዎች እስከ እርሻ ሠራተኞች፤ ከዱር እንስሳት እስከ ቤት እንስሳት ድረስ በሽታው ተገኝቷል።

ሁለተኛው አሳሳቢ ምክንያት የስርጭቱ ፍጥነት ነው። ከሰዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ባላቸው የወተት ላሞች የተሰራጨበት ፍጥነት አሳሳቢ አድርጎታል።

በትራምፕ አዲስ አስተዳደር የኅብረተሰብ ጤና ላይ የተፈጠረው አለመረጋጋት ሦስተኛው አስጊ ምክንያት ሲሆን፤ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያዎች ከሥራ ተባረዋል። እርምጃው የወፍ ጉንፋን ምርመራ መርሃ ግብሮች እንዲሰረዙ እና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የእርሻ ሠራተኞች ለመመርመር እንዲያመነቱ አድርጓል።

ጥጃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የወፍ ጉንፋን እንዴት ይሰራጫል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የወፍ ጉንፋን (በርድ ፍሉ) ለ100 ዓመታት ያህል በዶሮዎች እና በዱር አእዋፋት ዘንድ የኖረ ተላላፊ በሽታ ነው።

ቫይረሱ አየር ወለድ በሽታ እንደመሆኑ ከላም ወደ ላም አይተላለፍም፤ ከዚህ ይልቅ የወተት አመንጪ እጢዎቻቸውን አጥቅቷል።

ሳይንቲስቶች ቫይረሱ ወደ ላሞቹ የተላለፈው በወተታቸው በኩል መሆኑን ይናገራሉ ።

በዩናይትድ ስቴትስ የእንስሳት ሳይንስ ምርምር ማዕከል ባልደረባ ዶክተር ቶማስ ፒኮክ "በተበከለ የወተት ማሽን አማካኝነት የተላለፈ ይመስላል" ብለዋል።

የወፍ ጉንፋን ለ100 ዓመታት ያህል የቆየ የዶሮ እና የዱር አእዋፋት ተላላፊ በሽታ ነው።

በመጋቢት 2025 መገባደጃ ላይ፣ በሰሜን እንግሊዝ ውስጥ በዮርክሻየር በሚገኝ አነስተኛ እርሻ አንዲት በግ የወፍ ጉንፋን እንዳለባት ታወቀ።

እርሻው አንድ ላይ ተቀላቅለው የሚውሉ የበግ እና የዶሮ እርባታ ነበረው።

የዓለም ጤና ድርጅት በ24 አገራት ቢያንስ 954 ሰዎች በኤች5ኤን1 አቪያን ፍሉ ሲያዙ ከእነዚህም ውስጥ 464 ያህሉ ሞተዋል ሲል አስታውቋል።

በበሽታው የተያዙት ሰዎች በቫይረሱ ከተጠቁ ወፎች እና ሌሎች ፍጥረታት ጋር የቅርብ ግንኙነት ነበራቸው ተብሏል።

በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በሜክሲኮ ውስጥ የ59 ዓመት እድሜ ያለው ጎልማሳ ከዚህ በፊት በሰዎች ላይ ተመዝግቦ በማያውቅ ሌላ ዓይነት የወፍ ጉንፋን (ኤች 5ኤን2) ተጠቅቶ ሞቷል።

በሜክሲኮ ውስጥ በአንዳንድ የዶሮ እርባታዎች ላይ ወረርሽኞች ቢኖሩም ግለሰቡ ግን እንዴት እንደያዘው ግልጽ መረጃ የለም።

የዓለም ጤና ድርጅት የሰው ልጅ በበሽታው ከተያዙ እንስሳት ጋር በእርባታ እና በእርድ ወቅት የሚኖረው ንክኪ ወይም በበሽታው በተያዙ እንስሳት የሰውነት ፈሳሽ የተበከሉ ነገሮችን በመንካት ለወፍ ጉንፋን ሊጋለጥ እንደሚችል ገልጿል።

እንደ የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማእከል (ሲዲሲ) ቫይረሱ መለስተኛ ጉንፋን መሰል ምልክቶችን የሚያስከትል ሲሆን፣ ለሞት የሚያጋልጡ እንደ ሳምባ ምች ያሉ ከባድ ሕመሞችንም ሊያመጣ ይችላል።

ሰዎች በወፍ ጉንፋን ሊያዙ ይችላሉ?

ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ ወደ ወረርሽኝ የመቀየር እድሉ ከሰው ወደ ሰው መተላለፍ ይችላል ወይ በሚለው ላይ የተመሰረተ ነው።

እስካሁን ድረስ የወፍ በሽታ ከሰው ወደ ሰው አይተላለፍም።

ባለፈው ሚያዚያ ወር በዶሮ እርባታዎች ላይ 59 ጊዜ በሽታው ተቀስቅሷል። የዓለም የጤና ድርጅት የእንስሳት ጤና መረጃ መሰረት በአሜሪካ፣ አውሮፓ እና እስያ 44 ጊዜ በወፎች እና በአጥቢ እንስሳት በሽታው ተከስቷል።

ከታኅሳስ 2017 ዓ.ም. ወዲህ በአሜሪካ፣ ዩኬ፣ ሕንድ፣ ሜክሲኮ፣ ኮሎምቢያ እና ቬትናም ኤች5ኤን1 ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።

ለአስርት ዓመታት የወፍ በሽታ በሰዎች ላይ አነስተኛ ችግር የፈጠረ በአብዛኛው የወፍ ቫይረስ ሲሆን፤ አሁን ግን ለአጭር ጊዜ የሚቆይ በተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎች እየዘለለ ያለ ቫይረስ ነው።

"ቫይረሱ በመለወጥ እና በመላመድ የሚታወቅ ነው" ያሉት ዶ/ር ሪቨርስ፤ ለረጅም ጊዜ በስርጭት የሚቆይ ከሆነ ለመላመድ በርካታ መንገዶችን ያገኛል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ወፎች ዓለም አቀፍ ድንበሮችን የማይለዩ በመሆናቸው ተመራማሪዎች በፀደይ የወፎች እንቅስቃሴ በሽታው ሊኣገርሽ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

ክትባት እየተሰጣት ያለች ጫጩት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ክትባት አለ? ሰዎችስ መከተብ ይችላሉ?

እንስሳትን መከተብ አወዛጋቢ ነው። ስኬታማ ክትባት ከባድም ነው። ክትባቶች ተሽጠው የሚያልቁ ሲሆን፤ ይህም አንዳንድ አርሶ አደሮች በከፊል እንዲከትቡ እንደሚያደርግ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

"ለምሳሌ ፈረንሳይ ዳክዬዎችን ትከትባለች፤ ይህም ተላላፊ በሽታዎችን ዝቅ አድርጓል። በቀጠናው ስርጭቱን ቀንሶታል" ይላሉ ዶ/ር ሙኒር ኢቅባል የተባሉ ባለሙያ።

የተከተቡ ወፎች ቫይረሱን በመያዝ ለሌሎች ወፎች ማስተላለፍ ይችላሉ።

በአሜሪካ እና በሌሎች አገራት መንግሥታዊ ተቋማት የአቪያን ቫይረስ ክትባት ሚሊዮን ብልቃጦችን ለሰዎች ሲሉ እያከማቹ ነው።

"በከፍተኛ ስጋት አካባቢዎች ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው፤ ስለዚህ ከእንስሳት ጋር የቅርብ ንክኪ ላላቸው ሠራተኞች" ሲሉ ዶ/ር ካን ተናግረዋል።

"የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ወረርሽኝ የሚሆን ከሆነ የቫይረሱ ዓይነት ተወስዶ ክትባት በማዳበር በሰፊው ማምረት ይቻላል" ሲሉ አክለዋል።

ክትባት ማምረት ጊዜ የሚጠይቅ ሲሆን አሁን የተከማቸው ክትባት ለአጭር ጊዜ የሚቆይ መፍትሔ ነው ብለዋል።