በኒው ዮርክ በፖሊዮ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ምልክቶች በመታየታቸው የኒው ዮርክ ገዥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በግዛቲቱ አውጀዋል።
የጤና ባለሙያዎች ከፍሳሽ በወሰዱት ናሙና የፖሊዮ ቫይረስ በኒው ዮርክና አጎራባች አካባቢዎች መኖሩ ተረጋግጧል።
የፖሊዮ ቫይረስ በኒው ዮርክ ሲገኝ በ10 ዓመት ይህ የመጀመርያው ነው።
የልጅነት ልምሻን የሚያመጣው የፖሊዮ ቫይረስ ከአሜሪካ ምድር ጨርሶ ጠፍቶ ነበር። ይህም የሆነው ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ሰፊ የክትባት ዘመቻ መደረጉን ተከትሎ ነው።
እንደ አውሮጳዊያኑ አቆጣጠር በ1979 አሜሪካ ሙሉ በሙሉ ከፖሊዮ ነጻ መሆኗን አውጃ ነበር።
የኒው ዮርክ ባለሥልጣናት እንደሚሉት የክትባት ምጣኔ በአንዳንድ አካባቢዎች ዝቅተኛ ሆኖ ነበር። አርብ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ይህን የክትባት ምጣኔ ከፍ ለማድረግ ያለመ ነው።
የልጅነት ልምሻ ወይም ፖሊዮ ፈውስ የለውም፤ ብቸኛው መከላከያ ክትባት መውሰድ ነው።
በአመዛኙ ሕጻናትን የሚያጠቃው የልጅነት ልምሻ የጡንቻ መዳከምን ያስከትላል፤ ይህ እየከፋ ሲሄድ አካል ጉዳተኛ ያደርጋል፤ ብሎም ለሞት ይዳርጋል።
የኒው ዮርክ ባለሥልጣናት አሁን የክትባት ምጣኔን ካለበት ወደ 90 ከመቶ ለማድረስ አስቸኳይ ጊዜ ማወጅ እንዳስፈለገ ተናግረዋል።
በሰሜን ኒው ዮርክ በሮክላንድ አካባቢ አንድ ፖሊዮ ያልተከተበ ግለሰብ ላይ ተህዋሲው መገኘቱን ተከትሎ በተደረገ ፍተሻ ኦሬንጅ እና ሌሎች ሦስት አካባቢዎች በሚገኙ ፍሳሾች ተህዋሲው ተገኝቷል።
የኒው ዮርክ ገዥ ካቲ አርብ ዕለት ባወጁት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የጤና ባለሙያዎች በየአካባቢው በስፋት እንዲቀሳቀሱ እና የክትባት ዘመቻ እንዲጠናከር የሚያስችል ይሆናል።
ኒው ዮርክ በቅርብ ጊዜ በጤና ጉዳይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስታውጅ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ከዚህ ቀደም በኮሮና ቫይረስ መዛመትና በዝንጀሮ ፈንጣጣ ምክንያት ተመሳሳይ አዋጅ ማወጇ ይታወሳል።
በአሜሪካ 93 ከመቶ የሚሆኑ ጨቅላዎች የፖሊዮ ክትባትን ወስደዋል።












