ኡጋንዳውያን ‘ኑሮ አስወደዱብን’ ሲሉ የሚማረሩባቸው ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በካምፓላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኡጋንዳ ለበርካታ ዓመታት በዓለም ላይ ክፍት የሆነ የስደተኞች ፖሊሲ አላቸው ከሚባሉ አገራት አንዷ ናት።
በአገሪቷ 13 የስደተኞች መጠለያ ማዕከላት የሚገኙ ሲሆን፣ በዋና ከተማዋ ካምፓላ ደግሞ ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ፣ ከሶማሊያ እና ከደቡብ ሱዳን የመጡ በርካታ ፍልሰተኞች በጊዜያዊነት እና ቋሚነት ይኖራሉ።
ካባላጋላ፣ ካንሳንጋና ቡንጋ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ኑሯቸውን ከማድረግ ባለፈ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።
በእነዚህ አካባቢዎች የመግባቢያ ቋንቋው አማርኛ እና ትግርኛ የሆነ ይመስላል።
የጋባ መንገድ
ኡጋንዳ ትልቁ የሞተር ትራንስፖርት አገልግሎት ካላቸው የምሥራቅ አፍሪካ አገራት አንዷ ናት። እነዚህ ሰውና እቃ በማጓጓዝ የሚታወቁ ተሽከርካሪዎች 'ቦዳ ቦዳ' በመባል ይጠራሉ።
ጋባ የካንሳንጋ ዋና መንገድ ነው። በዚህ መንገድ ከሁሉም አቅጣጫ የሚመጡ የ‘ቦዳ ቦዳ’ አሽከርካሪዎች መሪዎች ኢትዮጵያውንና ኤርትራውያን መልካቸውን አይተው መለየት ስለማይችሉ በትግርኛ እና አማርኛ ‘እንዴት ነህ? ሰላም ነው? ቦዳ ፈለግሽ? . . . ሲሉ ይደመጣሉ።
በተለያዩ ሁኔታዎች ውሏቸውን ያሳለፉ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ምሽት ላይ አብዛኛው ወሬያቸው በአገራቸው እና በአውሮፓ እና አሜሪካ ስላሉ ቤተሰቦቻቸው፣ ጉዞ ስለተሳካላቸው እና ስላልተሳካላቸው ስደተኞች እንዲሁም ማለቂያ የሌለው ስለሚመስለው የስደት ሕይወታቸው ነው።
ከስድስት ወራት በፊት ወደ ኡጋንዳ እንደመጣ የሚናገረው ሰለሞን ክብሮም በጋባ መንገድ 'ሰለሞን ሳሎን' የሚል ፀጉር ቤት አለው።
ሰለሞን ወደ ኡጋንዳ ከመምጣቱ በፊት መኖሪያው ሱዳን ነበር። የእርስ በእርስ ጦርነት ሲቀሰቀስ ወደ ኡጋንዳ ሸሸ።

እሱ እንደሚለው፣ ሱዳንን ለቆ በወጣበት ወቅት በስደተኛ ላይ ጾታዊ ጥቃትን እና ሌሎች ጥቃቶች ሲፈጸሙ አይቷል።
“መንገድ ላይ ብዙ ነገር አጋጥሞናል፤ በወታደሮች ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች አጋጥመውኛል። ለእነርሱ ስታገል ፊቴ ላይ ተመትቻለሁ፤ ምልክቱ ፊቴ ላይ አለ። እነሱን ይዤ ወደ ጁባ ከገባሁ በኋላ ጉዞዬን ቀጥዬ እዚህ መጥቼ ሕይወትን አንድ ብዬ ጀመርኩኝ።”
ሆኖም ከጦርነቱ በኋላ በርካታ ጓደኞቹ በገንዘብ እጦት ምክንያት ከሱዳን ለመውጣት በመቸገራቸው ምክንያት፣ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ናቸው የሚለው ሰለሞን “የሱዳን ሕዝብ መልካም ሕዝብ ነው፤ . . . ስለእነርሱ ሳስብ ይከፋኛል” ይላል።
ሆኖም ሰሎሞን ካምፓላ ላይ ባገኘው ዕድል እና የስደተኞች ፖሊሲ ደስተኛ መሆኑን ይናገራል።
“ወላሂ፤ መልካም አገር ነው። ነጻነት ያለው፣ ማን ነህ? ምንድን ነህ? የማትባልበት አገር ነው። በሱዳን ገንዘብ እያለኝ እንኳን ወረቀቶች እና ሌሎች ነገሮች ስለሚያስፈልግ መሥራት የማልችልባቸው ቦታዎች ነበሩ። እዚህ ግን ለመሥራት ዕድሉ ክፍት ነው።”
“በቀን 17 ሰዓት ሥራ ላይ ነኝ ብል ማጋነን አይሆንብኝም፤ የምተኛበት ሰዓት ጥቂት ነው” የሚለው ሰለሞን፣ በርካታ ኤርትራውያን፣ ኢትዮጵያውያን እና ሱዳናውያን ደንበኞችን ማፍራቱን ይናገራል።
ተስፋ እና ጭንቀት የተፈራረቁበት ሕይወት
ባለፉት ዓመታት በርካታ ኤርትራውያን በካምፓላ እና አካባቢው በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ሲሳተፉ የቆዩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ነዳጅ ማደያዎች፣ መድኃኒት ቤቶች፣ ክሊኒኮች፣ ሆቴሎች፣ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች፣ ሱፐርማርኬቶች እና ሌሎች ኢንቨስትመንቶች የሚያስተዳድሩ ባለሃብቶች ሆነዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ምክንያት ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ወደ ኡጋንዳ የሚመጡ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ተመሳሳይ የንግድ ድርጅቶችን በመክፈት ላይ ይገኛሉ።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ ኡጋንዳን ወደ ሦስተኛ አገር መሸጋገሪያ አድርገው የሚጠባበቁም አሉ።
በካባላጋላ ገበያ አነስተኛ ሱቅ ያላት እና ስሟን መግለጽ ያልፈለገች ኢትዮጵያዊት ከአዲስ አበባ የመጣች ሲሆን፣ “በአገሬ ያጣሁትን ሰላም ካምፓላ ላይ አግኝቻለሁ” በማለት ወደ አገሯ የመመለስ ፍልጎት እንደሌላት ትናግራለች።
“በኡጋንዳ በጣም የምወደው ነገር ቢኖር ሰላማቸው ነው፤ ማን ነሽ? ከእኔ ጐን ሱቅ አትክፈች . . . ብሎ የሚነታረክ የለም” ትላለች።
የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ከተቋጨ በኋላ በርካታ በጦርነቱ ላይ የተሳተፉ የትግራይ ወጣቶች እና ሌሎች በሕገ ወጥ መንገድ ትግራይን ለቅቀው እየወጡ ነው።
ንጉሥ ኪዳኑ በትግራይ ኃይሎች ስር በመሆን በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ቢሳተፍም፣ ከሠራዊቱ ከተሰናበተ በኋላ በቀጥታ ያመራው ወደ ኡጋንዳ ነው።
“የአገራችን ሁኔታ ነው ወደ ስደት ያመራኝ። ጥሩ ኑሮ፣ ጥሩ ሥራ እና ገቢ ነበረኝ። ከስፖርት ክለባችን ጋር [ሰባ እንደርታ] ጥሩ ሥራ ነበረኝ። ከጦርነት ስንመለስ ግን ልክ እንደሌላው ሰው ወደ ዜሮ ነው የተመለስኩት። ተመልሼ ቢዝነስ የምጀምርበት ምንም ሁኔታ አልነበረም” ይላል።
በርካታ አዲስ ስደተኞችን “አስቸጋሪ” ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ የሚገልጸው ንጉሥ፣ አብዛኞቹ ሥራ አጥ እና ውጪ ከሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው በሚላክላቸው ገንዘብ የሚተዳደሩ በመሆናቸው በገንዘብ እጥረት ምክንያት የራሳቸውን ነገር ለመፍጠር ይቸገራሉ ብሏል።
አክሎም በትግራይ ባለው ሁኔታ የተነሳ በርካታ ወጣቶች ወደ ስደት ሊያመሩ ይችላሉ የሚል ስጋት እንደሚያድርበት ተናግሯል።
“ከሊብያ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የመን ብዙ መልእክቶች ይደርሱኛል፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ የሚናገሩ፣ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ተይዘው ሲደበደቡ እና ገንዘብ ክፈሉ ሲባሉ የሚያሳይ ቪዲዮ ይላክልኛል። በዚህ ምክንያት ጭንቀት ውስጥ ነኝ” ሲል ስደት የሚቆምበት መፍትሄ እንዲበጅ ይመኛል።

‘ኑሮ አስወደዱቡን’ -- የኡጋንዳውያን እሮሮ
በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ያላት ኡጋንዳ፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ (ዩኤንኤችሲአር) “ተራማጅ ፖሊሲዎች አላት” ሲል አሞካሽቷታል።
በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች 60 በመቶ ያህሉ ደቡብ ሱዳናውያን ሲሆኑ፣ ከ3 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመጡ ናቸው።
ከ40,000 በላይ ኤርትራውያን፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እና የሌሎች ጎረቤት አገራት ስደተኞች ደግሞ በተለያዩ ደረጃዎች ይገኛሉ።
ኡጋንዳን ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ልዩ ከሚያደርጋት አንዱ፣ ስደተኞችን በቀጥታ ተቀብላ ያለምንም ጥርጣሬና ጥያቄ መጠለያ መስጠቷ ነው።
ባለፉት 20 ዓመታት ሁሉም የኡጋንዳ አጎራባች አገራት - ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን ለስደት ምክንያት የሆኑ ግጭቶች አጋጥሟቸዋል።
ኡጋንዳውያን ከእነዚህ አጎራባች አገራት ከሚመጡ ስደተኞች ጋር የተወሰነ የዘር እና የቋንቋ ትስስር ስላላቸው ከስደተኞቹ ጋር በቀላሉ ለመዋሃድ አይቸገሩም።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በርካታ ኡጋንዳውያን እንደሚናገሩት አገራቸው በቋንቋ እና ባህል ለማይዛመዷቸው ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን መጠጊያ መሆኗ ኩራት ይሰማቸዋል።
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ የመጣው የስደተኞች ቁጥር፣ የኑሮ ውድነት እያስከተለብን ነው ማለታቸው አልቀረም፤ በተለይ የቤት ኪራይ።
ኢትዮጵያውያን ሆኑ ኤርትራውያን ከአገሬው ሰዎች ጋር ለመዋሃድ የሚያደርጉት ጥረት ውስን በመሆኑ ደግሞ ቅሬታ እንደሚፈጥርባቸው በብዛት ይናገራሉ።
ፌስቶ የተባለው ኡጋንዳዊ ሹፌር፣ ለአብነት ያህል ብዙ ስደተኞች ከውጪ በሚላክላቸው ገንዘብ የሚኖሩ ናቸው። ውሎ እና አዳራቸውን የሚያይ ሰው ገንዘብ አላቸው ብሎ እንዲያስብ የሚገፋፋ በመሆኑ በተለይ የቤት አካራዮች የሚጠይቁት ገንዘብ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል ይላል።
“ለቤት ኪራይ 100 ዶላር ነበር የምንከፍለው፤ አሁን በጣም በብዛት እየመጡ ስለሆነ 300 ዶላር ወይም ከዚያ በላይ ሆኗል። ከእኛ ጋር ተዋህደው መኖር አልቻሉም፤ ይህ ደግሞ አከራዮች እንዳያዝኑላቸው ያደርጋል። ከስደተኛ ፕሮግራም በነጻ ገንዘብ እንደሚቀበሉ እና ውጪ በሚገኙ ቤተሰቦቻቸው እንደሚታገዙ ይታወቃል። ለእነሱ ይሄንን ገንዘብ ማግኘት ቀላል ነው፤ በቀላሉም እያጠፋ ነው። ይህ ለእኔ አያስደስተኝም” ሲል ይናገራል።
ይህ እንደ እኔ ባሉ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል የሚለው ፌስቶ፣ ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት ውስጥ እየጨመረ የመጣ ክስተት መሆኑን ገልጿል።
ፌስቶ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ሁሉም ‘ወደ ሀብታም አካባቢዎች በሚወስደው መንገድ’ ላይ ነው የሰፈሩት ብሎ የሚጠቅሰው የጋባ መንገድ፣ ይህም ኑሮ እንዲወደድ ምክንያት ያደርገዋል የሚል እምነት አለው።
ካንሳንጋን አልፎ እንደ ቡንጋ፣ ሙንየንኞ እና ሙዚጋ ያሉ አካባቢዎች ሀብታም እና የተሻለ ገቢ ያላቸው ሰዎች መኖሪያ አካባቢዎች ናቸው ሲል ፌስቶ ይናገራል።
“ድሮ ባለ ሁለት መኝታ ቤት 200 ዶላር ይከራይ የነበረው አሁን ከ500 እስከ 600 ዶላር ይከራያል። ሱዳናውያን እዚህ በነበሩበት ጊዜ ሁሉንም ነገር ተወዶ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ከነጻነት በኋላ [ደቡብ ሱዳን] ወደ አገራቸው ሲመለሱ ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት ተመለሰ።
“አሁን ደግሞ ብዙ ኤርትራውያን አሉ፤ በብዛትም እየመጡ ነው። መምጣታቸው አይደለም ችግሩ - ለእኔ ዓለም አንድ ናት። መንግሥታችን ዜግነት ቢሰጣቸውም ቅር አይለኝም። ነገር ግን ቢያንስ እኩል የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲኖረን የሚያግዝ አሰራር ሊኖረን ይገባል” ይላል።

ወጣቶቹ የሚመኟት ሰላም
ኡጋንዳን ቤታቸው አድርገው የተቀመጡ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ነጋቸው ውስጥ ሠርቶ መለወጥ እና ሰላም ገዝፎ ይታያል። በአገሪቱ ከምንም በላይ ሰላም መኖሩ ሁሉም ሰው በሰላምና በፍቅር እንዲኖር ምክንያት እንደሆነው ይናገራሉ።
“እዚህ ከጦርነቱ ቀጠና የመጣ ስደተኛ ጥቂት የሚባል አይደለም። እዚህ ያለው ሰላም ያስቀናል፤ ሁሌም አገሬ እንዲህ በሆነ ያስብላል። ለአገሬ የምመኘው ይሄው ነው” የሚለው ንጉሥ “በትግራይ ወጣት ወደ ሥራው ተመልሶ፣ ስደት ቆሞ በየቀኑ ከምናየው ስቃይ እንድንላቀቅና ወላጆቻችን እፎይ የሚሉበት ሁኔታ ማየት ይናፍቀኛል” በማለት ወደ ትግራይ መመለስ እንደሚፈልግ ይናገራል።
የፀጉር ባለሙያው ሰለሞን ጉዞው ቀጣይ ነው፤ ከምንም ነገር በላይ ራሴን ማስተዳደር ስላለብኝ ደግሞ ማንኛውም ዓይነት ሥራ እየሠራሁ ገንዘብ ማግኘት አለብኝ ይላል።
“ሥራ የሌለው እንደ እኔ እንዲሠራ እፈልጋለሁ፤ እዚህ አብዛኛው ስደተኛ ተኝቶ ነው የሚውለው። አንዳንዶቻችን ደግሞ ሥራን እንንቃለን። ‘የሚላክልኝ ገንዘብ’ እስኪደርስ የሚል ብዙ ነው። ነጻነት ባለበት አገር መሥራት ነው ያለብን። እኔ ይሄኛው ሥራ እንኳ ቢቀዛቀዝብኝ ጽዳት እሠራለሁ።”
ከኤርትራ ከወጣ ከአስር ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ሰለሞን በስደት መቻቻል፣ መከባበር እና ፍቅር በጣም አስፈላጊ ናቸው የሚል እምነት አለው።
“እዚህ ሁላችንም አንድ ነን፤ በስደት ላይ እናትም አባትም የለንም። ሁሉም ሰው እንዴት በፍቅር መኖር እችላለሁ? ሰላም ያምጣልኝ፤ በስደት እየተበታተነ የሚገኘው ሕዝብ ሰላም የሚያገኝበት ጊዜ እንዲመጣ ነው ምኞቴ። በስደት ብዙ ስላየሁ ሰላምን እጓጓለታለሁ” በማለት ምኞቱን ይገልጻል።












