ኡበር ሴት አሽከርካሪዎችን ለመሳብ በየሳምንቱ 20 ሰዓታት ነጻ የልጅ እንክብካቤ አዘጋጃለሁ አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪው ኡበር በዩናይትድ ኪንግደም የሴት አሽከርካሪዎቹን ቁጥር ለመጨመር በየሳምንቱ 20 ሰዓታት ነጻ የልጅ እንክብካቤ እንዳዘጋጀ አስታወቀ።
ኡበር ይህንን አበል ማንኛውም አሽከርካሪ፣የሞግዚት ወይም የማቆያ ማዕከላትን አገልግሎት በሚሰጡ መተግበሪያዎች በኩል መጠቀም እንደሚችሉ ገልጿል።
"ሴት ሹፌሮችን ወደ ኡበር መሳብ እጅጉን እንፈልጋለን" ሲሉ የኡበር ዩኬ ዋና ሥራ አስኪያጅ አንድሪው ብሬም ይናገራሉ።
ነገር ግን አሽከርካሪዎችን የሚወክለው የታላቋ ብሪታንያ ነጻ የሠራተኞች ማኅበር (IWGB) በበኩሉ ይህንን "ማንም ማየት የሚችለው ለሕዝብ ግንኙነት የሚደረግ አሳዛኝ ትርዒት" ሲል ተቃውሞታል።
"ኡበር በእርግጥ ቤተሰቦችን መደገፍ ከፈለገ ልጆቻቸውን መንከባበከብ የሚያስችላቸውን የእረፍት ጊዜ እንዲያገኙ ለአሽከርካሪዎች በቂ ገንዘብ ይከፍል ነበር" ሲል ለቢቢሲ በመግለጫው አትቷል።
"ይልቅ የኡበር የሚያሳፍር ዝቅተኛ ክፍያ አሽከርካሪዎች በመንገድ ላይ ረጅም ጊዜ እንዲያሳልፉ ያስገድዳቸዋል። ይህም ሁኔታ በበርካታ አጋጣሚዎች ግንኙነቶችን ይሸረሽራል፤ እንዲሁም የቤተሰብን ቁርኝት ያፈርሳል" ሲል አክሏል።
ኡበር ከ1 ሺህ አሽከርካሪዎች ጋር ነጻ የሕጻናት እንክብካቤን እንደሞከረ እና እጅግ በጣም ጥሩ ምላሽ እንዳገኘ ተናግሯል።
በዚህ ከተሳተፉት ውስጥ 96 በመቶ የሚሆኑት አሽከርካሪዎች ወደ ሥራ ለመግባት ቀለል አድርጎልናል ማለታቸው ተገልጿል።
ይህ የኡበር እቅድ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ያሉ ከ100 ሺህ በላይ የድርጅቱ አሽከርካሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተነግሯል።
"ልክ እንደሌሎች ሙያዎች የኡበር አሽከርካሪዎች በዋነኛነት የተያዘው በአብዛኛው በወንዶች ነው። ይህ እኛ የምንፈልገው ነገር አይደለም" ሲሉ ብሬም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኡበር የዘረጋው ነጻ የሕጻናት እንክብካቤ መጀመሪያ ላይ ከአዳዲስ ይልቅ ነባር አሽከርካሪዎች ይጠቀማሉ ብለው እንደሚጠብቁ የተናገሩት የኡበር ዩኬ ዋና ሥራ አስኪያጅ "ነገር ግን በዋነኝት አሽከርካሪዎች ይህንን የመጠቀም ልምድ እንዲያዳብሩ ማድረግ ነው" ብለዋል።
ኡበር ዩኬ ይህንን እቅድ በአውሮፓውያኑ 2025 ሊተገብረው ያቀደ ሲሆን፤ የማራዘሙ ሁኔታ በጊዜ ሊታይ እንደሚችልም ብሬም አመልክተዋል።
ድርጅቱ ይህ እርምጃው በቅርብ ወራት ውስጥ ፍትሃዊ ያልሆነ ክፍያ ነው በሚል ሥራ የማቆም አድማ የመቱ አሽከርካሪዎችን ለማረጋጋት እንደሚያግዝ ተስፋ ያደርጋል።
በጥቅምት ወር የግላስጎው ኡበር አሽካርካሪዎች ኡበር የዋጋ ጭማሬ በደንበኞች ላይ ቢያደርግም ለአሽከርካሪዎቹ የሚደረገው ክፍያ ቀንሷል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አሽከርካሪዎቹ ቤተሰቦች ቢኖራቸውም ረጅም ሰዓት ለመስራት ተገደናል በሚል ተቃውሞ የስራ ማቆም አድማ በጥር ወር አድርገዋል።
ብሬም በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት አሽከርካሪዎች ኡበር የሚወስደውን ታሪፍ ጋር ሲነጻጻር ምን ያህል ገንዘብ እንዳገኙ ሳምንታዊ መረጃ ማየት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
አክለውም በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት እንቅስቃሴዎች መቆማቸውን ተከትሎ አሽከርካሪዎች ያልተለመደ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ነበር ፤ ለዚህም የነበረው ፍላጎት ከነበረው የተሽካርካሪ አቅርቦት በላይ በመሆኑ ነው።
"አሁን ወደተለመደው ሁኔታ ተመልሰናል። ምናልባት ይህ አሽከርካሪዎች በዚያ ወቅት የገጠማቸው ሁኔታ ላይ ተጽእኖ ያደርጋል" ብለዋል።












