ዩክሬን ምን ያህል የእህል ምርት ለዓለም ገበያ ታቀርባለች?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዩክሬን ጥቁር ባሕር ላይ ካሏት ወደቦቿ እህል ለዓለም ገበያ እንድታቀርብ የሚረዳትን ስምምነት መሰረዟን ሩሲያ አስታውቃለች።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ 2014 ዓ.ም. በሞስኮ እና ኪዬቭ መካከል ተደርሶ የነበረው ስምምነት ዩክሬን ጥሬ እህሎች እና ምግቦችን ለዓለም ገበያ እንድታቀርብ አስችሏት ነበር።

ይሁን እንጂ ሞስኮ ይህ ስምምነት እንዲገታ መወሰኗ በዓለም የምግብ ገበያ ዋጋ ዳግም ከፍ እንዲል ምክንያት ሆኗል።

ከጦርነቱ ወዲህ ምን ያክል እህል ከዩክሬን ተልኳል?

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ የሩሲያ ባሕር ኃይል ከዩክሬን የጥቁር ባሕር ወደቦች እንቅስቃሴ እንዳይኖር አድርጎ ነበር።

ይህም ዩክሬን ወደተቀረው ዓለም ለመላክ አከማችታው የነበረው 20 ሚሊዮን ቶን እህል እና ሌሎች እንደ በቆሎ እና የሱፍ አበባ የዘይት ምርቶች ባሉበት እንዲቆዩ ምክንያት ሆኖ ነበር።

በዓለማችን ከፍተኛ መጠን ያለው ምግብን ወደ ውጪ ከሚልኩ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ዩክሬን እንደመሆኗ ጦርነቱ በዓለም አቀፍ ገበያ የምግብ ዋጋን ከፍ አድርጎታል።

ሁለቱ አገራት ሐምሌ አጋማሽ 2014 ዓ.ም. ላይ መንቀሳቀሻ አጥቶ የነበረው እህል ለገበያ እንዲቀርብ ከስምምነት መድረሳቸውን ተከትሎ፣ ባለፉት ወራት ከ9.3 ሚሊዮን ቶን በላይ ምግብ በጥቁር ባሕር በኩል መጓጓዙን የተባበሩት መንግሥታት አሃዝ ያሳያል።

ዩክሬን በሩሲያ ወረራ ሳይፈጸምባት በፊት በወር አምስት ሚሊዮን ቶን ምግብ ትልክ ነበር። ባለፈው ወር ለገበያ የቀረበው ግን 4 ሚሊዮን ቶን እህል ነበር።

ዩክሬን ለዓለም ገበያ የምትልከው የእህል መጠን ከቀነሰባቸው ዋነኛ ምክንያቶች መካከል ኩባንያዎች እቃ ጫኛ መርከቦቻቸውን ወደ ጥቁር ባሕር የመላክ ፍላጎት ስለሌላቸው ነው።

“መርከባቸው በፈንጅ ሊመታ ወይም በሩሲያ ጥቃት ሊሰነዘርበት እንደሚችል ስጋት አላቸው” ይላሉ የባሕር ትራንስፖርት ጉዳዮችን የሚዘግበው ሎይድስ ሊስት ጋዜጠኛ ዴቪድ ኦስለር።

ሩሲያ ባሳለፍነው ቅዳሜ ጥቅምት 19/2015 ዓ.ም. ከዩክሬን ጋር ደርሳ ከነበረው ስምምነት መውጣቷ እና ከዩክሬን ወደቦች ጭነት የማስወጣት ሥራዎች መታገዳቸውን አስታውቃለች።

ሩሲያ ይህን ትበል እንጂ እህል የጫኑ መርከቦች ከሰኞ ጥቅምት 21 ጀምሮ ከዩክሬን ወደቦች መንቀሳቀስ ጀምረዋል።

እህሉ የተላከው ወደየትኞቹ አገራት ነው?

በተባበሩት መንግሥት አማካይነት ከዩክሬን የሚነሳው እህል መዳረሻውን በዓለማችን ወዳሉ ደሃ አገራት እና የረሃብ አደጋ ወደተጋረጠባቸው አካባቢዎች ነው።

ይሁን እንጂ ባለፉት ሦስት ወራት ከፍተኛው መጠን ያለው የዩክሬን እህል ከሄደባቸው አገራት መካከል ስፔን፣ ቱርክ፣ ጣሊያን፣ ቻይና እና ኔዘርላንድስ ይጠቀሳሉ።

ከጦርነቱ በፊት ከፍተኛ መጠን ያለውን የዩክሬን እህል የሚያስገቡት ሦስት አገራት ግብፅ፣ ኢንዶኔዢያ እና ባንግላዴሽ ነበሩ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፉት አራት ሳምንታት ከዩክሬን ከተላከው እህል መካከል 30 በመቶ የሚሆነው አነስተኛ ገቢ ወዳላቸው አገራት ነው ብሏል።

44 በመቶ የሚሆነው ደግሞ የተላከው ከፍተኛ ገቢ ወዳላቸው አገራት ነው።

የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በመላው ዓለም የምግብ ዋጋ ላይ ጭማሪ ታይቶ ነበር። ሁለቱ አገራት ግን አህል የጫኑ መርከቦች ያሚያልፉበት መተላለፊያ እንዲኖር መስማማታቸው የምግብ ዋጋ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኖ እንደነበር የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት አሃዝ አሳይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በመርከብ የተጫነ እህል

መተላለፊያዎቹ ምን ያህል ደኅንነታቸው የተጠበቀ ነው?

እህል የጫኑ መርከቦች ከኦዴሳ እና ከሌሎች አጎራባች ወደቦች እስከ ኢስታንቡል ሰርጥ ድረስ መተላለፊያ ኮሪዶር እንዲፈጠርላቸው ሩሲያ እና ዩክሬን ከቱርክ ጋር ተፈራርመው ነበር።

ይህ ኮሪዶር 310 ኖውቲካል ማይልስ (570 ኪሎ ሜትር) ገደማ ርዝመት እና 3 ኖውቲካል ማይልስ ስፋት አለው።

በስምምነቱ መሠረት በዩክሬና ጦር በፈንጂ በታጠረ መስመር ውስጥ የዩክሬን መርከቦች እህል ይዘው ይወጣሉ። ቱርክ ደግሞ በሩሲያ ጥያቄ መርከቦቹ ወታደራዊ ቁሶችን አለመጫናቸውን በፍተሻ ታረጋግጣለች።

ይህ ስምምነት ለ120 ቀናት የተፈረም ነበር። ስምምነቱ በአዲስ ውል ይራዘማል የሚል ተስፋ ተጥሎ የነበረ ቢሆንም፣ ሩሲያ የውሉን ተፈጻሚነት አግዳለች።

በምግብ ዋጋ ላይ ምን ለውጥ አለ?

ሩሲያ ስምምነቱን ካገደች በኋላ የግብይት ዋጋ 5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። የበቆሎ ዋጋም 2 በመቶ ጨምሯል።

በአሁኑ ወቅት ነጋዴዎች ሩሲያ ተጨማሪ ክልከላዎችን ልትወስድ ትችላለች በሚል ምርት ገዝተው እያከማቹ እንደሆነ ይታመናል።

ሩሲያ ይህን ውል ውድቅ ያደረገችው መርከቦቹ የሚተላለፉበትን ኮሪዶር “ደኅንነት ማረጋገጥ አይቻለኝም” በሚል ምክንያት ነው።

ሩሲያ በቅርቡ በሴቫስቶፖል ወደብ ላይ ለደረሰው ጥቃት ይህን የመተላለፊያ ኮሪዶር የሚጠቀሙ መርከቦች ተሳትፈውበታል ብላለች። የመንግሥታቱ ድርጅት በበኩሉ በሩሲያው ሴቫስቶፖል ወደብ ላይ ጥቃት ሲሰነዘር በመተላለፊው ላይ መርከብ አልነበረም ይላል።

ሩሲያ ይህን ስምምነት ካገደች በኋላም ኩባንያዎች የደኅንነት ማረጋገጫዎችን ከቱርክ፣ ከዩክሬን እና ከተባበሩት መንግሥታት ካገኙ በኋላ መተላለፊያ መስመሩን በመጠቀም ላይ ይገኛሉ።

ዩክሬን በጥቁር ባሕር በኩል ብቻ ነው መላክ የምትችለው ?

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፍታ ወደቦቿን ዝግ ማድረጓን ተከትሎ ኪዬቭ በየብስ የግብርና ምርቶቿን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ጥረት ስታደርግ ነበር።

ኪዬቭ በተቻላት አቅም ከባድ መኪናዎች እና ባቡሮችን ጥቅም ላይ ስታውል ቆይታለች።

ከወረራው በኋለም የአውሮፓ ኅብረት በባልቲክ ባሕር ከሚገኙ ወደቦች እና ከኮንስታንታ ወደብ እህል ለገበያ እንዲቀርብ መንገድ ቀይሶ ነበር። ይህ ሁሉ ጥረት ግን የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም።

የመንገድ መሠረተ ልማት አለመኖር እና የባቡር አቅም ማነስ ዩክሬን ከእህል ምርቷ ለዓለም ገበያ ማቅረብ የቻለችው 10 በመቶውን ያህል ብቻ ነው።