በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የአሜሪካ ዶላር ከሌሎቹ ገንዘቦች ልቆ ለምን ጠንካራ ሆነ?

ዶላር የያዘ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ዶላር ካለፉት ሁለት አስር ዓመታት ወዲህ ከሌሎች ዋና ዋና የመገበያያ ገንዘቦች ጋር ሲነጻጸር ጠንካራ ሆኗል።

ይህ ማለት ዶላር በጣም ውድ ሆኗል ማለት ነው። ዶላር ቀደም ሲል መግዛት ከሚችለው በላይ የብሪታኒያ ፓውንድ፣ የአውሮፓውን ዩሮ ወይም የጃፓንን የን ይገዛል ማለት ነው። ይህም በዓለም ዙሪያ ያሉ ድርጅቶችን እና ግለሰቦችንም ይነካል።

ዶላር ምን ያህል ጠንካራ ነው?

የዶላር ጥንካሬን የሚያመለክተው ጠቋሚ (ዲኤኬስዋይ) እንደሚያሳየው የአሜሪካን ዶላር ከሌሎች ስድስት ዋና ዋና ዓለም አቀፍ የመገበያያ ገንዘቦች ማለትም ከዩሮ፣ ከፓውንድ እና ከየን ጋር ሲነጻጸር በዚህ የፈተንጆች ዓመት በአማካይ በ15 በመቶ አድጓል።

በዚህ መለኪያ መሠረት ዶላር በ20 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የጥንካሬ ማማ ላይ ይገኛል።

ለመሆኑ ዶላር ለምን ጠንካራ ሆነ?

የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል ዘንድሮ ተደጋጋሚ የወለድ ጭማሪ አድርጓል። ይህም ብድርን የማያበረታታ ነው። ምክንያቱም በተጣለው ወለድ ምክንያት ተበዳሪዎች የሚመልሱት ገንዘብ ከፍተኛ ይሆናል።

ሌላም ጥቅም አለው። ከአሜሪካ መንግሥት ቦንድን በማቅረብ በመበደር ለወደፊት በወለድ ለመመለስ ቃል ስለሚገባ፣ ይህ ለባለሀብቶች ይበልጥ የሚስብ አስተማማኝ ኢንቨስትምንት ነው።

ቦንድ መንግስታት ገንዘብ የሚበደሩበት አንድ መንገድ ነው። ወደፊትም ወለድ ጨምረው ይከፍላሉ። ስጋት የሌለበት ዘርፍ መሆኑም ይነገርለታል።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ብቻ የውጭ ባለሃብቶች በ10.2 ቢሊዮን ዶላር የአሜሪካ መንግሥት ቦንድ ገዝተዋል። አሁን ድርሻቸው 7.5 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል።

ባለሃብቶች እነዚህን ቦንዶች ለመግዛት ዶላር መግዛት ይጠበቅባቸዋል። ይህ ፍላጎታቸው ደግሞ የዶላርን ዋጋ ያንረዋል።

ባለሃብቶች ዶላር ለመግዛት ሌሎች ምንዛሬዎችን ሸጠው ዶላር ይሸምታሉ። በሂደቱ የዶላርን አቅም ሲያጠነክረው፣ የሚሸጡትን ሌሎቹን የመገበያያዎች ገንዘቦች ዋጋቸውን ይቀንሰዋል።

በቅርቡ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ከፍተኛ የታክስ ቅናሽ አደረገ። ይህም ፓውንድ ከዶላር ጋር ሲነጻጸር እንዲያሽቆለቁል አስገደደው።

የዓለም ኢኮኖሚ ጫና ውስጥ ሲገባ ኢንቨስተሮች ዶላር የመግዛት ዝንባሌ አላቸው። ምክንያት ከተባለ የደግሞ አሜሪካ ምጣኔ ሃብት ምንዛሪዋን ችግር ሲኖር “መሸሸጊያ” አድርጎታል። ይህም የዶላርን ዋጋ ከፍ ያደርገዋል።

በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የጋዝ ዋጋ በመጨመሩ በአውሮፓ እና በእስያ የሚገኙ አገራት ምጣኔ ሃብት እየተፈተነ ነው።

በነዳጅ ዋጋ መጨመር አሜሪካ ብዙም አልተጎዳችም። ባለፉት ስድስት ወራት ኢኮኖሚዋ ቢቀዛቀዝም ድርጅቶች አሁንም ሠራተኞቻቸውን አላባረሩም። ይህም ያላቸውን መተማመን እንደማሳያ ምልክት ተደርጎ ይቆጠራል።

የዶላር መወደድ ከሌላ ዓለም ገንዘባቸውን የሚያገኙ እንደ አፕል እና ስታርባክስ ያሉ የአሜሪካ ኩባንያዎችን እየጎዳ ነው።

በዚህም ሳቢያ ስታንዳርድ ኤንድ ፑርስ በሚባለው የአክሲዮን ገበያ የሚገበያዩ የአሜሪካ ኩባንያዎች ከዓለም አቀፍ ሽያጮች 100 ቢሊዮን ዶላር ሊያጡ ይችላሉ ተብሏል።

ዶላር የሚቆጥር ሰው እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዶላር በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

ደካማ ምንዛሪ ያላቸው ሃገራት ከጠንካራ ዶላር ሊጠቀሙ ይችላሉ። ለአሜሪካ የሚሸጡትን ዕቃዎችና አገልግሎቶች ርካሽ በማድረግ ወጪ ንግዳቸውን በማሳደግ ይጠቅማቸዋል።

በተቃራኒው ደግሞ ከአሜሪካ የሚያስገቧቸው ዕቃዎች የበለጠ ውድ ይሆናሉ ማለት ነው።

ነዳጅ የሚሸጠው በዶላር ነው። የዶላር ዋጋ በመጨመሩ በብዙ የዓለም አገራት የነዳጅ ዋጋ ከፍ ብሏል።

ኬንያን በምሳሌነት እናንሳ። የኬንያ ሽሊንግ ከዶላር ጋር ሲነፃፀር የመግዛት አቅሙ ከዚህ በፊት ባልታየ ደረጃ ዝቅ ብሏል። እአአ ከ2022 መጀመሪያ ጀምሮ የነዳጅ ዋጋ በ40 በመቶ ጨምሯል።

ዶላር በተነጻጻሪነት የተረጋጋ የመገበያያ ገንዘብ ነው። በዚህ ምክንያት ብዙ አገራት እና ድርጅቶች ብዙ ጊዜ ገንዘብ የሚበደሩት ከራሳቸው መገበያያ ገንዘብ ይልቅ በአሜሪካ ዶላር ነው።

የዶላር ዋጋ ሲጨምር ዕዳውን በአገር ውስጥ ምንዛሪ ለመክፈል በጣም ውድ ይሆናል።

ጠንካራ በሆነው ዶላር ክፉኛ ከተመቱት አገራት አንዷ አርጀንቲና ናት።

በዚህም ምክንያት የውጭ ምንዛሪ ክምችቷን ለመጠበቅ ቅንጡ መርከቦችን እና ውስኪን ጨምሮ የተለያዩ ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦችን ለጊዜው አግዳለች።

ነዳጅ የምትቀሳ ሠራተኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዶላር ወደ አገራቸው የሚልኩ ሠራተኞችስ?

በየዓመቱ በውጭ አገራት የሚሠሩ ሰዎች ወደ 625 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ወደ አገራቸው ይልካሉ። ይህ ገንዘብ ለሃገራቸው ምጣኔ ሃብት ወሳኝ ሊሆን ይችላል።

በዩናይትድ ስቴትስ ያሉ የውጭ አገር ሠራተኞች በዓመት 150 ቢሊየን ዶላር ወደ አገራቸው ይልካሉ።

ከዚህ ውስጥ ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆነው ወደ ሜክሲኮ፣ 16 ቢሊዮን ዶላሩ ወደ ቻይና፣ 11 ቢሊየን ዶላር ወደ ሕንድ እና 11 ቢሊዮን ዶላር ወደ ፊሊፒንስ እንደሚላክ ይታሰባል።

የአሜሪካ ዶላር ሲጠነክር ብዙ የሌሎች ሃገራት መገበያያ ገንዘቦችን መግዛት ይችላል። ይህም በዶላር ገንዘብ የተላከላቸውን ተጠቃሚ ያደርጋል።

በርናዴት ክሩዝ ከሦስት ልጆቿ ጋር በፊሊፒንሷ ሳን ሆሴ ከተማ ትኖራለች።

የቤተሰቡ ህይወት የተመሠረተው ላለፉት 18 ዓመታት በነርስነት የሚሠራው ባለቤቷ ፍሬድ ከኒውዮርክ በሚልከው ዶላር ነው።

ዶላር ከፊሊፒንስ ፔሶ ጋር ሲነጻጸር በ13.5 በመቶ ጨምሯል። “በፊሊፒንስ ምግብ እና አገልግሎቶችን ጨምሮ ሁሉም ምርቶች በዋጋ እየጨመሩ ነው” ትላለች በርናዴት።

“ዶላር መወደዱ የምፈልገውን ነገር እንድገዛ እየረዳኝ ነው። ባለቤቴ በውጭ አገር የሚከፈለውንም መስዋዕትነት የበለጠ ጠቃሚ ያደርገዋል።”

ከዶላር መወደድ ጋር በተያያዘ አገራት ምን እየሠሩ ነው?

ብዙ አገራት የወለድ መጣኔን በመወሰን የመገበያያ ገንዘባቸውን ዋጋ ለማሳደግ እየሞከሩ ነው።

በአርጀንቲና የማዕከላዊ ባንክ የወለድ ምጣኔ 69.5 በመቶ ነው። በጋና 19 በመቶ፣ በናይጄሪያ 14 በመቶ እና በብራዚል 13.75 በመቶ ነው።

የወለድ መጣኔ ሲጨምር የንግድ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ገንዘብ ለመበደር የበለጠ ውድ ይሆንባቸዋል ማለት ነው።

ድርጅቶች ለማደግ ሊቸገሩ፣ ሠራተኞችንም ሊያባርሩ ይችላሉ። ቤተሰቦች ወጪያቸውን እንዲቀንሱም ይገደዳሉ።

ይህ ደግሞ የአገራት ምጣኔ ሃብት እንዲወድቅ ሊያደርግ ይችላል።