በሕንድ ሃይማኖታዊ ፌስቲቫል ላይ ከ110 በላይ ሰዎች ተረጋግጠው ሞቱ

በሰሜናዊ ሕንድ በሃይማኖታዊ ፌስቲቫል ላይ ቢያንስ 116 ሰዎች ተረጋግጠው መሞታቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
አደጋው ያጋጠመው አትራ ፕራዴሽ ግዛት ሳትሳንግ በተባለ የሂንዱ እምነት ተከታዮች ሃይማኖታዊ ፌስቲቫል ላይ መሆኑን የፖሊስ ኃላፊ ሻላብህ ማቱር ተናግረዋል።
ከሟቾቹ መካከል ሴቶች እና ሕጻናት እንደሚገኙበት ተገልጿል።
እስካሁን ድረስ የመረጋገጥ አደጋው እንዴት ሊከሰት እንደቻለ ግልጽ ባይሆንም የዓይን እማኞች ፌስቲቫሉ የተካሄደበት ስፍራ መውጫ በጣም ጠባብ መሆኑን እና አቧራማ አውሎ ንፋስ ግራ መጋባት እና ድንጋጤ ፈጥሮ ሰዎች መሯሯጥ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ከአንደጋው የተረፈ አንድ ግልሰብ ለቢቢሲ ሲናገር፤ “ሁሉም ነገር በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነበር። ድንገት ጩኅት ሰማሁ። መሯሯጥ እና መረጋገጥ ተፈጠረ” ብሏል።
ሌላ የፌስቲቫሉ ተሳታፊ ደግሞ የነበረውን ሁኔታ ስትናገር፤ “ስነ-ስርዓቱ እንዳበቃ ሰዎች በፍጥነት ለመውጣት ሲሞክሩ መገፈታተር እና መረጋገጥ ተፈጠረ። በጣም ብዙ ሰዎች ቱቦ ውስጥ ወድቀው ሕይወታቸው አልፏል” ስትል ተናግራለች።
እስካሁን የሟቾች ቁጥር 116 ነው የተባለ ቢሆንም በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የአትራ ፕራዴሽ ግዛት የፖሊስ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከአደጋው በኋላ ጉዳት የደረሰባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በደረቅ ጭንት መኪኖች እና በባለ ሦስት እግር ተሸከርካሪዎች ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎች አሳይተዋል።
በሆስፒታሎች በራፍ ላይ እንዲሁ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች እስክሬን በአንድ ላይ ተከማችቶ እና የተጎጂዎች ቤተሰቦች እርዳታ ሲጠይቁ ታይተዋል።
የፖሊስ ኃላፊው ስነ-ስርዓቱ የተካሄደበት ስፍራ ከአቅም በላይ በርካታ ሰዎችን ማስተናገዱን ተናግረው ክስተቱን ተከትሎ ምርመራ መጀመሩን ተናግረዋል።
አደጋውን ተከትሎ አድራሻቸው የጠፉ ሰዎች ቁጥርም በመቶዎች እንደሚቆጠር ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።
በሕንድ በሃይማኖታዊ ፌስቲቫል ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ሰዎች ተረጋግጠው ሲሞቱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
እአአ 2013 በማደሃያ ግዛት በሂንዱ ፌስቲቫል ላይ 115 ሰዎች ተረጋግጠው ሞተው ነበር።












