ዲፕፌክ ምሥሎች ቴይለር ስዊፍትን ‘እርቃኗን’ ካሳዩ በኋላ ሕግ እንዲወጣ ተጠየቀ

ቴይለር ስዊፍት

የፎቶው ባለመብት, REUTERS

ዝነኛዋ ድምጻዊት ቴይለር ስዊፍት ‘እርቃኗን’ የሚያሳዩ በዲፕፌክ የተሠሩ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ መዘዋወራቸውን ተከትሎ፣ የአሜሪካ ፖለቲከኞች አዲስ ሕግ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የእውነት የሚመስሉ ሐሰተኛ ምሥሎችና ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በዲፕፌክ (deepfake) መተግበሪያ እየተሠሩ እንዳይሰራጩ ለማድረግ ድርጊቱን እንደ ወንጀል ወስዶ የሚወጣ ሕግ እንዲወጣ ነው የጠየቁት።

የቴይለር ሐሰተኛ ምሥሎች በኤክስና ቴሌግራም ላይ ነበር የተለቀቁት።

ኤክስ ምሥሎቹን አስወግዶ ምሥሎቹን ባሰራጩ ላይ “ተገቢውን እርምጃ” እንደወሰደ ገልጿል።

ኤክስ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነም አክሏል።

የቴይለር የዲፕፌክ ምሥሎች ከመጥፋታቸው በፊት 47 ሚሊዮን ጊዜ ታይተዋል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎች (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) በመጠቀም የሚፈጠሩ ዲፕፌክ ምሥሎች ወይም ቪድዮዎች መነጋገሪያ ከሆኑ ቆይቷል።

እአአ በ2023 የተሠራ ጥናት ዲፕፌክ በ550% እንደጨመረ ይጠቁማል።

በአሜሪካ ዲፕፌክ መፍጠርን ወይም ማጋራትን እንደ ወንጀል የሚያይ ሕግ የለም።

በዩናይትድ ኪንግደም ዲፕፌክ የሆኑ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ምሥሎች ወንጀል ተብለው ተደንግገው በ2023 ተከልክለዋል።

የአሜሪካ የምክር ቤት ተወካይ የሆኑት ዴሞክራቱ ጆ ሞራሌ፣ የቴይለር ዲፕፌክ ምሥሎች “እጅግ አስቀያሚ ናቸው” ብለዋል።

ዲፕፌክን የሚከለክል ሕግ ረቀቂም አቅርበዋል።

ወሲባዊ ይዘት ያለው ዲፕፌክ መሥራትና ማጋራትን በወንጀል የሚያስቀጣ ያደርገዋል።

እንዲህ ያሉ ምሥሎችና ተንቀሳቃሽ ምሥሎች “የማይሽር የስሜት ጠባሳ ያሳድራሉ። የገንዘብ ጉዳት፣ ስም ማጥፋትም ያደርሳሉ። ዋነኛ ተጎጂ ደግሞ ሴቶች ናቸው” ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ከሚሰራጩ ዲፕፌኮች አብዛኞቹ ወሲባዊ ይዘት አላቸው። ሴቶች ላይ ያነጣጠሩት 99 በመቶ ናቸው።

የዴሞክራት የምክር ቤት አባል ይቬት ዲ ክላርክ “ቴይለር ስዊፍት የገጠማት አዲስ ነገር አይደለም። ለዓመታት ሴቶች በቴክኖሎጂ ኢላማ ተደርገዋል” ብለዋል።

ሪፐብሊካን የምክር ቤት አባል ቶም ኪን ጁንየር ዲፕፌክ በፍጥነት እያደገና በርካሽ እየተሠራ መምጣቱ አስጊ መሆኑን ተናግረዋል።

“ቴይለር ስዊፍት ላይም ይድረስ ሌላ ወጣት ላይም ይድረስ ዜጎችን መከላከል አለብን” ብለዋል።

ቴይለር ስለ ምሥሎቹ በአደባባይ አስተያየት አልሰጠችም። ሆኖም ዴይሊ ሜል እንደዘገበው የሕዝብ ግንኙነት ክፍሏ ክስ ለመመሥረት አስቧል።