ናይጄሪያ ውስጥ በትምህርት ቤት ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ 17 ሕጻናት ሞቱ

ለ17 ሕጻናት ሞት ምክንያት በሆነው እሳት የተቃጠለው ትምህርት ቤት

የፎቶው ባለመብት, Yahaya Mahi

የምስሉ መግለጫ, ለ17 ሕጻናት ሞት ምክንያት በሆነው እሳት የተቃጠለው ትምህርት ቤት
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሰሜናዊ ናይጄሪያ በሚገኝ እስላማዊ ትምህርት ቤት በደረሰ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ቢያንስ 17 ሕጻናት መሞታቸውን ባለሥስልጣናት አስታወቁ።

ሌሎች በርካታ ተማሪዎች በአደጋው የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው ለህክምና ዛምፋራ ግዛት ውስጥ ካውራን ናሞዳ በምትባለዋ ከተማ ወደሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ተወስደዋል።

እሳቱ ማክሰኞ ምሽት ላይ ከትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ከሚገኝ ቤት ተነስቶ ወደ ወደ ትምህርት ቤቱ በተዛመተበት ጊዜ ጉዳት የደረሰባቸው ዕድሜያቸው ከ10 አስከ 16 ዓመት የሚሆናቸው ሕጻናት እንቅልፋ ላይ እንደነበሩ ይታመናል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት በአደጋው የተጎዱት እርዳታ እንዲያገኙ ጥረት እያደረጉ የእሳቱንም መንስኤ ለማወቅ ምርመራ እያካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የእሳት አደጋው መከሰቱን ተከትሎ ባለሥልጣናት እና የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪ ሠራተኞች ከስፍራው በደረሱበት ጊዜ እሳቱ በትምህርት ቤቱ ላይ ከፍታ ጉዳትን አድርሶ እንደነበር ተገልጿል።

የአካባቢው ፖሊስ ኃይል ቃል አቀባይ ያዚድ አቡበከር እንዳሉት ሕብረተሰቡ በአደጋው ሕይወታቸው ላለፈው ሕጻናት ትናንት ረቡዕ ከሰዓት በኋላ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውን ፈጽሟል።

ትምህርት ቤቱ የሚገኝበት ቦታ እሳቱን ለመቆታጠር የተደረገውን ጥረት አስቸጋሪ እንዳደረገው በስፍራው የነበረው የዓይን እማኝ ያሃያ ማሂ ለቢቢሲ የሃውሳ ቋንቋ አገለግሎት ተናግሯል።

"የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች እርዳታ ለመስጠት በጊዜ ቢመጡም ወደ ትምህርት ቤቱ የሚወስደው ጠባብ መንገድ ወደ አደጋው ስፍራ ለመድረስ አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጥሮባቸው ነበር" ብሏል።

የአካባቢው ባለሥልጣን ማንኒር ሃይዳራ እንዳሉት ይህንን አደጋ ተከትሎ ሌሎች እስላማዊ ትምህርት ቤቶች ለእሳት አደጋ ተጋላጭ አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።

"እንዲህ ዓይነት አደጋ በድጋሚ እንዳይከሰት ለመከላከል እርምጃዎችን እንወስዳለን" በማለት የአካባቢው አስተዳደር አስፈላጊውን ሁሉ እንሚኣደርግ አመልክተዋል።

የአደጋው ሰላባዎች ከሆኑት መካከል የአንዱ አባት ለቢቢሲ ሃውሳ እንደተናገሩት ክስተቱ በፈጠረው ሐዘን በጣም ቢጎድም በፈጣሪ ላይ ያላቸው እምነት መጽናናት እንደሆናቸው ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቱ ላይ አደጋው በደረሰበት ጊዜ በውስጡ ወደ 100 የሚጠጉ ተማሪዎች እንደነበሩ እንሚታመን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

ብዙዎቹ ተማሪዎች የዛምፋራ ግዛት ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ በሆነችው በካውራ ናሞዳ ዙሪያ ከሚገኙ የተለያዩ መንደሮች የመጡ መሆናቸው ተነግሯል።