ጃፓን ምጣኔ ኃብቷን ለማሳደግ ወጣቶች መጠጥ እንዲጠጡ ዘመቻ ጀመረች

መጠጥ እየጠጡ ያሉ ወጣቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ወጣቱ ዜጋ መጠጥ አልጠጣ ያላት ጃፓን መጠጥን ለማበረታት ባለሥልጣናቱ አዲስ ዘመቻን ከፍተዋል።

ወጣቱ ትውልድ ከወላጆቻቸው ባነሰ ሁኔታ አልኮል እንደሚጠጡ መረጃዎች የጠቆሙ ሲሆን ይህም በአገሪቱ ሴክ ተብሎ ከሚጠራውን የሩዝ ወይን የሚገኘውን ግብር በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቶታል ተብሏል።

ይህንንም ለመቀልበስ የአገሪቱ የግብር ኤጀንሲ ብሔራዊ ዘመቻን ጀምሯል።

ዘመቻው “ሴክ ቪቫ” ይሰኛል፤ መጠጥን የበለጠ ለወጣቱ አጓጊ ለማድረግ እና በዚህ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግም አቅዷል።

በዚህም ዘመቻ ከ20 እስከ 39 ዓመት የሆናቸውን ወጣቶች የሚያሳትፍ ውድድር ተዘጋጅቷል።

ወጣቶቹ የጃፓን መጠጥ የሆኑትን ሴክ፣ ሾቹ፣ ዊስኪ፣ ቢራና ወይን ላይ ያላቸው የቢዝነስ ሐሳቦች እንዲያካፍሉም ተጠይቀዋል።

የግብር ባለሥልጣናቱን በመወከል ውድድሩን እያዘጋጀ ያለው ድርጅት እንዳለው በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የመጠጥ ሽያጭ መቀነሱን አስታውቋል።

ለዚህም የተጠቀሱት ምክንያቶች በወረርሽኙ ምክንያት አዲስ የኑሮ ዘይቤ በመምጣቱ በተለይም የአገሪቱን መጠጥ በመግዛት የአንበሳ ድርሻ የነበረው በዕድሜ ተለቅ ያለው ዜጋም መጠጥ በመቀነሱ ነው ተብሏል።

ተወዳዳሪዎች የማስተዋወቂያ ሐሳቦችን፣ የምርት ስያሜዎች እንዲሁም ላቅ ያሉ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አዘጋጁ ተብለዋል።

የጃፓን መገናኛ ብዙኃን ምላሹ የተደበላለቀ ነው ብሏል። በተለይም ጤናማ ያልሆነ ልማድን ለማሳደግ በተከፈተው ዘመቻ ላይ ትችቶችና ወቀሳዎች እየተስተናገዱ ነው።

ነገር ግን ሌሎች ያልተለመዱ ሐሳቦችንም በኢንተርኔት እያጋሩ ይገኛሉ። ለምሳሌም ያህል ታዋቂ ተዋናዮች በዲጂታል ክለቦች እንደ አስተናጋጅነት የሚሰሩበት ምናባዊ እውነታዎችንም ፈጥረው በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።

ተወዳዳሪዎች ሐሳቦቻቸውን ለማቅረብ እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ ቀነ ገደብ ተሰጥቷቸዋል። የዘመቻው ድረ-ገጽ የጃፓን የአልኮል ገበያ እየቀነሰ መምጣቱን እና ለዚህም የአገሪቱ የዕድሜ ባለጸጎች ሞት እና የወሊድ መጠን ማሽቆልቆል ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ብሏል።

ከግብር ኤጀንሲ የተገኙ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአውሮፓውያኑ 1995 ይጠጣ ከነበረው 100 ሊትር በሳምንት በ2020 ወደ 75 ሊትር ቀንሷል።