አገራት ለአየር መንገዶቻቸው መሪነት የሚፈልጓቸው ‘የአፍሪካ አቪየሽን አባት’ የሚባሉት አቶ ግርማ ዋቄ ማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, ETHIOPIAN/FB
በንጉሡ ዘመን አቶ ግርማ ዋቄ 4 ኪሎ የሒሳብ ተማሪ ነበሩ። ኳስ መጫወት ነፍሳቸው ነበር።
ከዕለታት አንድ ቀን የኳስ ጓደኞቻቸው “ና ቦሌ ደርሰን እንምጣ” አሏቸው።
ግርማ ዋቄ “ለምን?” ሳይሉ ተከተሏቸው።
ለካንስ ጓደኞቻቸው ለአብራሪነት ሊፈተኑ ነበር።
አቶ ግርማ ግን በጭራሽ ሐሳቡ አልነበራቸውም።
እዚያ ሲደርሱ ወረቀት ይታደላል። “ኧረ እኔ ገና የ2ኛ ዓመት ተማሪ ነኝ” አሉ።
“ችግር የለውም ተፈተን” ተባሉ፤ ወረቀት ተሰጣቸው። ተፈተኑ፤ አውሮፕላን አብራሪ ለመሆን። ክፋቱ ደግሞ አለፉ።
የሚገርም አጋጣሚ ነበር።
መሠልጠንም ጀመሩ። ትንሽ ቆይቶ ግን የሕይወታቸው የበረራ አቅጣጫ ተቀየረ።
አስተማሪዎቻቸው ጥሩ አብራሪ እንደማይሆኑ ነገሯቸው። ወደ ማርኬቲን ቀየሯቸው።
አቶ ግርማ እነሆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚበሩበት ከፍታ እየጨመረ፣ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በኢትዮጵያ የአቪየሽን ሰማይ ላይ ነበሩ፤ እስካለፈው ሳምነት ድረስ።
‘ተወልደን ፀጉር እያለው ነው የማውቀው’
በፍጥነት ካልበረርን የአቶ ግርማ ዋቄን ረዥም የሥራ ዘመን አንዘልቀውም።
ሕይወታቸውን በወፍ በረር ብቻ እንቃኝ።
ከዘመናት በኋላ አቶ ግርማ ከተራ ኦፊሰርነት ጀምረው የካርጎ ክፍል ኃላፊ ሆነው ተመደቡ። በአየር መንገዱ የመጀመሪያው የካርጎ ዳይሬክተርም ሆኑ።
ድሮ አውሮፕላን ሰውን ያሳፍራል እንጂ እንደ መናኛ አይዙሱ ዕቃ ተሸክሞ፣ ኩሊነት ሠርቶ፣ ገንዘብ ያመጣል ተብሎ ብዙም አይዳነቅም ነበር።
በዚህ የተነሳ ለካርጎ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ ነበር። ኧረ ዞር ብሎ የሚያየውም አልነበረም።
“ካርጎ ራሱን ችሎ ትልቅ ቢዝነስ እንዲሆን ያስቻሉት አቶ ግርማ ናቸው” ይላሉ በአቪየሽን ጉዳዮች ጋዜጠኛ እና ተንታኝ አቶ ቃለየሱስ በቀለ።
አቶ ግርማ ዋቄ ካርጎ ክፍል ዳይሬክተር ሳሉ አንድ ነፍሰ ቀጭን፣ ጎረምሳ ከወዲያ ወዲህ ‘ቱር ቱር’ ሲል ይመለከታሉ።
ይህ ወጣት ከማርኬቲንግ ተመርቆ ገና ካርጎ ክፍል መግባቱ ነበር። ትጋቱ ገረማቸው።
እያቀረቡት መጡ። ከአቶ ግርማ ቅርብ ሆኖ ረዥም ዘመን አገለገለ።
በኋላም አየር መንገዱን ለመምራት በቃ። ያ ወጣት አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ነው።
በኋላ እርሳቸውን ተክቶ የአየር መንገዱ ሥራ አስፈጻሚ ሆነ።
አቶ ግርማ ዋቄ፤ አቶ ተወልደን መቼ እንደሚያውቋቸው ሲናገሩ፣ “ገና ሳይመለጥ - ሙሉ ፀጉር እያለው ነዋ የማውቀው” ብለው ይቀልዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, kaleyesus bekele
የአቶ ግርማ ዋቄ ቀይ መስመር
አቶ ግርማ ዋቄ የአየር መንገዱ ከፍተኛ አመራር እያሉ የመጀመሪያው ቦርድ ሊቀመንበር ያን ጊዜ ከበረሃ የመጡት አቶ ስዬ አብረሃ ነበሩ።
ህወሓት መሩ ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ጊዜ አየር መንገዱ ተፈተነ። ካፒቴን መሐመድን የመሰሉ ስመ ጥር ሥራ አስፈጻሚዎች ያጸኑት አየር መንገድ ተናወጠ።
ለ22 ዓመታት የአቪየሽን ጉዳዮችን በመዘገብ የሚታወቁት አቶ ቃለየሱስ አየር መንገዱ በኢህአዴግ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ለውጦች ጊዜ ሁሉ የአስተዳደር መንገጫገጭ (management Turbulence) ይገጥመው ነበር ይላሉ።
ለምሳሌ ንጉሡ ሲወርዱ ደርግ ከአየር ኃይል ጄኔራል አምጥቶ በኃላፊነት ሾመ። ካድሬዎችንም በውስጡ ሰግስጎ ነበር።
የደርግ ጥላቻ መነሻው የነበረው አየር መንገዱ ‘የንጉሡ አየር መንገድ ነው’ ከሚል እሳቤ ነበር።
በኋላ ግን ደርግ ትንፋሽ ሲወስድ ከስህተቱ ተምሮ አየር መንገዱን አንጻራዊ የአስተዳደር ነጻነትን አጎናጸፈው።
አቶ ግርማ ዋቄ በወቅቱ ደርግ ለአየር መንገዱ የነበረውን አሉታዊ ስሜት ሲገልጹ፣ “ጭራሽ አየር መንገድ አያስፈልገንም” የሚሉ ሰዎችም ነበሩበት ይላሉ።
ለምን ሲባሉ “አውሮፕላን ‘ለንጉሡ ጉራ እና ሽርሽር ሲባል እንጂ ለዚች ድሃ አገር ምን ይፈይድላታል?’ ብለው ይሉ ነበር-ደርጎች” ሲሉ ያስታውሳሉ።
ኢህአዴግ ሲመጣ ሌላ ጣጣ መጣ።
አየር መንገዱን ጥምድ አድርጎ ያዘው፤ የኢህአዴግ በጎ ያልሆነ አመለካከት መነሻው ደግሞ ሌላ ነው። አየር መንገዱ በደርግ ጦርነት ጊዜ “ስንቅ እና ትጥቅ እያቀበለ አስፈጅቶናል” የሚል።
በዚያ አስቸጋሪ ዘመን የቦርድ ሊቀመንበሩ አቶ ስዬ አብረሃ ነበሩ።
የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በዛ። በርካታ ጎምቱ የአየር መንገዱ ሠራተኞች መልቀቅ ያዙ። አቶ ግርማ ዋቄም ቀድመው ለቀቁ። 37 ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችም ተከተሏቸው።
አንጋፋው አየር መንገድ ክንፉ የተመታ ያህል መንገታገት ያዘ።
አቶ ግርማ ዋቄ ለአምስት ወር ሥራ ፈተው አዲስ አበባ ተቀመጡ።
ከዚያም የገልፍ አየር መንገድ በሚያጓጓ ደመወዝ ወሰዳቸው።
ከገልፍ በተሻለ ደመወዝ ዴኤችኤል (DHL) ወሰዳቸው።
ከዴኤችኤል እንደገና ገልፍ በተሻለ ኃላፊነት እና ደመወዝ መልሶ ወሰዳቸው። እንዲህ እንዲያ እያሉ 9 ዓመት ውጭ ቆዩ።
የገልፍን የካርጎ ክፍል በኃላፊነት እያስተዳደሩ ሳለ አንድ ቀን ከከባድ ባለሥልጣን፣ ከባድ የስልክ ጥሪ ደረሳቸው።
ለካንስ አገር ቤት ለአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢ ለውጥ ተደርጎ ነበር።
ቦታውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን ተረክበውታል። ወደ ግርማ ዋቄ የደወሉትም እርሳቸው ነበሩ።
ከ5 ሺህ ዶላር ወደ 5 ሺህ ብር ደመወዝ
አየር መንገዱ ፈተና ውስጥ ገብቶ ነበር፤ በዚያ ዘመን።
አቶ ስዩም መስፍን አመራሩን ሰብስበው “ታዲያ ምን ተሻለን?” ብለው አማከሩ።
“ግርማ ዋቄ የሚባል ጎበዝ ሰው አለ እሱን አምጣው” ተባሉ።
ለዚያ ነበር አቶ ስዩም ወደ ግርማ ዋቄ ስልክ የመቱት።
ደግሞ መጥተህ አናግረኝ አይደለም ያሏቸው። መጥቼ ላናግርህ ነበር ያሏቸው።
የአንድ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዴት እኔን መጥቶ ያናግረኛል፤ “ባይሆን እኔ መጥቼ ላናግርዎ” ብለው አቶ ግርማ ዋቄ ቅዳሜ ቀን ኢትዮጵያ ከተፍ አሉ።
አቶ ስዩም መስፍን ሊያግባቧቸው ሞከሩ። “እባክህ ያሳደገህን አየር መንገድ ታደገው” ተባሉ።
በዚያን ወቅት (በአውሮፓውያኑ 2003/04) የአቶ ግርማ ደመወዝ ጥቅማ ጥቅም ሳይጨምር 5ሺህ ዶላር ነበር። ደመወዝ ሲጠየቁ “ያው ብስራትን የምትከፍሉትን ክፈሉኝ፤ ይበቃኛል” አሉ።
“አገርህ ትፈልግሃለች ስለው 5ሺህ ዶላሩን ትቶ በ5ሺህ ብር ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ መጣ” ብለው አቶ ስዩም መስፍን ሲመሰክሩላቸው በቦታው ነበርኩ ይላሉ ጋዜጠኛ ቃለየሱስ በቀለ።
አቶ ግርማ በአንድ ወቅት በአንድ የአገር ውስጥ ቴሌቪዥን ይህንኑ አስመልክተው ሲናገሩ፣ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስፈጻሚ ደመወዝ እኮ አፍሪካ ውስጥ 3 አውሮፕላን ከሚያስተዳድር አንድ ግለሰብ ደመወዝ ያነሰ ነው፤ እርካታው ግን የትየለሌ ነው” ብለው ነበር።
“በደመወዝማ ቢሆን ማንም ሰው ኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሠራም ነበር” ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል።
ብቻ “ያሳደገህን አየር መንገድ ና እና ተረከብ” ተብለው ሲጋበዙ ዐይናቸውን አላሹም። ግን ደግሞ አንድ ጥብቅ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ።
“ጣልቃ ከገባችሁብኝ እለቃለሁ” ብለው አስፈራሩ። አቶ ስዩም ቃል ገቡላቸው።
“አንድም ቀን ቃላቸውን አላጠፉብኝም፤ ሰባት ዓመት ሙሉ ነጻነቴን ጠብቀውልኛል” ብለዋል አቶ ግርማ ዋቄ የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍንን ሲያመሰግኑ።
ከዚያስ ምን ሆነ?
ከዚያማ አሥራ አንድ ዓመታት የተለዩትን አየር መንገድ ማቃናት ጀመሩ።
ሥልጣኑን በተረከቡ ማግስት ‘ትክክለኛ ባለሙያዎችን ትክክለኛ ቦታ ላይ በመመደብ’ ጀመሩ።
መንገጫገጭ የገጠመውን አየር መንገድ መስመር አስያዙት።
አቶ ተወልደ ያኔ ኒው ዮርክ ሄደው ነበር።
አቶ ግርማ ዋቄ ለአቶ ተወልደ ጥሪ አደረጉላቸው። “ና ባክህ አግዘኝ” አሏቸው። ድሮ በካርጎ ክፍል ይተዋወቁ የለ?
አቶ ተወልደ ሳይውሉ ሳያድሩ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።
ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር አድርገው መደቧቸው።
ጊዜው ክንፍ አውጥቶ በረረ።
በፈረንጆች 2014 ነገሮችን ለማስተካከል ብቻ ቃል ገብተው ሥራ የጀመሩት ግርማ ዋቄ፣ ከአየር መንገዱ ጋር ሊለያዩ አልቻሉም።
እርሳቸው ልልቀቅ ሲሉ - አቶ ስዩም “በፍጹም!” ሲሏቸው እንደቀልድ ዓመታት ነጎዱ።
በመጨረሻም በአውሮፓውያኑ ጥር 2011 “አሁንስ በቃ ልሂድ” ብለው ቆረጡ። እንግዲያውስ የምትተማመንበትን ተተኪ አምጣ ተባሉ።
“ተወልደ ይረከበኝ” አሉ። በክብር ሽኝት ተደርጎላቸው ለቀቁ። በክብር ብቻ ሳይሆን በለቅሶ ተሸኙ።

የፎቶው ባለመብት, kaleyesus bekele
የአቶ ግርማ ‘ድሪምላየነሮች’
አቶ ግርማ ለአየር መንገዱ ብዙ አልመዋል። ካለሟቸው ብዙዎቹን አሳክተዋል ይላሉ የአቪየሽን ጋዜጠኛ እና ተንታኝ አቶ ቃለየሱስ።
ከእነዚህ አንዱ ካርጎ ክፍሉን ሁነኛ የገቢ ምንጭ ማድረግ ነው።
ሌላው የድሪምላይነር 787 አሥር አውሮፕላኖችን በወቅቱ 1.5 ቢሊየነር ዶላር ወጪ አስደርገው ግዢ ማሳካታቸው ነው።
“ከፍተኛው ስኬታቸው ርዕይ-2010 (VISION 2010) ቀርጸው ማስተግበራቸው ነው” ይላሉ አቶ ቃለየሱስ።
ይህን ያሳኩት ደግሞ ከአቶ ተወልድ ጋር በመሆን ነበር። ለአየር መንገዱ ትልቅ ለውጥ ያመጣ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ነበር።
ይህ ስትራቴጂ በ2010 (እአአ) አየር መንገዱን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያለው አየር መንገድ ማድረግ አስቻለ።
ድሮ የናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድን ቁልቁል ይመለከቱት ነበር።
ድሮ አንዳንድ የአረብ አገራት አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጠገባችን ለምን ይቆማል ብለው ይንቁት ጀምረው ነበር።
አሁን የብዙ አገራት ሕልም ኢትዮጵያ አየር መንገድን መሆን ነው። “ይህ እንዲሆን ብዙ ሰዎች ተግተዋል፤ ግን ደግሞ የግርማ ዋቄ ሚና ትልቅ ነው” ይላሉ የአቪየሽኑ ተንታኝ።
አቶ ግርማን አፍሪካዊያን ለምን ያደንቋቸዋል?
አቶ ግርማ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በጡረታ እንደተገለሉ ተሻምታ የወሰደቻቸው ርዋንዳ ናት።
አቶ ግርማ ግን ማረፍ ፈልገው ነበር። ከልጆቻቸው ጋር ዘለግ ላለ ጊዜ መቆየት፤ የባለቤታቸውን የከብት ርቢ ማገዝ ወዘተ ነበር ዕቅዳቸው።
ማረፍ የቻሉት ግን አንድ ዓመት ብቻ ነው።
ርዋንዳ ሁለት ኃላፊነት ሰጠቻቸው።
የርዋንዳ አየር መንገድን ‘በሁለት ክንፉ እንዲበር’ ማስቻል አንዱ ነው። ለዚህ የቦርድ ሊቀመንበር ተደርገው ተሾሙ።
ሁለተኛው ደግሞ የርዋንዳ የትራንስፖርት ሚኒስትር የአቪየሽን ጉዳዮች አማካሪ ሆኑ።
አቶ ግርማ ርዋንዳ በድምሩ አምስት ዓመት አገለገሉ።
“በቆይታቸው ለአየር መንገዱ ጥሩ መሠረት ጥለዋል፤ ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የሥራ ዕድልን ከፍተዋል” ይላሉ ጋዜጠኛ ቃለየሱስ።
ከሩዋንዳ በኋላ የቶጎ ፕሬዝዳንት የአቪየሽን ጉዳዮች አማካሪም ሆነዋል።
በሌሎች የአፍሪካ አገራትም ኦፊሳላዊ ባልሆነ መንገድ ምክር ይለግሱ ነበር።
በትልልቅ የኢቪየሽን ጉባኤዎች ላይ እየተጋበዙ የአፍሪካ አየር መንገዶች እርስ በርስ ተጋግዘው መሥራት እንዳለባቸው ይመክሩ፣ ይዘክሩ ነበር።
በዚህ የተነሳ የአፍሪካ አቪየሽን አባት (The father of African Aviation) የሚል ተቀጽላን አገኙ።
“ቅጽል ስም ብቻ አይደለም፤ ‘Girma Waqe life achievement award’ የሚባል የሕይወት ዘመን ሽልማት በስማቸው ይሰጣል” ይላሉ የአቪየሽን ጋዜጠኛ ቃለየሱስ።
በአፍሪካ የአቶ ግርማ ስም ከፍ ያለ ነው የሚሉት ጋዜጠኛ ቃለየሱስ፣ ለዚህ የሚጠቅሱት ማስረጃ ከአንድም ሁለት ሦስቴ ርዋንዳ በሥራ አጋጣሚ በተጓዙባቸው ወቅቶች የታዘቧቸውን ሁኔታዎች ነው።
“በቃ ሁሉም ዋቄ፣ ዋቄ ሲሉ ነው የሚሰማው፤ ዝቅ ብለው በአክብሮት ጭምር ነው የሚጨብጧቸው፤ አቶ ግርማ እዚያ ትልቅ ስም ነው ያላቸው፤ ያስደንቃል።”
“ግርማ ዋቄ የሚለው ስም ለአበዳሪዎች ዋስትና ነው”
የአቪየሽን ጉዳዮች ጋዜጠኛ ቃለየሱስ፤ የአቶ ግርማ ከኢትዮጵያ አየር መንገድን ተከትሎ ሌሎች ዐይናቸውን የጣሉባቸው ጉልህ ምክንያት አለ ይላሉ።
አየር መንገዶች ግርማ ዋቄን በአመራር ቡድናቸው ውስጥ ማካተታቸው በአቪዬሽን ዘርፍ የዳበረውን ልምዳቸው ብቻ ፈልገው አይደለም ይላሉ። “ስማቸውም ብራንድ ነበር።”
ቃለየሱስ “ዋቄ የሚለው ስም ለአበዳሪዎች ጭምር መተማን ይፈጥራል” ብለው ይከራከራሉ።
አውሮፕላን የሚገዛው በዱቤ ነው። አበዳሪዎች ደግሞ እምነት ሊኖራቸው የግድ ነው።
ኤክዚም ባንክ፣ ዩሮፒያን ክሬዲት ኤጀንሲ የብድር ዋስትና ይሰጣሉ። ሲሰጡ ታዲያ ብድር አቅራቢዎች የአየር መንገዱን የብድር ታሪክ፣ የሒሳብ መዝገብ ብቻ አይደለም የሚያዩት። የተረጋጋ ማኔጅመንት እና ቦርድ አለ ወይ? ብለውም ይፈትሻሉ።
ይህ በብድር ሒደት ላይ የራሱ ነጥብ አለው የሚሉት ጋዜጠኛ ቃለየሱስ፣ አየር መንገድ ላይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነቱ ከታየ አበዳሪዎች እምነታቸው ይሸረሸራል ሲሉ ያስረዳሉ።
ግርማ ዋቄ ቀደም ባሉ ቃለ ምልልሶቻቸው ደጋግመው ከሚያነሷቸው ጠንካራ ሐሳቦች መካከል “ጣልቃ ገብነትን አለመውዳቸው” ነው።
ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ “እከሌን ቅጠር፤ ወደዚህ ብረር፤ ያን አውሮፕላን ግዛ የሚለኝን አልወድም” ብለው ያውቃሉ።
እሱ ከአየር መንገድ ወጣ እንጂ አየር መንገዱ ከእርሱ አልወጣም ነበር
በሥራቸው ባህሪ የተነሳ አየር መንገዱ ቤት ነው የሚሉት ጋዜጠኛ ቃለየሱስ፣ አቶ ግርማ ዋቄ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነውም ከቢሮ አካባቢ ንቅንቅ አይሉ እንደነበር ታዝበዋል።
“ይህ በቦርድ አሠራር የተለመደ አይደለም፤ ‘ቦርድ ሩም’ የሚባል አለ፤ የቦርድ ሰብሳቢን ግን ሁልጊዜ ማየት አልተመደም” የሚሉት ቃለየሱስ፣ አቶ ግርማ ግን ከአቶ መስፍን ጣሰው ቢሮ ፊት ለፊት ትንሽዬ ቢሮ ይዘው ሁልጊዜ ሲሠሩ ነበር የማያቸው። ሲሉ ትዝብታቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።
ግርማ ዋቄ ድሮም ቢሆን ሥራ ለቀው አየር መንገዱን እርግፍ አድርገው መተው እንዳልቻሉ በቅርብ የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ።
ለምሳሌ ከአየር መንገዱ ለ11 ዓመታት ተለይተው በገልፍ አየር መንገድ በሚሠሩበት ጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነገር ያስጨንቃቸው ነበር።
በአንድ ወቅት የቀድሞው ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ በሰጡት ቃለ ምልልስ “ጋሽ ግርማ ጡረታ ወጥቶ ሳለ እንኳ አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ይደውልልኝ ነበር” ሲሉ ለዚህ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ግርማ ዋቄ ከአየር መንገዱ ይወጣል እንጂ አየር መንገዱ ከግርማ ዋቄ አይወጣም።
*ይህ ዘገባ ከሁለት ዓመት በፊት በቢቢሲ አማርኛ ላይ ቀርቦ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ማሻሻያ ተደርጎበት በድጋሚ የቀረበ ነው።















