አሜሪካ እና ቻይና የገቡበትን ውጥረት ለማርገብ በዚህ ሳምንት ሊነጋገሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ እና ቻይና ባለስልጣናት በሁለቱ የዓለም ግዙፍ ምጣኔ ሀብት ባለቤቶች መካከል የተከሰተውን የንግድ ጦርነት ለማርገብ በዚህ ሳምንት ንግግር እንደሚጀምሩ ተገለፀ።
የቻይና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሂ ሊፊንግ የፊታችን አርብ በሲውዘርላንድ ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቀው ንግግር እንደሚሳተፉ የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ፀሐፊ ስካት ቤሰንት እና የዩናይትድ ስቴት የንግድ ወኪል ጀሜሰን ጊሪር ዋሽንግተንን ወክለው በንግግሩ እንደሚሳተፉ በቢሮዎቻቸው በኩል ገልፀዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ዳግም ከተመለሱ በኋላ ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ እስከ 145 በመቶ ታሪፍ ጥለዋል።
ቤጂንግ ለዚህ እርምጃ አጸፋ የሰጠች ሲሆን በአንዳንድ የአሜሪካ ምርቶች ላይ እስከ 125 በመቶ ቀረጥ መጣሏን አስታውቃለች።
የዓለም አቀፍ የንግድ ባለሙያዎች የአገራቱ ንግግር በርካታ ወራት እንደሚፈጅ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ንግግሩ የቻይና ምክትል ፕሬዝዳንት ሃን ዜንግ የዶናልድ ትራምፕን በዓለ ሲመት ከታደሙ በኋላ በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ የሚደረግ የመጀመሪያው ግንኙነት ነው።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ፀሐፊ ቤሰንት የዓለም አቀፍ የምጣኔ ሀብት ስርዓቱን ለማስተካከል እና የአገራቸውን ጥቅም ለማስከበር ንግግሩን በጉጉት እየጠበቁት እንደሆነ ተናግረዋል።
"እንደሚሰማኝ ከሆነ [ንግግሩ] ውጥረት ማርገብ ላይ የሚያተኩር ነው። ትልቅ የንግድ ስምምነት አይሆንም። ነገር ግን ከመሻገራችን በፊት ውጥረቱን ማርገብ ይኖርብናል" ሲሉ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ገልፀዋል።
የቻይና ንግድ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በበኩላቸው "ዩናይትድ ስቴር ጉዳዩን በድርድር መፍታት ከፈለገች በአንድ ወገን የጣለችው ታሪፍ በራሷ እና በመላው ዓለም ላይ የሚያደርሰውን ከባድ አሉታዊ ተፅዕኖ መጋፈጥ ይኖርባታል" ብለዋል።
የቻይና መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገበው ቤጂንግ ከዋሽንግተን ጋር ለመነጋገር የወሰነችው ዓለም አቀፍ ተፈላጊነቷን በተለይም ከአሜሪካ ነጋዴዎች የቀረበላትን ጥያቄ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
መገናኛ ብዙኃኑ ቻይና ለመነጋገር በሯ ክፍት መሆኑን፤ ነገር ግን ይህ የማይሆን ከሆነ እስከ መጨረሻው ለመፋለም መወሰኗን አክሎ ዘግቧል።
የሁለቱ አገራት የንግድ ጦርነት በፋይናንስ ገበያው አለመረጋጋት የፈጠረ ሲሆን፤ በዓለም ንግድ ላይም አስደንጋጭ ምልክቶች ታይተዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የንግድ ባለሙያዎች በተለይም በንግግሩ የመጀመሪያ ደረጃ ተስፈኛ አይደሉም።
ለዚህም የሚያነሱት እ.አ.አ. በ2018 እንደነበረው ሁሉ የአገራቱ ንግግር ምልልስ እንደሚኖር ገልፀው ለወራት አሊያም ከዓመት በላይ ሊራዘም የሚችል ነው ብለዋል።












