የአሜሪካዋ ግዛት በእያንዳንዱ መማሪያ ክፍል አሥርቱ ትዕዛዛት እንዲለጠፉ ትዕዛዝ አስተላለፈች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሉዚያና እያንዳንዱ እስከ ዩኒቨርሰቲ ያለ የሕዝብ ትምህርት ቤት መማሪያ ክፍሎች ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ አሥርቱ ትዕዛዛት እንዲለጠፉ ትእዛዝ ያስተላለፈች የመጀመሪያዋ የአሜሪካ ግዛት ሆናለች።
በሪፐብሊካን የተደገፈውን ሐሳብ አገረ ገዥው ጄፍ ላንድሪ ረቡዕ ዕለት ፈርመው ሕግ ያፈደረጉት ሲሆን አሥርቱ ትዕዛዛት "የግዛታችን እና የብሔራዊ መንግሥታችን መሠረታዊ ሰነዶች ናቸው" ሲሉ ገልጸዋል።
ህጉ በሲቪል መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተቃውሞ ይገጥመዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ ህግ በአሜሪካ ህገ መንግሥት የተቀመጠው እና ሐይማኖትን እና የመንግሥት መለያየትን የሚገልጸውን ሕግ የሚጻረር ነው ብለው ይከራከራሉ።
“ምክር ቤቱ የሃይማኖት መመስረትን ወይም የሐይማኖትን መተግበርን የሚከለክል ህግ አያወጣም” ይላል።
የግዛቱ ህግ አንድ አሥርቱ ትዕዛዛት 28 ሴሜ በ 35.5 ሴሜ በሆነ ፖስተር ላይ በደንብ እንዲታይ ተደርጎ መጻፍ እንደለበት ያስገድዳል።
በተጨማሪም ትዕዛዛቱ እንዴት "ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል የአሜሪካ የህዝብ ትምህርት ዋነኛ አካል እንደነበሩ" ከሚገልጽ ባለ አራት አንቀጽ "መግለጫ" ይኖረዋል።
በ2025 ከግዛቲቱ የገንዘብ ድጋፍ በሚያገኙ ሁሉም ክፍሎች ውስጥ እስከ 2025 ፖስተሮቹ መሰቀል ያለባቸው ሲሆን ከግዛቱ ድጋፍ የማያገኙት ደግሞ በራሳቸው የሚያዘጋጁ ይሆናል።
ቴክሳስ፣ ኦክላሆማ እና ዩታን ጨምሮ ሌሎች በሪፐብሊካን የሚመሩ ግዛቶችም ተመሳሳይ ህጎችን በቅርቡ አቅርበዋል።
ትምህርት ቤቶች፣ ፍርድ ቤቶች እና የፖሊስ ጣቢያዎችን ጨምሮ በሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ አስርቱን ትዕዛዛት የመለጠፍ ጉዳይ በርካታ የህግ ውዝግብ አስነስቷል።
እአአ በ 1980 የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኬንታኪ ተመሳሳይ ህግ በማውጣት ትዕዛዛቱ በአንደኛ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲለጠፍ ለማድረግ ያቀረበችውን ሃሳብ ሽሮታል።
ከፍተኛው ፍርድ ቤት አስርቱ ትዕዛዛት እንዲለጠፉ የሚጠይቀውን መስፈርት "ምንም ዓለማዊ ዓላማ የሌለው" እና "በባህሪው ሃይማኖታዊ ነው" ሲል ወስኗል።
ፍርድ ቤቱ እንደ መግደልና መስረቅ ካሉ የወንጀል ጉዳዮች በተጨማሪ አሥርቱ ትዕዛዛት የሰንበትን ቀን ማክበርን ጨምሮ ፈጣሪን ማምለክን በማካተቱ ነው ሐይማኖታዊ ነው ያሉት።












