"ቤይሩት የጦርነት ቀጠና ሆናለች" የቢቢሲ ዘጋቢ

ቤይሩት

የፎቶው ባለመብት, NAFISEH KOHNAVARD / BBC

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የሐማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ያለው ጦርነት አንድ ዓመት ሊሞላው ቀናት በቀሩበት በአሁኑ ወቅት በሊባኖስ የምታካሄደውን የአየር እና የምድር ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።

እስራኤል ለሊቱን የሊባኖስን ምዕራባዊ ከተማ ዳሄህን ስትደበደብ ማደሯ ተሰምቷል።

እስራኤል በሰሜናዊ ሊባኖስ በሚገኘው ቤዳዊ የስደተኞች መጠለያ ላይ ባደረሰችው የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት የሐማስ ወታደራዊ አዛዥ መገደሉ ተሰምቷል።

የቢቢሲ ዘጋቢ ከቤይሩት እስራኤል እየፈጸመች ስለምትገኘው የአየር ትቃት ስትገልጽ "አመንም አላመንም በአሁን ሰዓት ቤይሩት የጦር ቀጠና ሆናለች" ብላለች።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በትናንትናው ለሊት ጥቃት በደቡባዊ ሊባኖስ ቤንት ጄቤል አካባቢ በሚገኝ ሆስፒታል አጠገብ ባለ መስጂድ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

ሳላህ ጋንዶር ሆስፒታል ዘጠኝ የሕክምና አባላቱ በአየር ጥቃቱ መጎዳታቸውን ገልጿል።

የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል በመስጂዱ ውስጥ የሔዝቦላህ ተዋጊዎች ነበሩ ሲል መግለጫ ሰጥቷል።

“በመስጂድ ውስጥ ከሳላህ ጋንዶር ሆስፒታል አጠገብ” የሔዝቦላ አባላት ማዘዣ ጣብያ ውስጥ ሳሉ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ነው ጦር ሠራዊቱ የተናገረው።

የሊባኖስ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣብያም ሆስፒታሉ አካባቢ የእስራኤል አየር ኃይል ጥቃት መፈጸሙን ዘግቧል።

ኤኤፍ ፒ በበኩሉ የሆስፒታሉን ዳይሬክተር ጠቅሶ የአየር ጥቃት መድረሱን እና ከትቃቱ በኋላም ለቅቀው መውጣታቸውን ዘግቧል።

የሊባኖስ ጤና ሚኒስትር እስራኤል በሊባኖስ የአየር ጥቃት ከጀመረች ጊዜ አንስቶ ከ2000 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከእነዚህም መካከል 127ቱ ሕጻናት 261 ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለሊቱን እንዲሁም ማለዳውን የእስራኤል ጦር ኃይል በደቡባዊ ሊባኖስ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች መኖርያ ቤታቸውን ለቅቀው እንዲሄዱ እንዲሁም የሔዝቦላህ ተቋማት ናቸው ከሚባሉ አካባቢዎችም ራሳቸውን እንዲያርቁ ሲያስጠነቅቅ ነበር።

በምስራቃዊ ቤይሩትም የእስራኤል የቅኝት ሰው አልባ አውሮፕላኖች በከተማዋ ላይ ሲያንዣብቡ ታይተዋል።

በደቡባዊ ሊባኖስ ድንበር አካባቢ የምታደርገውን የአየር እና የምድር ጥቃት ያጠናከረችው እስራኤል ለሊቱን በሊባኖስ ሰማይ ላይ ሄሌኮፕተሮቿ ተደጋጋሚ በረራ ሲያደርጉ ይሰማ ነበር።

ሔዝቦላሕ ከእስራኤል የምድር ጦር ጋር የሚያደርገውን ጦርነት ማፋፋሙን የገለጸ ሲሆን አሁንም ሚሳዔሎችን ወደ እስራኤል እየተኮሰ ይገኛል።

የእስራኤል ጦር ጥቃቱን ባስፋፋበት በአሁኑ ወቅት በሊባኖስ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

እስራኤል አሁንም በደቡብ ሊባኖስ የሚኖሩ ዜጎች ቤታቸውን ጥለው እንዲሄዱ እያስጠነቀቀች ትገኛለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሐማስ ታጣቂ አዛዥ ከሆኑት መካከል አንዱ ነው የተባለው ሳይድ አታላህ ከሚስቱና ከሁለት ልጆቹ ጋር በሊባኖሷ ከተማ ትሪፖሊ መገደሉ ተሰምቷል።

ምንም እንኳ የእስራኤል ጦርም ሆነ ሐማስ እስካሁን ድረስ ስለ ግድያው ምንም ያሉት ነገር ባይኖርም ለሔዝቦላህ ቅርብ የሆኑ የዜና ምንጮች ግን ግድያውን ዘግበዋል።

ከሐማስ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለው ፊላስቲን የተባለው ጋዜጣ በሰሜናዊ ሊባኖስ ትሪፖሊ ውስጥ በሚገኘው ቤዳዊ በተሰኘው የፍልስጤም ስደተኞች መጠለያ ሳእድ አታላህ ከሦስት የቤተሰቦቹ አባላት ጋር ተገድሏል ሲል ዘግቧል።

የሊባኖስ ዕለታዊ ጋዜጣ የሆነው አን ናሃር በበኩሉ ሚስቱ እና ሁለት ልጆቹን ጨምሮ መገደላቸውን ዘግቧል።

የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላን በፈጸመው የአየር ጥቃት አታላህ ከቤተሰቦቹ ጋር ይኖርበት የነበረው አፓርትመንት ሙሉ በሙሉ መውደሙንም ዘግቧል።

ሐማስ የአዛዡን ግድያ እስካሁን በይፋ ባይገልጽም የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ እንዲሁም አጋር የሆኑ ታጣቂ ቡድኖች አዛዡ ከእነ ቤተሰቡ ስለመገደሉ እየተናገሩ ይገኛሉ።

የእስራኤል ጦር ከሊባኖስ የተተኮሱ ናቸው ያላቸውን አምስት ሚሳዔሎች የተወሰኑትን ሲያከሽፍ የተቀሩት ደግሞ ሰው በሌለባቸው መሬቶች እንዲወድቁ መደረጋቸውን አስታውቋል።

በትናንትናው ዕለት 222 ሚሳዔሎች ከሊባኖስ ወደ እስራኤል ግዛት መተኮሳቸውን ጦሩ ጨምሮ አስታውቋል።

ሔዝቦላህ አዳያሴህ በተባለች መንደር ትናንት ምሽት የእስራኤል ምድር ጦር የከፈተውን ጥቃት መመከቱን ገልጿል።

ሔዝቦላህ ተዋጊዎች ከእስራኤል ጦር ጋር “የተታኮሱ ሲሆን” “እየገፋ መጥቶ የነበረው ጦር ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ በማድረስ፣ ወደ ኋላ እንዲሸሽ እንዲሁም ተዋጊዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገናል” ብሏል።

ቢቢሲ ዛሬ ማለዳው ከቦታው እንዳረጋገጠው በዚህ ስፍራ አሁንም ውግያ እየተካሄደ ይገኛል።

የእስራኤል ጦር በዚህ ተናጠል ጥቃት ላይ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።