እስራኤል የሐማስን ጥቃት 1ኛ ዓመት በምትዘክርበት ቀን በጋዛ እና በቤይሩት ጥቃት ፈጸመች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤል መከላከያ ኃይል እሑድ ዕለት ቤይሩት የሚገኙ በርካታ የሄዝቦላህ የደኅንነት ቀጣናዎች እና የመሣሪያ ማከማቻዎችን መምታቱን ገለጸ።
በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ከፍተኛ ድምፅ ያለው ፍንዳታ ተሰምቷል። ይህ የሆነው የእስራኤል ጦር በአካባቢው ያሉ ሰዎች ለቀው እንዲወጡ ማሳሳቢያ ከሰጠ ከሰዓታት በኋላ ነው።
እስራኤል በሊባኖስ የምታደርገውን ጥቃት አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፣ እሑድ ምሽት በተፈጸመው ጥቃት የቤይሩት ሰማይ በቃጠሎ እና በጭስ ታፍኖ ታይቷል።
የሊባኖስ ፓርላማ አባል የሆኑት ሜልሔም ኻላፍ “ሊባኖስ ላይ ከፍተኛ ጥቃት እየተፈጸመ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሜልሔም እንደሚሉት እስራኤል ቤይሩት ላይ እያደረሰች ያለው ጥቃት “ተመጣጣኝ” አይደለም።
“ሰላማዊ ዜጎች ላይ ቦምብ መጣል፤ መንደሮችን ማውደም፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕንፃዎችን ማፈራረስ፤ ንፁሐንን መግደል፤ ይሄ ሁሉ እስራኤል ሽብርተኛ ያለችውን ለመግደል የምታደርገው ጥረት ነው።”
በተያያዘ ዜና የሊባኖሱ ሄዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል በፈጸመው ጥቃት 10 ሰዎች መቁሰላቸው ተሰምቷል።
የእስራኤል የአምቡላንስ አገልግሎት እንደገለፀው በሐይፋ እና ሪቤሪያስ ከተሞች ሄዝቦላህ በሰነዘረው የሚሳዔል ጥቃት 10 ሰዎች ቆስለዋል።
ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል የተኮሳቸው ሚሳዔሎች በአካካቢው የሚገኝ አንድ ምግብ፣ መኖሪያ ቤት እና አውራ ጎዳና መትተዋል ሲል የእስራኤል መከላከያ ገልጿል። እስራኤል እንዴት የሄዝቦላህ ሚሳዔል አየር መቃወሚያዋን አልፎ ሊገባ እንደቻለ ምርመራ እያደረገች ትገኛለች።
በሌላ በኩል ድንበር አካባቢ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ አንድ እስራኤላዊ ወታደር ሲገደል፣ ሁለት ባልደረቦቹ ደግሞ ክፉኛ መቁሰላቸው ተሰምቷል።
እስራኤል ባለፈው ሳምንት ነው እግረኛ ጦሯን ወደ ሊባነኖስ በማዝመት ወረራ ፈጽማለች። የእስራኤል መከላከያ ኃይል የሊባኖሱን ሄዝቦላህ ለማጥፋት በሚል ነው የምድር ዘመቻ እና የአየር ጥቃት እያካሄደ ይገኛል።
የፍልስጤሙ ሚሊሻ ሐማስ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 በእስራኤል ምድር ባደረሰው ጥቃት 1200 እስራኤላውያንን ገድሎ 250 ገደማ ሰዎች አግቶ መውሰዱ ይታወሳል።
ከዚህ ጥቃት በኋላ እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዛ ያሰማራችው እስራኤል ከሐማስ ወታደሮች ጋር የምታደርገው ጦርነት ድፍን አንድ ዓመት ሆኖታል።
በጋዛ ሰርጥ ባለው ጦርነት ምክንያት ሕፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ እስካሁን ከ41 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የፍልስጤሙ ሐማስን በመደገፍ በድንበር በኩል ወደ እስራኤል የሮኬት ጥቃት ሲፈጽም የቆየው የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከእስራኤል ጋር ወደ ለየለት ጦርነት ውስጥ ገብቷል።
ይህ የሆነው እስራኤል ነባሩ የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህን በአየር ጥቃት መግደሏን ካሳወቀች በኋላ ነው።
የኢራኑ አያቶላህ ኻሜኒ የቅርብ ወዳጅ እንደሆ የሚነገርላቸው ሐሳን ናስራላህ መገደል ቴህራን ወደ ቴል አቪቭ የሚሳዔል ጥቃት እንድትሰነዝር ምክንያት ሆኗል።
እስራኤል በሐማስ የተፈጸመባትን ድንገተኛ ጥቃት ድፍን አንድ ዓመት በምትዘክርበት ወቅት በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ግጭት እጅጉን እየተካረረ ይገኛል።












