የሆሊውድ ተዋንያን የቪዲዮ ጌም ሠሪዎችን በመቃወም በድጋሚ አድማ ሊመቱ ነው

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
የአሜሪካ ተዋንያንን የሚወክለው ማኅበር የቪዲዮ ጌም ሠሪዎችን በመቃወም ሁለተኛ ዙር አድማ ለማካሄድ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ።
ማኅበሩ (SAG-AFTRA) ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን የተዋንያን ክፍያ እንዲጨመር ለመጠየቅና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሠራሽ አስተውሎት) በተዋንያን ላይ ያሳደረውን ጫና በመቃወም አድማ መደረጉ ይታወሳል።
የሆሊውድ ተዋንያን ከሐምሌ 31/2023 ጀምሮ ዋነኛ የቴሌቭዥን ድራማ እና ፊልም ሠሪዎችን በመቃወም አድማ አካሂደዋል።
የቪዲዮ ጌም አምራች ድርጅቶችን የሚወክለው ተቋም ቃል አቀባይ እንዳሉት፣ ሁለቱም ወገኖች ፍትሐዊ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ይፈልጋሉ።
ሁለተኛው አድማ ይካሄድ በሚለው ላይ ድምጽ የሚሰጠው ከመስከረም 5 እስከ 25 ባሉት ቀናት ነው።
በቪዲዮ ጌም ላይ ለሚሳተፉ ባለሙያዎች 11% የክፍያ ጭማሪ እንዲደረግ መጠየቁን ተዋንያኑን የሚወክለው ማኅበር ገልጿል።
ኤአይ በፈጠራ ባለሙያዎች ላይ አደጋ ስለደቀነ ከዚህ አደጋ እንዲጠበቁም ባለሙያዎቹ ጠይቀዋል።
የተሻለ የሥራ ሁኔታ እንዲመቻችም ጥያቄ አቅርበዋል።
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት የሆነችው ተዋናይት ፍራን ድሬቸር “ኤአይ ሥራችንን ችግር ውስጥ ከቷል። የሥራ ዕድሎች አጥብቦብናል። ማኅበራችን ሁሌም በአባሎቻቸን ጎን ይቆማል” ብላለች።
ማኅበሩ በመዝኛው ዘርፍ የሚሠሩ 160,000 ባለሙያዎችን ይወክላል።
ከቪዲዮ ጌም ሠሪ ድርጅቶች ጋር ስምምነቶች የተፈራረመ ሲሆን፣ ጥቅምት ላይ ስምምነቱ ቀኑ ያልፍበታል።
ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ቢደረግም አሁንም ውይይቶች መካሄድ ይኖርባቸዋል።
በውይይቶቹ የሚሳተፉትን 10 የቪዲዮ ጌም አምራቾች የሚወክለው ተቋም ቃል አቀባይ የሆነችው ኦድሪ ኩሊንግ የተዋንያንን ሚና የማያሳንስ “ፍትሐዊ ስምምነት” ላይ እንዲደረስ ይሻሉ ብላለች።
“በቀና ልብ እየተደራደርን ነው። ሁሉኑም ወገን የሚጠቅም ስምምነት ላይ በቅርቡ እንደርሳለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ስትልም አክላለች።
የቴሌቭዥን ድራማና ፊልም ሠሪዎችን በመቃወም የተደረገው አድማ ለ50 ቀናት የቀጠለ ነው። ከዚህ ቀደም ማኅበሩ አድማ የመታው ለ11 ወራት በ2016 ነበር።












