የሆሊውድ ጸሃፊዎች አድማቸውን ለማቆም ስምምነት ላይ ደረሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሆሊውድ ጸሃፊዎች የስራ ማቆም አድማቸውን ለማቆም የሚያስችል ጊዜያዊ ስምምነት ከስቱዲዮ ኃላፊዎች ጋር መድረሳቸውን ተናገሩ።

ጸሐፊዎቹ ለአምስት ወራት ያህል የዘለቀ የስራ ማቆም አድማም ካደረጉም በኋላ ነው ስምምነት ላይ ተደርሷል የተባለው።

የአሜሪካ ጸሐፊዎች ማህበር (ደብልዩጂኤ) ስምምነቱን በተመለከተም “ለጸሐፊዎች ትርጉም ያለው ጥቅም እና ጥበቃ የሚሰጥ፤ ልዩ ነው” ብሎታል።

ሆኖም በመጨረሻም ውሳኔው የማህበሩ አባላት ይሆናል።

ይህ የስራ ማቆም አድማ በሆሊውድ ውስጥ በአስርት አመታት ውስጥ ከተከሰቱት ረጅሙ ነው።

ለወራት ቀጥሎ በነበረው የስራ ማቆም አድማ አብዛኛው የፊልም እና የቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ቀጥ እንዲል ሆኗል።

ከጸሐፊዎቹ በተጨማሪ የፊልም ተዋናዮችም የስራ ማቆም አድማ ላይ ይገኛሉ።

ሚያዝያ መጨረሻ አካባቢ የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ ሆሊውድ የሚገኝባት የካሊፎርኒያ ግዛት ምጣኔ ኃብት በቢሊዮኖች በሚቆጠር ዶላር አስወጥቷታል።

የአሜሪካ ጸሃፍያን ማህበር አባላት ወደ ስራ ከመመለሳቸው በፊት ‘አሊያንስ ኦፍ ሞሺን ፒክቸር ኤንድ ቴሌቪዥን ፕሮዲውሰርስ’ ከተሰኘው እና ከ350 በላይ የቴሌቪዥን እና የፊልም ፕሮዳክሽን ኩባንያዎችን ከሚወክለው የንግድ ማህበር ጋር በሶስት አመት ውል መስማማት አለባቸው።

ማህበሩ በቀረበው የድርድር ሁኔታ በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮች መጠናቀቅ እንዳለባቸው አሳውቆ አድማውም አልቆመም ብሏል።

ነገር ግን “ከዛሬ ጀምሮ ማህበሩ እያደረገ ያለውን ተቃውሞ አቁሟል” በማለት አስታውቋል።

በተነሳው ውዝግብ ምክንያት በርካታ ታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ተከታታይ ፊልሞች እና ሌሎች ትዕይንቶች እንዲቋረጡ ምክንያት ሆኗል።

ከፊልም ኢንዱስትሪው ጋር በተዛማጅነት የሚሰሩ ምግብ የመዋቢያ እና አልባሳት አቅራቢዎች፣ አናጢዎች፣ የካሜራ ኦፕሬተሮችም ክፉኛ ተጎድተዋል።

በባለፉት ጥቂት ቀናት ታዋቂዎች የፊልም ማሳያዎቹ ኔትፍሊክስ፣ ዲዝኒ፣ ዩኒቨርሳል እና ዋርነር ብሮስ ኩባንያ ኃላፊዎች በድርድሩ በግላቸው መገኘት አዲስ ተስፋን ፈንጥቋል።

የሆሊውድ ጸሐፊዎችና ተዋናዮች ይህንን አድማ ለመምታት ዋነኛ ምክንያት የሆናቸው ክፍያ፣ የሥራ ሁኔታ እና በፊልሞች ላይ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) መጠቀም የፈጠረው ስጋት ናቸው።