‘ብሬክዳንስ’ እንዴት በኦሊምፒክ መድረክ የውድድር ስፖርት ሆኖ መጣ?

የፎቶው ባለመብት, Carroll Weston/BBC
አትሌቶችን በተለያዩ የስፖርት ውድድሮች በማሳተፍ የሚታወቀው ኦሊምፒክ አሁን ደግሞ ዳንሰኞችን ማሳተፍ ጀምሯል።
“ብሬክዳንስ” በፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ አንድ የመወዳደሪያ ዘርፍ ሆኖ ቀርቧል።
እአአ በ2018 በቦነስ አይረስ በተካሄደው የወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ብሬክዳንስ ተካቶ ነበር።
ለመሆኑ የዚህ ዳንስ አመጣጥ ምን ይመስላል?
ብሬክዳንስ የተጀመረው በ1970ዎቹ በኒው ዮርክ ከተማ ነው። ቢ-ቦይንግ ወይም ቢ-ገርሊንግ በመባልም ይታወቃል።
ከሮክ እስከ ላቲን የከበሮ ምቶች ላይ መሠረት በማድረግ የሚሰባበሩበት የዳንስ ዘይቤ ነው። እግር እና እጅን በመጠቀም ከፍተኛ እንቅስቃሴዎች ይደረጉበታል።
ብሬክዳንስ ከአሜሪካ ደቡብ ብሮንክስ ጎዳናዎች (ከፍተኛ ወንጀል እና ድህነት ያላበት አካባቢ ነው) የተጀመረ ሲሆን፣ ራስን ለመግለጽ ትልቅ ዘዴ ነው ይባላል።
ዳንሱ በፍጥነት ከኒው ዮርክ ውጭም ተስፋፋ። እአአ በ1980ዎቹ ደግሞ ለበርገር ኪንግ፣ ለፔፕሲ እና ለኮካ ኮላ ማስታወቂያዎችም ጥቅም ላይ ውሏል።
ከዚህም አልፎ ‘ዋይልድ ስታይል’፣ ‘ቢት ስትሪት’ እና ‘ብሬክዳንስ’ የተባሉ ዝነኛ ፊልሞች ዋና ማጠንጠኛ ሆነ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እአአ በ1985 የሂፕ ሀፕ የዳንስ ቡድን የሆነው ሮክ ስቴዲ ለወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን ዳንሱን አቀረበ።
ቀዳማዊት እመቤት ናንሲ ሬጋን ብሬክዳንስ ሲለማመዱ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ሲኤንኤን እጅ ይገኛሉ።
ዳንሱ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በጣም ተወዳጅ ከመሆኑ የተነሳ የአሜሪካው የራፕ ቡድን ‘ብሬክ ማሽን’ በ1984 የዩናይትድ ኪንግደም ምርጥ 40 ሙዚቃዎች ውስጥ ስትሪት ዳንስ፣ ብሬክ ዳንስ ፓርቲ እና አር ዩ ሬዲ የሚሉ ሙዚቃዎች ውስጥ ለመካተት በቅተዋል።
በመላዋ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ወጣቶች በቀለማት ባሸበረቁ ልብሶቻቸው ተውበው እንዲህም ይደነሳል? የመሬት ስበት ወዴት አለህ? የሚያስብሉ ዳንሶችን በገበያ ማዕከላት እና በምሽት ክበቦች ወለል ላይ ይከውኑ ጀመር።
የአሜሪካው የዳንስ ቡድን ደብሊውኤፍኤልኤ አባላት ኖቲንግሃም ደርሰው ከተመለሱ በኋላ ከተማዋ የዩኬ ብሬክዳንስ ማዕከል ሆነች።
በከተማው መሃል በሚገኘው ሮክ ሲቲ የምሽት ክበብ ውስጥ በብሬክዳንስ የሚወዳደሩ የዳንስ ቡድኖች ተፈጠሩ።
ዳንሱ በ1980ዎቹ መገባደጃ ላይ ተወዳጅነቱ ቢቀንስም ከዚያን ጊዜ ወዲህ በርካታ ወዳጆችን እያፈራ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ብሬክዳንስ በኦሊምፒክ ላይ እንዴት ይተገበራል?
በዚህ ረገድ የወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ የተሳካ መደላደል ፈጥሯል።
የ2018ቱ ውድድር በወንዶች፣ በሴቶች እና በድብልቅ [አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት] በሚል በሦስት ተከፍሎ ተከናውኗል።
በኦሊምፒክ ተወዳዳሪዎቹ በሦስት ደረጃዎች ይሳተፋሉ፡
ተወዳዳሪዎች ዳንሳቸውን በዳኞች ፊት ያቀርቡ እና ከፍተኛ ውጤት የተሰጣቸው የብሬክዳንስ ዳንሰኞች ወደ ቀጣዩ ዙር ያልፋሉ።
በመቀጠል እያንዳንዱ ዳንሰኛ አንድ ለአንድ ከሌሎች ጋር “ፉክክር” ውስጥ ይገባል።
አራቱን ቀሪ ተወዳዳሪዎች በጥሎ ማለፍ ለሜዳሊያ ይወዳደራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዳኞቹ አሸናፊዎችን እንዴት ይለያሉ?
በኦሊምፒክ ላይ እንደሚታዩት ሌሎች የዳንስ-ስፖርታዊ ውድድሮች ሁሉ የብሬክዳንስ ዳኞችም ተወዳዳሪዎችን በተለያዩ መስፈርቶች ይገመግማሉ።
የ2018 የወጣቶች ኦሊምፒክስ ‘ትሪቪየም ቫልዩ’ ሥርዓትን ለዳኝነት ጥቅም ላይ አውሏል።
ይህም ሦስት ሰፊ የግምገማ መለያዎችን ያካትታል። እነዚህም የአካል፣ የአቀራረብ እና የጥበብ ጥራት ናቸው።
የዳንሰኞች ቴክኒክ፣ ልዩ ሆኖ መታየት፣ ፈጠራ፣ ተጠባቂ አለመሆን እና ግለሰባዊነት ተደማምረው በመጨረሻው ውጤት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።












