ሩሲያ 120 ሚሳይሎችን ከአየር እና ከባሕር ላይ አስወነጨፈች - የዩክሬን ባለሥልጣናት

የዩክሬን ሰንደቅ ዓላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዩክሬን ትላልቅ ከተሞች ላይ ያነጣጠረ የሩሲያ ሚሳይሎች ጥቃት መፈጸሙን የአገሪቱ ባለሥልጣንት ገለጹ።

ይህንንም ተከትሎ በመላው ዩከሬን የአየር ጥቃት ማስጠንቂያዎችም እየተላለፉ ነው።

የፕሬዝዳንቱ አማካሪ ማይካሂሎ ፖዶሊያክ ሰላማዊ ዜጎች እና የሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ ከ120 በላይ ሚሳኤሎች ተወንጭፈዋል ብለዋል።

በዋና ከተማዋ ኪዬቭ ቢያንስ ሁለት ፍንዳታዎች የተሰሙ ሲሆን፣ ነገር ግን እነዚህ በሚሳኤል ጥቃቶች ወይም በአየር መከላከያዎች ስለመመከታቸው ግልጽ የሆነ መረጃ የለም።

በተጨማሪም በኻርኪቭ፣ ኦዴሳ፣ ሉቪቭ እና ዚሂቶሚር ከተሞች ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።

የደቡባዊ ኦዴሳ ግዛት መሪ ማክሲም ማርቼንኮ “በዩክሬን ግዙፍ የሚሳኤል ጥቃት መድረሱን” ተናግረዋል።

የዩክሬን አየር ኃይል በበኩሉ ሩሲያ አገሪቱን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከአየር እና ከባሕር ላይ በሚወነጨፉ የክሩዝ ሚሳኤሎች እያጠቃች ነው ብሏል።

በተጨማሪም በርካታ የካሚካዚ ሰው አልባ አውሮፕላኖችም ጥቅም ላይ ውለዋል ብሏል።

ሐሙስ ማለዳ ላይ የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያዎች በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተሰምተዋል።

የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ኦሌክሲይ አሬስቶቪች ሰላማዊ ዜጎች እነዚህን ጥቃቶች የሚከላከል መጠለያ እንዲፈልጉ አሳስበው፣ የአገሪቱ የአየር መከላከያ ሠራዊት ጥቃቱን እየተከላከለ ነው ብለዋል።

የኪዬቭ የከተማው ወታደራዊ አስተዳደር በበኩሉ ተመትቶ የወደቀ ሮኬት ቁርጥራጭ ህንጻ ላይ መውደቁን ገልጸዋል። በዚህም በዋና ከተማዋ “በርካታ ፍንዳታዎች” መከሰታቸውን ከንቲባ ክሊችኮ ተናግረዋል።

የደቡባዊቷ ግዛት ሚኮላይቭ አስተዳዳሪ ቪታሊ ኪም አምስት ሚሳኤሎች በአየር መከላከያ መክሸፋቸውን ጽፈዋል።

የምዕራባዊቷ የሊቪቭ ከተማ ከንቲባ አንድሪ ሳዶቪ በርካታ ፍንዳታዎች መከሰታቸውን ተናግረዋል።

ፖዶሊያክ ሩሲያ “ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ለማውደም እና ሰላማዊ ዜጎችን በጅምላ ለመግደል” አቅዳለች ሲሉም ወቅሰዋል።