የፈረንሳዩ መምህር ተቀልቶ እንዲገደል አነሳስተዋል የተባሉ ስምንት ሰዎች ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በፈረንሳይ ከአራት ዓመታት በፊት ሳሙኤል ፓቲ የተሰኘው መምህር ተቀልቶ እንዲገደል የጥላቻ ዘመቻዎችን ሲያካሂዱ ነበር የተባሉ ስምንት ግለሰቦች ጥፋተኛ ተባሉ።
ሰባት ወንድና አንዲት ሴት በመምህሩ ግድያ ሚና ተጫውተዋል በሚል ከሶስት እስከ 16 ዓመት የሚደርስ ቅጣት ተበይኖባቸዋል።
ሳሙኤል በፓሪስ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የታሪክ እና የጂኦግራፊ መምህር ነበር።
ጥቃቱ የተፈጸመው ሳሙኤል "ሐሳብን በነጻነት መግለጽ" በተሰኘ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ወቅት ለተማሪዎቹ የነብዩ መሀመድን አጸያፊ ምስሎች አሳይቷል በሚል በማህበራዊ ሚዲያ በሃሰት መወንጀሉን ተከትሎ ነው።
የቼቼንያ ተወላጅ ጽንፈኛው የ18 ዓመቱ አብዱላህ አንዞሮቭ ሳሙኤልን በሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ገድሎታል። አንዞሮቭ የ47 ዓመቱን መምህር ከገደለ ከደቂቃዎች በኋላ በፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ተገድሏል።
ግድያው ከመፈጸሙ ከቀናት በፊት ሳሙኤል ሙስሊም ተማሪዎችን ክፍሉን ለቀው እንዲወጡ ካዘዘ በኋላ "አጸያፊ" የተባለውን የነቢዩ መሐመድ ምስልን አሳይቷል የሚሉ የማህበራዊ ሚዲያ ውንጀላዎች ገዳዩን አነሳስተውታል ተብሏል።
እውነታው ግን ፓቲ ሐሳብን በነጻነት መግለጽ በሚመለከት ትምህርት እየሰጠ በነበረበት ወቅት ነብዩ መሐመድን ይወክላሉ የተባሉት በቻርሊ ሄብዶ መጽሄት መጀመሪያ የወጡ አወዛጋቢ ካርቱኖችን አሳይቷል።
መምህሩ ከማሳየቱ በፊት እነዚህ ምስሎች ቅር የሚያሰኟችሁ ከሆነ አይናቸውን እንዲጨፍኑ ተማሪዎቹን ጠይቋል።
በአንደኛው የቻርሊ ሄብዶ ካርቱን ላይ ነብዩ መሃመድ በተርባን ጥምጥም ፈንታ ቦምብ ጭንቅላታቸው ላይ መታየቱ አወዛጋቢ መሆኑ ይታወሳል።
ገዳዩ በሌለበት የዋለው ይህ ችሎት በሞራል እና በቁሳቁስ ድጋፍ ያደረጉ ሰዎች ላይ ያተኮረ ነበር።
በእድሜ ትንሿ ተጠርጣሪ ግድያው ሲፈፀም እድሜዋ 13 የነበረ ሲሆን፣ መምህሩ ከመገደሉ ዘጠኝ ቀናት በፊት ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት በሌላቸው ምክንያቶች ከትምህርት ቤቱ ታግዳ ነበር። በዚህም የነብዩ መሐመድ ካርቱን በታየበት ክፍል ጊዜም አልተገኘችም ተብሏል።
ከሰባት ሳምንታት በላይ የወሰደው የፍርድ ሂደት አንዲት የ13 ዓመት ተማሪ የተናገረችው ውሸት በማህበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቶ ከቁጥጥር ውጭ እንደሆነ ተሰምቷል።
አርብ ዕለት ከተፈረደባቸው መካከል የዚህች ልጅ አባት ብራሂም ቺኒና ይገኙበታል።
ቺኒና በመምህሩ ላይ በበይነ መረብ ዘመቻ የጀመረ ሲሆን የጽንፈኛ እስላም አክቲቪስት አብዱልሃኪምን እርዳታ ጠይቋል ተብሏል። አብዱልሃኪም በዚህ ችሎት የጥፋተኝነት ብይን ተላልፎበታል።
መሳሪያ ሲገዛ አብረውት የነበሩ የገዳዩ ሁለት ጓደኞች ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል። እንዲሁም በጉዳዩ ላይ መልዕክት አካፍሏቸዋል የተባሉ አራት ሰዎችም ግድያን በማነሳሳት ወንጀል ተፈርዶባቸዋል።












